
ከ 3 ሰአት በፊት
ፖሊስ ከአንድ ሳምንት በፊት ሦስት ታዳጊ ሴት ልጆቹን ገድሏል ያለውን የዋሽንግተን ነዋሪ እየፈለገ ነው።
የ32 ዓመቱ ትራቪስ ዴከር በእገታ እና የዘጠኝ፣ የስምንት እና የአምስት ዓመት ዕድሜ ያላቸውን ሦስት ልጆቹን በመግደል በመጀመሪያ ደረጃ የግድያ ወንጀል እንደሚፈለግ የዋሽንግተን ግዛት ዌናች ፖሊስ መሥሪያ ቤት ገልጿል።
ከቤት ውጭ ያሉ እንቅስቃሴዎችን እንደሚያዘወትር የተገለፀው ዴከር በተራራማና በደን በተሸፈነ ገጠራማ ሥፍራ እንደተደበቀ ባለሥልጣናት ያምናሉ።ይህም ፍለጋውን አስቸጋሪ አድርጎታል ብለዋል።
“ከቀረበ አደጋ ሊያደርስ እንደሚችልም” የተሰጋ ሲሆን ግለሰቡ ምን ሊያደርግ እንደሚችል ግን ፖሊስ አልገለጸም ።
ፔቲይን፣ ኢቭንሊ እና ኦሊቪያ የተባሉት ታዳጊዎቹ ራቅ ባለ ሥፍራ በሚገኝ ካምፕ ውስጥ ታፍነው መሞታቸውን ፖሊስ የገለጸው በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ ነበር።
የታዳጊዎቹን መጥፋት እናታቸው ለፖሊስ ያሳወቀችው ከዘጠኝ ቀናት በፊት ሲሆን የልጆቿ አባት ዴከር ልጆቹን ለማየት ከወሰደ በኋላ ሳይመልስ ሲቀር ነበር ለፖሊስ ያሳወቀቸው።
ዴከር የስልክ ጥሪዋንም አልመለሰም ነበር።
ከጥቂት ቀናት በኋላም ፖሊስ ከካምፑ አቅራቢያ የሦስቱን ልጆች አስክሬን አግኝቷል።
ፖሊስ የዴከርን የእጅ ስልክ እዚያው መሬት ላይ ያገኘው ሲሆን እርሱ ግን በሥፍራው አልነበረም። እንደ መኖሪያ ይገለገልበታል ተብሎ የሚታመነው መኪናውም በአቅራቢያው ተገኝቷል።
የቺላን ካውንቲ ሸሪፍ ማይክ ሞሪሰን ዴከር ካለበት እንዲመለስ ጥሪ ባቀረቡበትና ረቡዕ ዕለት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ” ምንም ዓይነት ምክንያት ተቀባይነት የለውም።ጤነኛ አዕምሮ ያለው ሰው እንዲህ ዓይነት ድርጊት አይፈፅምም” ብለዋል።
ዴከር ከቤት ውጭ ያለውን ሕይወቱን የሚመራበት ክህሎቱ የአሜሪካ ፌደራል ፖሊስን ጨምሮ የባለሥልጣናቱን ፍለጋ አዳጋች ለማድረግ ሳይረዳው እንዳልቀረም ሸሪፍ ሞሪሰን ገልጸዋል።
ሸሪፍ ሞሪሰን ከዴከር ቤተሰቦች ጋር ከተነጋገሩ በኋላ እንዳሉት ዴከር አንዳንድ ጊዜ ከቤት ከወጣ እስከ ሁለት ወር ተኩል ድረስ አይመለስም።
በመሆኑም ልጆቹን ከመግደሉ በፊት ከአካባቢው ወጥቶ ራሱን ለመደበቅ ሁኔታዎችን ሳያመቻች እንዳልቀረ እና ለረጅም ጊዜ እንዴት መቆየት እንዳለበት ያለው እውቀቱ እንደረዳው ሸሪፍ አስረድተዋል።
” ለዚህ ሰላማዊ የሆነ መፍትሄ እንፈልጋለን፤ ሆኖም ግን ጥረታችንን አናቋርጥም” ያሉት ሸሪፍ ሞሪሰን፣ ዴከር ከተደበቀበት ወጥቶ እጁን እንዲሰጥ ጠይቀዋል። ” ድብብቆሹን እንተወውና ለልጆችህ ትክክለኛ የሆነውን ነገር እናድርግ ” ብለዋል ሸሪፍ ባስተላለፉት መልዕክት።
የአሜሪካ ማርሻል አገልግሎት ረቡዕ እለት ዴከር ያለበትን ለጠቆመ 20 ሺህ ዶላር ሽልማት እንደሚሰጥ አስታውቋል።
ፍለጋው በአካባቢው በተጓዦች ለሚዘወተሩና ታዋቂ ለሆኑ በርካታ ብሔራዊ ፓርኮች መዘጋት ምክንያት ሆኗል።