
ከ 5 ሰአት በፊት
ፋጡ ውሬ፣ ቤተሰቦቿ እና ወዳጆቿ በአሜሪካ ውስጥ ስመ ጥር በሚባለው ሐርቫርድ ዩኒቨርስቲ ለድኅረ ምረቃ ትምህርቷ ለመክፈል 200 ሺህ ዶላር አሰባስበዋል።
ሴራሊዮናዊቷ ፋጡ ከሐርቫርድ ዩኒቨርስቲ ለመመረቅ የቀራት ጥቂት ወራቶች ናቸው።
ሆኖም ዶናልድ ትራምፕ ሐርቫርድ ከውጭ አገር የመጡ ተማሪዎችን እንዳይቀበል እንዲሁም በውጭ አገራት የሚገኙ ኤምባሲዎች ለተማሪዎች የሚሰጡትን ቀጠሮ እንዲያቆሙ ማገዳቸውን ተከትሎ የፋጡ ቀጣይ ዕጣ ፈንታ አጣብቂኝ ውስጥ ገብቷል።
ለፋጡ ሐርቫርድ ዩኒቨርስቲ በተቀበላት ወቅት ትልቅ ዕድል ነበር።
“ለቤተሰባችንም ሆነ ለማኅበረሰባችን የትውልዱ ትልቅ ዕድል አድርገው ነበር ያዩት” ትላለች በሐርቫርድ ቲኤች ቻን ስኩል ኦፍ ፐብሊክ ኸልዝ የዶክትሬት ተማሪ የሆነችው ፋጡ።
ፋጡ በሴራሊዮን የሴቶች የማህጸን ዕጢ ያለውን ተጽእኖ በሐርቫርድ ቆይታዋ እያጠናች ትገኛለች።
ነገር ግን ለመመረቅ ጥቂት ወራት ሲቀራት ያ ሁሉ መስዋዕትነት እና ልፋት መና ሊቀር ነው የሚለው ሃሳብ እና ጭንቀት ሆኖባታል።
የፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር በውጭ አገር የሚገኙ ኤምባሲዎቻቸው የተማሪ ቪዛ ቀጠሮዎችን መስጠትን ለጊዜው እንዲያግዱ ትዕዛዝ አስተላልፏል።
የአመልካቾችን የማኅበራዊ ሚዲያ ገጾች የማጣራት ሂደት ለማስፋት በዝግጅት ላይ እንዳለ ያስተዋወቀው አስተዳደሩ፤ ለተማሪዎች አዳዲስ የቪዛ ቀጠሮ እንዳይሰጥ ሲል መከልከሉ ተገልጿል።
ይህም ትራምፕ ከመጠን በላይ ‘ሊበራል’ በሚሏቸው አንዳንድ ስመ ጥር ዩኒቨርስቲዎች ላይ እየወሰዱት ያለው ሰፋ ያለ እርምጃ አካል መሆኑም ተጠቅሷል።

የተማሪዎች የቪዛ ቀጠሮች እንዲቆም መወሰኑን ተከትሎ ጥያቄ የቀረበላቸው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ታሚ ብሩስ “ወደ አገራችን የሚመጡ ሰዎችን ማንነት የማጣራት ተግባራችንን በቁም ነገር የምንወስደው ነው። ያንንም በማድረግ እንቀጥላለን” ብለዋል።
ይህ እርምጃ የመመረቂያ ጽሁፏን ለመከላከል እና በመጪው ኅዳር ወር ለምትመረቀው ፋጡ “ወደ አሜሪካ መመለስ እችል ይሆን?” የሚለው ጭንቀት ውስጥ ከቷታል።
“ውሳኔው እርግጠኛ አለመሆንን ይፈጥራል። እንደ ዶክትሬት ተማሪነቴ ምርምሬ በእንቅስቃሴ ላይ የተመሠረተ ነው። እንዲህ ዓይነት መዘግየቶች ጥናቶችን ከማደናቀፍ በተጨማሪ እንቅስቃሴዎችን ይገታሉ” ትላለች።
ፋጡ ወደ ሐርቫርድ ዩኒቨርስቲ ስትገባ “ለአህጉሪቷ ተስፋ ሰንቃ” እንደሆነ ትናገራለች።
እንደ ፋጡ ያሉ ተማሪዎች በግል ወይም በአካዳሚያዊ ምክንያቶች የጥናት ቆይታቸውን ማራዘም ይችላሉ። እንዲህ ዓይነት ሁኔታዎች በሚያጋጥሙበት ወቅት ቪዛቸውን ለማስረዘም አይ-20 የተሰኘ ቅጽ ያስገባሉ።
ይህ የኢሚግሬሽን ቅጽ በዩኒቨርስቲ ተቋማት የሚሰጥ ሲሆን በሙሉ ጊዜያቸው ተማሪ እንደሆኑ እና ትምህርቱን ለመጨረስ በቂ የገንዘብ አቅም እንዳላቸው የሚያሳይ ሕጋዊ ሰነድ ነው።
ፋጡ አይ-20 ሰነዷን ተቀብላለች፤ ይህም ማለት ወደ ሐርቫርድ ለመመለስ እና የዶክትሬት ፕሮግራሟን ለመጨረስ የዩኒቨርስቲውን እንዲሁም በቂ ገንዘብ እንዳላት መስፈርቶቹን አሟልታለች።
ነገር ግን በቅርቡ የትራምፕ አስተዳደር ባወጣው ፖሊሲ ምክንያት በአሁኑ ወቅት ለቪዛ ቀጠሮ ማመልከት አትችልም።
የተማሪዎችን የቪዛ ቀጠሮ ማገድ ውሳኔ ሙሉ በሙሉ እንዲሁም በዘላቂነት ከተተገበረ፤ “አሳዛኝ ጉዳት ነው” የምትለው ፋጡ “ምርምሯ እና ጥናቷም” ይቆማል።
የገንዘብ እና የስሜት ጉዳት
ፋጡ በሃርቫርድ ዩኒቨርስቲ የተጠየቀችውን በሺዎች የሚቆጠር ዶላር ለትምህርቷ ለመክፈል በእሷ እና በቤተሰቦቿ ላይ ከፍተኛ ጫና አሳርፎባታል።
“ብድር ተበድሬያለሁ። የዶክትሬት ትምህርቴን እየተማርኩ እየሠራሁ ነበር። ማለቂያ የሌላቸው ወጪዎች ለቪዛ፣ ለመኖሪያ ቤት፣ ለጤና አገልግሎት ከፍያለሁ። ከገንዘቡ በተጨማሪ በተደጋጋሚ ከአሜሪካ የኢሚግሬሽን ሥርዓት ጋር መታገል እንዲሁም በአገሪቱ ሕግ እና ሥርዓት አክብሮ ለመመራት ሞክረናል። እያንዳንዷ መዘግየት ዶላሮችን ያስከፍላል፤ የአእምሮ ሰላማችንንም የሚያስከፍል ነው” ትላለች።
ፋጡ በግል የደረሰባት ብቻ ሳይሆን፤ የፖሊሲው አንድምታ ለወደፊቱ አፍሪካውያን ምሁሮች ያስጨንቃታል።
“ይጎዳል። እኔን ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ የትምህርት በሩ ለጠበባቸው አፍሪካውያን ተማሪዎች የሚጎዳ ነው። በዚህ መልኩ እንዲህ ፍጹም ሲዘጉ፤ ሲጀመርም በእነዚህ ስፍራዎች መገኘታችን እንደ ምንም እንደማይታይ ነው” ስትል ትገልጻለች።
ከዚህ ቀደም በአሜሪካ ትምህርታቸውን ለመከታተል የሚፈልጉ የውጭ አገር ተማሪዎች ቪዛ ከመሰጠቱ በፊት በአገራቸው በሚገኝ የአሜሪካ ኤምባሲዎች ቃለ መጠይቆችን ማድረግ ይጠበቅባቸው ነበር።
በአውሮፓውያኑ 2023/24 የትምህርት ዓመት ከ210 አገራት የተውጣጡ ከ1.1 ሚሊዮን በላይ ዓለም አቀፍ ተማሪዎች ወደ አሜሪካ ዩኒቨርስቲዎች መግባታቸውን የውጭ አገር ተማሪዎችን መረጃ የሚሰበስበው ‘ኦፕን ዶርስ’ የተሰኘው ተቋም አስታውቋል።
ፋጡ፣ አሜሪካ “ዓለም አቀፍ ትምህርትን እንደ የጋራ ኢንቨስትመንት ዕውቅና የሚሰጡ” ፖሊሲዎችን በሥራ ላይ ማዋል እንዳለበት ታስባለች።
ፋጡ አክላም “አሜሪካ ክህሎትን መቀበል ብቻ ሳይሆን በዚህም እያደገች ነው” ስትል ታስረዳለች።
ለዶናልድ ትራምፕ መልዕክት እንዳላት የተጠየቀችው ፋጡ “ፖሊሲዎች ሊያገሉ ወይም ሊያነቃቁ ይችላሉ። አዎ የመጣነው ልንማር ነው። ነገር ግን ልንመራ፣ ልንገነባ እንዲሁም አስተዋጽኦ ለማድረግ ነው። ታሪክ በሮችን እንደዘጉ ሳይሆን እንደከፈቱ ሰው አድርጎ አድርጎ እንዲያስብዎት ይሁን” ስትል መልዕክት አስተላልፋለች።