
ከ 2 ሰአት በፊት
በዩናይትድ ኪንግደም ፖሊስ ሕጋዊ ሰነድ የሌላቸው ስደተኞችን የሚበዘብዙ ቀጣሪዎችን ኢላማ ማድረጉን ተከትሎ በሕገ ወጥ ሥራ ላይ የተሰማሩ ሰዎች እስር መበራከቱን የአገሪቱ መንግሥት ገለጸ።
ባለፈው ዓመት ብቻ በዩኬ በሚገኙ ተቋማት ላይ ፖሊስ ባካሄደው ዘመቻ የኢሚግሬሽን ባለሥልጣናት ከ6 ሺህ 400 በላይ ሰዎችን ማሰራቸውን የአገር ውስጥ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ያወጣው መረጃ አመልክቷል።
ይህ ቁጥር ከቀደመው ዓመት ጋር ሲነጻጸር ከ51 በመቶ በላይ እንደሚልቅም መሥሪያ ቤቱ ባወጣው መረጃው ገልጿል።
ሆኖም ከእነዚህ እስሮች ውስጥ ምን ያህሎቹ ወደ ክስ፣ ወደ ፍርድ ወይም ከአገር መባረርን እንደሚያስከትሉ አልገለጸም።
የኢሚግሬሽን ሕግ አስፈፃሚዎች የአገሪቱን የኢምግሬሽን ሥርዓት የሚጥሱ እና ተጋላጭ የሆኑ ሰዎችን የሚበዘብዙ አካላትን ለመከላከል ሥራውን ማጠናከሩንም መረጃው ጠቅሷል።
ባለሥልጣናት ሕጋዊነትንና የሥራ ሁኔታን ለማየት ከ9ሺህ በላይ ተቋማትን የጎበኙ ሲሆን ከእነዚህ መካከል ምግብ ቤቶች ፣ የጥፍር ሳሎን እና የግንባታ ሥፍራዎች ይገኙበታል።
እንዲህ ያሉ ተቋማት በአብዛኛው ስደተኞች ምቹ ባልሆነ፣ በሕገ ወጥ የሥራ ሰዓት እና በዝቅተኛ ክፍያ እንዲሰሩ ያደርጋሉ።
የአገር ውስጥ መሥሪያ ቤቱ እንዳለው ስደተኛ ሰራተኞችን የሚበዘብዙ በርካታ ተቋማት አሉ።
ለአብነትም በሱሪይ በካራቫን ፓርክ በመላላክ [ደሊቨሪ] ሥራ ላይ ተሰማርተው እየሰሩ የነበሩ ዘጠኝ ሰዎች መታሰራቸውን ጠቅሷል።
መጋቢት ወር ላይ በተካሄደ ዘፊ ዘመቻም የፖሊስ መኮንኖች በቤልፋስት ታይታኒክ ኳርተር በሚገኝ የግንባታ ሥራ ላይ ተሰማርተው የነበሩ 36 ሰዎችን በቁጥጥር ሥር አውለዋል። ከእነዚህ መካከል አንዳንዶቹ በአገሪቷ ለመቆየት የተፈቀደላቸውን ጊዜ ያሳለፉ ሲሆኑ ሌሎቹ ደግሞ የሥራ ፈቃድ የሌላቸው ናቸው።
የኢሚግሬሽን ሕግ አስፈፃሚ ዳይሬክተር ኤዲ ሞንትጎምሪይ እንዳሉት በርካቶቹ በዩኬ በነጻነት መኖር እና መሥራት እንደሚችሉ በሕገ ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች ውሸት ተታለው የገቡ ናቸው።
“እውነታው ግን እነዚህ ሰዎች መጨረሻቸው አስቸጋሪ የሆነ የኑሮ ሁኔታን መጋፈጥ ፣ ዝቅተኛ ክፍያ እና ሰብዓዊነት በጎደለው የሥራ ሠዓት መሥራት ነው” ብለዋል።
የድንበር ደኅንነት እና ጥገኝነት ሚኒስትር ዴም አንጀላ ኤግል፣ “መንግሥት የድንበር ደኅንነትን የሚጥሱ እና ሕገ ወጥ ቀጣሪዎችን ከሥሩ ነቅሎ ማውጣቱን ይቀጥላል” ብለዋል።
ባለፈው ዓመት በዩኬ የመሥራት እና መኖር መብት የሌላቸውን ወደ 30 ሺህ የሚጠጉ ሰዎችን ወደ መጡበት መመለሱን መንግሥት አስታውቋል።
የሥራ ቪዛን እና እንዲቆዩ ከተሰጣቸው ጊዜ በላይ የሚቆዩ ስደተኞችን ለመከላከል ሕግ በማውጣት ሕገ ወጥ ስደትን እየታገለ መሆኑንም አክሏል።
ከዚህም በተጨማሪ አንዳንዶች ወደ አገሪቷ ለመግባት ተጠቅመውበታል ያለውንና በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ወቅት የተጀመረውን ለእንክብካቤ ሰራተኞች ይሰጥ የነበረውን ልዩ ቪዛ መሰረዙን ገልጿል።
መንግሥት እየወሰደ ባለው እርምጃ ላይ የተለያዩ አስተያየቶች የተሰጡ ሲሆን አንዳንድ የንግድ ተቋማት በሥራ ቪዛ ላይ የተጣለውን ገደብ የተቃወሙት ሲሆን አንዳንድ ወግ አጥባቂዎች ደግሞ ማሻሻያው ሕገ ወጥ ስደትን ለማስቆም በቂ አይደለም ብለዋል።
የቅርብ ጊዜ መረጃዎች እንዳመለከቱት በዚህ ዓመት እስከ ሚያዝያ ወር ድረስ ባለው ጊዜ ብቻ ወደ 44 ሺህ የሚጠጉ ሰዎች በሕገ ወጥ መንገድ ወደ ዩኬ የገቡ ሲሆን ከ80 በመቶ በላይ የሚሆኑት የገቡት በአነስተኛ ጀልባዎች በሚደረግ ሕገ ወጥ ጉዞ ነው።