የ29 ዓመቱ ኪልማር አብሬጎ ጋርሲያ

ከ 3 ሰአት በፊት

የአሜሪካ ጠቅላይ ፍርድ ቤት በስህተት ከአገር ተባሯል በሚል የትራምፕ አስተዳደር እንዲመልሰው ሲጠይቀው የነበረው የኤል ሳልቫዶር ተወላጅ ክስ ተመሰረተበት።

አሜሪካ በስህተት ወደ ኤል ሳልቫዶር ያባረረችውን ይህንን ግለሰብ ወደ አገር መልሳ በሁለት የፌደራል ወንጀሎች ክስ እንደመሰረተችበት ገልጻለች።

የ29 አመቱ ኪልማር አብሬጎ ጋርሲያ በመጋቢት ወር ነበር ከአሜሪካ የተባረረው።

ኪልማር በአሁኑ ወቅት ሕጋዊ ፈቃድ የሌላቸውን ስደተኞች ከቴክሳስ ወደ ሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች በማዘዋወር ለበርካታ ዓመታት በሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ሴራዎች ተሳትፏል የሚል ክሶች ቀርበውበታል።

አሜሪካ በግለሰቡ ላይ የእስር ማዘዣ ካቀረበች በኋላ ኤል ሳልቫዶር ኪልማርን ለመልቀቀ መስማማቷን ጠቅላይ አቃቤ ህግ ፓም ቦንዲ አርብ ዕለት ገልጸዋል።

የኪልማር ጠበቃ በበኩላቸው የደንበኛቸውን ክስ “አሳፋሪ” ሲሉ ጠርተውታል።

ግለሰቡ፣ አሜሪካ ከአገር አባራቸው በኤል ሳልቫዶር አደገኛ እስር ቤት እንዲገቡ ከተደረጉ 250 ሰዎች መካከል አንዱ ነው።

የአሜሪካ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ኪልማር ከአገር የተባረረበት ሁኔታ ሕጋዊ አይደለም በማለት ዋይት ሐውስ እንዲመልሰው በሚያዝያ ወር ውሳኔ ያሳለፈ ሲሆን ፤ ዋይት ሃውስም ይህንን ብያኔ ሲቃወም ቆይቷል።

ኪልማር በቴኔሲ ፍርድ ቤት የውጭ ዜጎችን ለማጓጓዝ በማሴር እና ሕጋዊ ሰነድ የሌላቸውን ግለሰቦች በሕገወጥ መንገድ በማጓጓዝ የሚሉ ክሶች ቀርበውበታል።

ጠቅላይ አቃቤ ሕግ እንዳሉት ኪልማር በሕገወጥ የሰዎች ዝውውር “ጉልህ ሚና” የተጫወተ፤ እንዲሁም በሺዎች የሚቆጠሩ ሕገወጥ ስደተኞችን ወደ አሜሪካ ለማዘዋወሩ መረጃ እንዳላቸው ተናግረዋል።

ክሱ፣ ግለሰቡ ከአውሮፓውያኑ 2016 ጀምሮ ሰነድ የሌላቸውን ግለሰቦች ከቴክሳስ ወደ ሜሪላንድ እና በሌሎች ግዛቶች መካከል ከ100 ጊዜ በላይ አጓጉዟል የሚል ተካቶበታል።

በተጨማሪም አሜሪካ የውጭ አገር አሸባሪ ድርጅት ብሎ የፈረጀችውን ኤምኤስ- 13 አባላትን አጓጉዟል ሲል ክሱ አትቷል።

የትራምፕ አስተዳደር ቀደም ሲል ግለሰቡን ድንበር ተሻጋሪ የሆነው የሳልቫዶር ወሮበላ ቡድን አባል ነው ሲል ወንጅሎት ነበር።ኪልማር ይህንን አልተቀበለውም።

ጠቅላይ አቃቤ ሕጉ በተጨማሪም ለዚህ የወሮበላ ቡድን የጦር መሳሪያ እና አደንዛዥ ዕጾችን ያዘዋውራል ሲሉ ኪልማርን ቢወነጅሉም፤ በፍርድ ቤት በቀረበው ክስ ላይ ግን ይህ አልተካተተም።

ኪልማር አርብ ዕለት በቴኔሲ ፍርድ ቤት ቀርቧል።

የግለሰቡ ጠበቆች ደንበኛቸው ከዚህ ቀደም በአሜሪካም ይሁን በኤል ሳልቫዶር በቀረበበት የወሮበላ ቡድን አባልነት ውንጀላም ይሁን በማንኛውም ወንጀል ተከሶ እንደማያውቅ ተከራክረዋል።

ከጠበቆቹ አንዱ የሆኑት ሲሞን ሳንዶቫል ሞሼንበርግ ክሱን “አሳፋሪ” እንዲሁም አጠቃላይ ሁነቱን “ሥልጣንን አላግባብ መጠቀም” ሲሉ ፈርጀውታል።

“መንግሥት የፍርድ ቤት ትዕዛዝን በመተላለፍ ኪልማርን በውጭ አገር እስር ቤት አጥፍተውት ነበር። አሁን ከወራት መዘግየት እና ሚስጥራዊ አካሄድ በኋላ ስህተታቸውን ለማረም ሳይሆን ለፍርድ ለማቅረብ እየመለሱት ነው” ብለዋል።

ጠበቃው አክለውም “ይህ ሥልጣንን ያለ አግባብ መጠቀም እንጂ ፍትህ አይደለም። መንግሥት [በአውሮፓውያኑ] 2019 ጉዳዮን ወደተመለከቱት የኢሚግሬሽን ዳኛ አቅርቦ ፍትሃዊ የፍርድ ሂደት እንዲያገኝ ሊያመቻች ይገባል” ብለዋል።

ኪልማር ገና በታዳጊነቱ ነው ከኤል ሳልቫዶር ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ ወደ አሜሪካ የገባው።

በአውሮፓውያኑ 2019 በሜሪላንድ ውስጥ ከሌሎች ሦስት ሰዎች ጋር በፌደራል የኢሚግሬሽን ባለስልጣናት ተይዞ ነበር።

ሆኖም የኢሚግሬሽን ዳኛ በትውልድ አገሩ ባሉ የወሮበላ ቡድኖች ጥቃት ሊደርስበት ይችላል በሚል ምክንያት ከአገር እንዳይባረር ጥበቃ አድርጎለታል።

ከዚያ በኋላ በያዝነው ዓመት መጋቢት ወር በትራምፕ አስተዳደር ከአገር የተባረረ ሲሆን የአገሪቱ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሕጋዊ አይደለም በሚል ወደ አሜሪካ እንዲመለስ ብያኔ አስተላልፏል።