ቡና በስኒ

ከ 5 ሰአት በፊት

ቀደም ባሉት ጊዜያት ቡና ከጤና እክሎች ጋር ተያይዞ ስሙ በክፉ ይነሳ ነበር። ነገር ግን ባለፉት አስርት ዓመታት የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ቡና መጠጣት ለጤና በረከት ሊሆን ይችላል።

ካፌይን በዓለም ላይ በጣም ታዋቂው አነቃቂ ንጥረ ነገር ነው።

ሰዎች ለዘመናት ተፈጥሯዊ የካፌይን ምንጭ የሆነውን ቡና ሲጠጡ ቢቆዩም በጤና ላይ አለው ተብሎ ከሚናፈሰው አሉታዊ ወሬ ጋር ተያይዞ ለአስርት ዓመታት እርስ በእርሳቸው የሚጣረሱ መልዕክቶች ሲተላለፉ ቆይተዋል።

በለንደን ኢምፔሪያል ኮሌጅ የካንሰር ኤፒዲሚዮሎጂ ፕሮፌሰር እና በዓለም አቀፍ የካንሰር ምርምር ኤጀንሲ (አይኤአርሲ) ኃላፊ የሆኑት ማርክ ጉንተር “በተለምዶ ቡና እንደ መጥፎ ነገር ይታይ ነበር” ይላሉ።

“በ1980ዎቹ እና 90ዎቹ የተደረጉ ጥናቶች ቡና የሚጠጡ ሰዎች ለልብ ችግር የመጋለጥ ዕድላቸው ከፍ ያለ ነው የሚል መደምደሚያ ላይ ደርሰዋል፤ ነገር ግን ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ነገሮች እየተለወጡ መጥተዋል።”

ጉንተር ባለፉት አስርት ዓመታት ውስጥ ሰፋ ያለ ቁጥር ያላቸው ሰዎች ላይ በተደረጉት ጥናቶች የተነሳ፣ ተመራማሪዎች አሁን በመቶ ሺዎች ከሚቆጠሩ ቡና ጠጪዎች መረጃ ሰብስበዋል።

ታድያ እነዚህ ጥናቶች ምን ይነግሩናል? የቡና ፍጆታችን ያላቸውን የጤና ጥቅሞችን ወይስ አደጋዎችን?

ቡና የተጠበሱ ዳቦዎች፣ ኬኮች እና ድንች ጥብስ ውስጥ የሚገኘው አሲሪላሚድ የተባለ ካንሰር አምጪ ንጥረ ነገር በመያዙ ተነሳ ለካንሰር የማጋለጥ ዕድሉ ከፍተኛ ነው ተብሎ ይታመን ነበር።

አሲሪላሚድ በየዕለቱ በከፍተኛ ሙቀት በሚበስሉ እንደ ድንች ጥብስ ያሉ የስታርች ይዘት ያላቸው ምግቦች ውስጥ የሚከሰት ነው።

ነገር ግን በአውሮፓውያኑ 2016 ቡና ከ65 ዲግሪ ሴንቲግሬድ በላይ በጣም የፈላ ካልሆነ በስተቀር ካንሰርን አያመጣም ሲል ደምድሟል።

በ2023 በተደረገ ግምገማ ደግሞ ቡና በአመጋገባችን ውስጥ የአሲሪላሚድ ዋነኛ ምንጭ ከሆኑት መካከል አንዱ ቢሆንም፣ ለካንሰር ከሚያጋልጡን ነገሮች መካከል ስለመሆኑ ግን ገና ጠንካራ መደምደሚያ ያለው ማስረጃ ላይ አልተደረሰም ሲሉ ይሞግታሉ።

ጥናቶች ቡና የጤና በረከቶች እንዳሉት ይመሰክራሉ

የቡና የጤና በረከቶች

በርካታ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ቡና በእርግጥ በሽታ የመከላከል ውጤት ሊኖረው ይችላል።

አንዳንድ ጥናቶች በቡና መጠጣት እና ህሙማን ለአንዳንድ የካንሰር ዓይነቶች ያላቸው ዝቅተኛ ተጋላጭነት ጋር ያለውን ግንኙነት ያሳያሉ።

ጉንተር በአውሮፓውያኑ 2017 በመላው አውሮፓ በ16 ዓመታት ውስጥ በግማሽ ሚሊዮን ሰዎች ላይ የቡና አወሳሰድ ልማድን የመረመረ የጥናት ውጤትን ይፋ አድርጓል።

በዚህም ጥናት ብዙ ቡና የጠጡ ሰዎች በልብ ህመም፣ በስትሮክ እና በካንሰር የመሞት ዕድላቸው ዝቅተኛ ሆኖ ተገኝቷል።

እነዚህ ግኝቶች በአሜሪካ እንዲሁም በዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) ውስጥ በቅርቡ የተደረጉ ጥናቶችን ጨምሮ በሌሎች የዓለማችን ክፍሎች ከተደረጉ ምርምር ውጤቶች ጋር የተጣጣሙ ናቸው።

ጉንተር በቀን እስከ አራት ሲኒ ቡና የሚጠጡ ሰዎች ምንም ከማይጠጡት ጋር ሲነፃፀሩ በበሽታ የመያዝ ዕድላቸው ያነሰ መሆኑን ማስተዋሉን ይናገራሉ።

የቡና ጥቅም ከዚህ በላይም ሊሄድ ይችላል።

በጉንተር ጥናት ውስጥ ቡና ጠጪዎች ቡና ከማይጠጡ ሰዎች የበለጠ አጫሽ እና ጤናማ ያልሆነ አመጋገብ የሚከተሉ ነበሩ።

ቡና ለልብ ህመም እና ለካንሰር ያለን ተጋላጭነትን ከቀነሰ፣ ጤናማ ያልሆኑ ባህሪ ተጽእኖዎችን ለመሻር፣ እኛ ከምናስበው በላይ ኃይል ሊኖረው እንደሚችል ይጠቁማል።

ካፌይን የሌለው ወይም ካፌይን ያለው ቡና ቢሆን ይህ እውነት ነው።

ካፌይኑ የወጣለት ቡና ልክ እንደ መደበኛ ቡና ተመሳሳይ መጠን ያለው በሽታ ተከላካይ ንጥረ ነገር አለው ሲል ጥናት አረጋግጧል።

ጉንተር በጥናታቸው ወቅት ካፌይን ያለው እና የሌለው ቡና በሚጠጡ ሰዎች ጤና መካከል ምንም ልዩነት አላስተዋሉም።

ይህም ከቡና ጋር ተያይዘው የሚመጡ የጤና በረከቶች ከካፌይን ውጪ በሆነ ምክንያት ነው ብሎ እንዲደመድም አድርጎታል።

ቡና አብዝተው የሚጠጡ ሰዎች ለደም ግፊት የመጋለጥ እድል ቢኖራቸውም ለልብ ሕመም ግን የመጋለጥ እድላቸውን አያሰፋውም።
የምስሉ መግለጫ,ቡና አብዝተው የሚጠጡ ሰዎች ለደም ግፊት የመጋለጥ እድል ቢኖራቸውም ለልብ ሕመም ግን የመጋለጥ እድላቸውን አያሰፋውም።

ቡና ጤናችን ላይ የሚያስከትለውን አሉታዊ ተጽዕኖ እንዴት ማወቅ ተሳነን?

ከበርካታ ቡና ጠጪዎች በተገኘ መረጃ ላይ የተመሠረተ ጥናት ቢደረግም በጤና ላይ የሚያስከትለውን አሉታዊ ተጽዕኖ በሚመለከት ምክንያት እና ውጤትን አስተሳስሮ የሚነግረን ግን ጥቂት ነው።

በብሪስቶል ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪ የሆኑት ፒተር ሮጀርስ ካፌይን በባህሪ፣ በስሜት፣ በንቃት እና በትኩረት ላይ የሚያሳድረውን ተጽዕኖ ሲያጠኑ፣ ቡና የሚጠጡ ከማይጠጡ ሰዎች የተሻለ የጤና ሁኔታ ሊኖራቸው ይችላል ይላሉ።

በጉንተር ጥናት ላይ እንደሚታየው ደግሞ ጤናማ ያልሆነ የአኗኗር ልምድ ቢኖራቸውም ይህ አይቀየርም።

ሮጀርስ “አንዳንድ ሰዎች ቡና ከበሽታ መከላከል ውጤት ሊኖረው እንደሚችል ጠቁመዋል፤ ይህ ግን በሚገባ ያልተፈተሸ በመሆኑ አከራካሪ ነው” ይላሉ።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ቡና አዘውትረው የሚጠጡ ሰዎች በተደጋጋሚ የደም ግፊት የሚገጥማቸው ሲሆን፣ ይህም ለልብ ህመም የመጋለጥ ዕድላቸውን ይጨምረዋል።

ነገር ግን ሮጀርስ ቡና በመጠጣት ከፍተኛ በደም ግፊት እና ከፍ ያለ የልብና የደም ሥር (cardiovascular) ዕክል መካከል ያለውን ቁርኝት የሚያሳይ ማስረጃ አልተገኘም ይላሉ።

አጠቃላይ መረጃን ከተጠቃሚ ሰብስቦ መረጃውን ከመተንተን በተሻለ ቡናን የሚመለከቱ በክሊኒክ የሚደረጉ ሙከራዎች ጥቅሞቹን እና ጉዳቶቹን በተሻለ ሁኔታ ሊያሳዩ ይችላሉ።

የተመራማሪዎች ቡድን ካፌይን ያለው ቡና መጠጣት በደም የስኳር መጠን ላይ የሚያስከትለውን ውጤት የተመለከቱበት አንድ ሙከራ አድርገዋል።

በእንግሊዝ ቤዝ ዩኒቨርስቲ የሥነ-ምግብ እና የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማዕከል የተካሄደው አነስተኛ ጥናት፣ ቡና ከተቆራረጠ የሌሊት እንቅልፍ በኋላ ለቁርስ የሚሰጠውን ምላሽ እንዴት እንደሚጎዳ አሳይቷል።

ቡና በቁርስ ምትክ ከቀረበ ጣፋጭ መጠጥ ተከትሎ የጠጡ ተሳታፊዎች ከቁርስ በፊት ቡና ካልጠጡት ጋር ሲነፃፀሩ በደማቸው ውስጥ ያለው የስኳር መጠን በ 50 በመቶ ከፍ ብሎ ተገኝቷል።

ተመራማሪዎቹ በላብራቶሪም ሆነ መረጃዎችን ሰብስቦ በመተንተን የሚደረጉ ጥናቶች ቡና በጤና ላይ ያለውን አሉታዊ ተጽዕኖ አንደማያሳዩ ያረጋግጣሉ።

ነፍሰ ጡር እናቶች ላይ በተደረገ ጥናት ካፌይን ያለባቸውን መጠጦች ሙሉ በሙሉ ማቋረጥ እንዳለባቸው ይመክራሉ
የምስሉ መግለጫ,ነፍሰ ጡር እናቶች ላይ በተደረገ ጥናት ካፌይን ያለባቸውን መጠጦች ሙሉ በሙሉ ማቋረጥ እንዳለባቸው ይመክራሉ

ቡና መጠጣት የጽንስ መቋረጥን ይጨምራል?

በእርግዝና ወቅት ካፌይን ያለበት ቡና መጠጣትን በተመለከተ የሚሰጠው ምክር የተምታታ ነው።

በአውሮፓውያኑ 2022 የተካሄደ አንድ ጥናት ቡናን ከእርግዝና በፊት፣ በእርግዝና ወቅት እና በፅንስ መቋረጥ መካከል ያለውን ግንኙነት አሳይቷል።

ከዚህ በተጨማሪም ሲጋራ ማጨስ ከካፌይን አወሳሰድ ጋር የተያያዘ በመሆኑ ለጽንስ መቋረጥ አስተዋጽኦ አለው።

የምግብ ጥናት ባለሙያ የሆኑት ኤስተር ማየርስ ቡና ላይ የተደረጉ 380 ጥናቶችን ከመረመሩ በኋላ ለአንድ አዋቂ ሰው በቀን አራት ስኒ ቡና፣ ለነፍሰጡር እናቶች ደግሞ ሦስት ስኒ አሉታዊ ውጤት የለውም ይላሉ።

ይሁን እንጂ ሌሎች ባለሙያዎች ነፍሰ ጡር እና ጡት የሚያጠቡ እናቶች በቀን ከአንድ ወይንም ከሁለት ሲኒ ቡና በላይ እንዳይጠጡ ይመክራሉ።

ከዚህ በተጨማሪ ቀደም ሲል የተደረጉ ጥናቶች ነፍሰ ጡር ሴቶች የፅንስ መቋረጥን፣ ዝቅተኛ ክብደት ያለው ጨቅላን ላለመውለድ፣ የሞተ ጨቅላ የመውለድ አደጋን ለመቀነስ ቡናን ሙሉ በሙሉ ማቋረጥ አለባቸው ሲሉ ይመክራሉ።

የምጣኔ ኃብት ባለሙያ የሆነችው እና ‘ኤክስፔክት ቤተር’ የተባለ መጽሐፍ ደራሲዋ ኤምሊ ኦስተር በእርግዝና ወቅት መደረግ ስላለባቸው ጥንቃቄዎች ታብራራለች።

እንደ ኤምሊ ማብራሪያ ለነፍሰጡር እናቶች ትልቁ አሳሳቢ ጉዳይ በተለይ በእርግዝናቸው የመጀመሪያዎቹ ሦስት ወራት የሚኖራቸው የካፌይን ፍጆታ ከፅንስ መቋረጥ ጋር የተቆራኘ የመሆን ዕድሉ የሰፋ ነው ትላለች።

አክላም ከካፌይን በተጨማሪ ሲጋራ ማጨስ ከፍተኛ ለሆነ የጽንስ መቋረጥ እንደሚያጋልጥ ታስቀምጣለች።

አክላም “. . . በእርግዝናቸው መጀመሪያ ወራት ላይ የማቅለሽለሽ ስሜት ያላቸው ሴቶች ጽንሱ የመቋረጥ ዕድሉ አነስተኛ ነው። ምክንያቱም ይህ የሚረብሽ ስሜት ያላቸው ነፍሰጡር ሴቶች ቡናንም አብረው ያስወግዳሉ። . . .ስለዚህ ብዙ የማቅለሽለሽ ስሜት ያላቸው እና ቡና የማይጠጡ እናቶች እርግዝናቸው የመቋረጥ ዕድሉ አነስተኛ ነው።”

በመጨረሻም በቀን ከሁለት እስከ አራት ሲኒ ቡና መጠጣት ትላለች ኦስተር፣ የጽንስ መቋረጥ አደጋን አይጨምርም።

ቡና በስኒ

የቡና ሱሰኝነት

ቡና ውስጥ የሚገኘው ካፌይን አነቃቂ ንጥረ ነገር ነው፤ ይህም ማለት በአእምሯችን ላይ ተጽዕኖ ያሳድራል።

አንዳንድ ሰዎች ቀኑን ሙሉ ካፌይን ያለው ቡና ሲጠጡ ሊውሉ ይችላሉ።

ሌሎች ደግሞ ከአንድ ስኒ በኋላ ይጨነቃሉ። ጥናቶች እንደሚያሳዩት በሰዎች ጂን (ዘረመል) መካከል ያለው ልዩነት ለካፌይን በሚሰጡት ምላሽ ላይ ተጽዕኖ ያሳድራል።

እርግጥ ነው እንደ ሰው ሊለያይ ይችላል፤ ነገር ግን ይህን መጠን ማለፍ የእንቅልፍ እጦት፣ ጭንቀት፣ የሆድ ህመም፣ የልብ ምት መጨመር እና የራስ ምታት ሊያስከትል ይችላል።

የአሜሪካው ምግብ እና መድኃኒት ቁጥጥር ባለሥልጣን ተመራማሪዎች ደግሞ 1200 ሚሊ ግራም ቡና (12 ሲኒ) በፍጥነት ከወሰድን ሰውነታችን ከቁጥጥራችን ውጪ ሊንቀጠቀጥ ይችላል ይላሉ።

ማየርስ “አንድ ሰው ለካፌይን በጎ ምላሽ የሚያሳይበት እና ሌላኛው ቶሎ የሚረበሽበት ምክንያትን ገና አልደረስንበትም” ይላሉ።

መደበኛ ጠጪዎች ወይንም ሱሰኞች ደግሞ አእምሯቸው ለካፌይን የሚሰጠው ምላሽ የተለየ ነው።

“አእምሯችን በየቀኑ ካፌይን መውሰድን ሲለማመድ፣ ሰውነታችንን ከካፌይን ጋር ለመኖር እና መደበኛ ሥራውን ለማስቀጠል የሚያደርገው አካላዊ ለውጦች አሉ” ይላል ሮጀርስ።

“ቡና መጠጣት የዕለት ተግባራችንን በብቃት ለመሥራት ባለን አቅም ላይ ምንም ዓይነት ፋይዳ አያመጣም” የሚለው ሮጀርስ የካፌይን ሱስ ሳይሆን ጥገኝነት መኖሩን ይናገራል።

ካፌይን የተባለው ንጥረ-ነገር ወደ ሰውነታችን ሲዘልቅ ምግብ በሚያልመው ሥርዓት በኩል አልፎ በአንጀት አድርጎ የደም ዝውውራችን ጋር ይደርሳል።

ነገር ግን ሥራውን መሥራት የሚጀምረው የነርቭ ሥርዓታችን ጋር ሲደርስ ነው።

ካፌይን፤ አዴኖሳይን ከተሰኘው ሰውነታችን የሚያመነጨው ያለ ንጥረ ጋር ተመሳሳይነት አለው። አዴኖሳይድ የነርቭ ሥርዓትን በማረጋጋት የልብ-ምት እንዲረጋጋ እና የመዝናናት መጠናችን ከፍ እንዲል የማድረግ አቅም አለው።

ካፌይን ከአዴኖሳይን ጋር ሲደባለቅ የልብ-ምታችን ይጨምራል፣ አእምሯችን ፈጣን ይሆናል፣ የረሃብ ስሜት ይጠፋ እና ንቁ ያደርገናል። ለዚህ ነው የትኩረት መጠናችን ከሌላው ጊዜ የላቀ የሚሆነው።

ካፌይን ‘ስሜትን’ (ሙድ) የመቀየር ኃይል አለው። ድካም ይቀንሳል፤ አካላዊ ብቃትን ከፍ ያደርጋል።

ባለሙያዎች የካፌይንን ጥቅም ከፍ ለማድረግ በመጠኑ መውሰድ እና ከሰዓት ከመጠጣት ይልቅ በነጋታው ጠዋት በመጠጣት የተሻለ ውጤት ማግኘት ይቻላል ይላሉ።