የቫግነር አርማ

ከ 4 ሰአት በፊት

የሩሲያው ቅጥረኛ ተዋጊ ቡድን ፣ቫግነር በማሊ ያለውን ‘ተልዕኮ አጠናቆ’ ከአገሪቱ ሊወጣ መሆኑን አስታወቀ።

ቫግነር በምዕራባዊቷ አፍሪካዊቷ አገር ማሊ ከአውሮፓውያኑ 2021 ጀምሮ ከአገሪቱ መከላከያ ሰራዊት ጋር በመጣመር ጽንፈኞችን ለመምታት እየሰራ ነበር።

ቫግነር “ከማሊ ሕዝብ ጎን በመሆን ሽብርተኝነትን ተዋግቷል፤ በዚህም ነዋሪዎችን ለዓመታት ሲያሸብሩ የነበሩ በሺዎች የሚቆጠሩ ታጣቂዎች እና አዛዦቻቸውን ገድያለሁ” ሲል በቴሌግራም ገጹ አስታውቋል።

ቫግነር ከአገሪቱ እንደሚወጣ ያስታወቀው የማሊ ወታደሮች ከአንድ ሳምንት ባነሰ ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ የከፋ ጥቃት ከደረሰባቸው በኋላ በአገሪቱ ማዕከል ከሚገኘው ትልቅ የጦር ሰፈር መውጣታቸውን የሚገልጹ ዘገባዎች እየወጡ ባለበት ወቅት ነው።

ማሊ ለአስርት ዓመታት ከእስላማዊ ታጣቂዎች ጋር ስትታገል ቆይታለች።

የአገሪቱ መንግሥት ይህንን የጸጥታ ችግር ለመቋቋም ተስኖታል የሚሉ ክሶች ከቀረቡ በኋላ ወታደራዊ ኃይሉ ከጥቂት ዓመት በፊት ስልጣኑን ተቆጣጥሯል።

የአገሪቱን መንግሥት ለማገዝ በመጀመሪያ ተሰማርቶ የነበረው የፈረንሳይ ጦር በአውሮፓውያኑ 2022 አገሪቱን ለቆ ወጥቷል። ከጥቂት ዓመታት በፊት ወታደሮች ሥልጣን የተቆጣጠሩባቸው ማሊ፣ ኒጀር እና ቡርኪናፋሶ ከቀድሞ ቅኝ ገዢያቸው ፈረንሳይ ጋር ያላቸውን ግንኙነት በማቋረጥ ከሩሲያ ጋር ቅርበት ፈጥረዋል።

ስልጣኑን በኃይል የተቆጣጠረው ወታደራዊ ኃይል አማጽያኑን ለመዋጋት ከሩሲያ ቅጥረኛ ቡድን ቫግነር አብሮ እየሰራ ይገኛል።

በምላሹም ታጣቂዎቹ ስትራጂካዊ ጠቀሜታ ያላቸውን የተፈጥሮ ሀብቶችን ያገኛሉ።

በቅርብ ሳምንታት ውስጥ በሳህል ግዛት በሚገኙ የጦር ሰፈሮች ላይ የጂሃዲስቶች ጥቃቶች እያገረሹ መምጣታቸው ተገልጿል።

ባለፈው ዕሁድ ከአልቃይዳ ጋር ግንኙነት ያለው ቡድን በቡሌስኪ ከተማ እና በወታደራዊ ካምፕ ላይ ከፍተኛ ጥቃት መፈጸሙን አስታውቋል።

በዚህም ጥቃት 30 ወታደሮች መገደላቸውን ሮይተርስ ምንጮችን ዋቢ አድርጎ ዘግቧል።

በማግስቱ ሰኞ ይኸው ጃማ ኑስራት አል ኢስላም ወኣል ሙስሊሚን የተሰኘው ቡድን በታሪካዊቷ የቲምቡክቱ ከተማ በሚገኘው ጦር ላይ ያነጣጠረ ጥቃት መፈጸሙን የገለጸ ሲሆን፤ ነዋሪዎች በበኩላቸው የተኩስ እና የፍንዳታ ድምጽ መስማታቸውን ገልጸዋል።

ታጣቂዎቹ በተጨማሪ በደቡብ ምስራቅ ሲካሶ ክልል ውስጥ በሚገኘው ማሁ መንደር የሚገኝ የጦር ሰራዊት ካምፕ ላይ ጥቃት ፈጽመው አምስት ሰዎችን ገድለዋል።

በሳህል ቀጠና እየጨመሩ የመጡ ጥቃቶች የሩሲያው ቅጥረኛ ተዋጊ ቡድን ቫግነር ታጣቂዎች ውጤታማ ናቸው ወይ የሚለው ላይ ጥርጣሬችን ፈጥሯል።

ቫግነር ከማሊ መውጣቱን ቢያስታውቅም፤ የሩስያ ኃይሎች አሁንም በአገሪቱ የጸጥታ ሁኔታ ላይ ንቁ ሚና እንደሚኖራቸው ተገልጿል።

የቅጥረኛው ተዋጊ ቡድን ተቀናቃኝ የሆኑት የአፍሪካ ኮርፕስ የሚባሉት የሩሲያ ወታደሮች በአህጉሪቱ ውስጥ የቫግነርን ሚና እንደሚወስዱ ሲነገር ቆይቷል።

ሩሲያ በምዕራብ እና በመካከለኛው አፍሪካ ወታደራዊ፣ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ተጽእኖዋ እየጨመረ ነው።

ቫግነር ማሊን ቢለቅም ዋና መስሪያ ቤቱ ከሚገኝበት የመካከለኛው አፍረካ ሪፐብሊክ ይወጣ እንደሆነ አልተገለጸም።