
ከ 8 ሰአት በፊት
የሳይንስ ሊቃውንት አመጋገባችንን ብንቀይር እና የሥጋ እና የወተት ተዋጽፆዎችን በዕፅዋት ምግቦች በመተካት የአየር ንብረት ለውጥን ለመዋጋት ይረዳል ሲሉ ቆይተዋል።
የዓለምን ሕዝብ የአመጋገብ ሥርዓትን መቀየር ግን ቀላል አይደለም።
የመጀመሪያው ምክንያት በአንዳንድ ቦታዎች የምግብ ምርጫዎች የተገደቡ መሆናቸ ነው። የምግብ ባህል፣ የምንበላው መጠን እና የምግብ አሠራርም ተፅዕኖ አላቸው።
ከሁሉም በላይ ደግሞ ማኅበራዊ ሚዲያ በምግብ እና በአየር ንብረት ለውጥ መካከል ስላለው ግንኙነት በሐሰተኛ እና በአሳሳች መረጃዎች ተሞልቷል። ዋና ዋናዎቹን ጉዳዮች እንደሚከተለው ቃኝተናቸዋል።
ጉዳይ 1፡ ሥጋ የአየር ንብረት ለውጥ አያመጣም
በአንድ በስፋት በታየ የኤክስ ልጥፍ “ቀይ ሥጋ የአየር ንብረት ለውጥ አያመጣም” ሲል በስህተት ሰፍሯል።
ኢንደስትሪዎች በአየር ንብረት ላይ የሚያደርጉትን ተጽዕኖ ተጠያቂነቱን ወደ እንስሰሳት ለማዞር የተደረገ “ውሸት” መሆኑን በቪዲዮው ላይ ተጠቁሟል።
ለአየር ንብረት ለውጥ ትልቁን ድርሻ የሚወስዱት እንደ ነዳጅ እና የድንጋይ ከሰል ያሉት ቢሆኑም ምግብ ለማምረት በሚደረገው ሂደት እንደካርቦን ዳይኦክሳይድ እና ሚቴን ያሉ የሙቀት አማቂ ጋዞችን ይፈጥራሉ።
ሳይንቲስቶች እንዲያውም በዓለም ላይ ከሚለቀቁት የሙቀት አማቂ ጋዞች ውስጥ አንድ ሦስተኛ የሚሆነው ከምግብ ሥርዓት ጋር ሊገናኝ እንደሚችል ይገምታሉ። ከእነዚህ ውስጥ ከግማሽ በላይ የሚሆኑት እንስሳትን መሠረት ያደረጉ ምግቦችን ከማምረት ጋር የተያያዙ ናቸው ይላሉ።
ነገር ግን ሁሉም ከእንስሳት የሚገኙ ምግቦች አንድ ዓይነት አይደሉም። በተለይም የበሬ እና የበግ ሥጋ በጣም ጉዳት አድራሽ መሆናቸው ታውቋል።
ለዚህ ምክንያት የሆው ደግሞ ከብቶች እና በጎች ሚቴን ወደ ከባቢ አየር ስለሚለቁ ነው። በተጨማሪም ሳር ይመገባሉ። ለሚመገቡት ሳር የሚሆን ቦታ ለማዘጋጀት ደግሞ ብዙ ጊዜ ዛፎችን እና ካርቦን የሚያከማቹ ደኖች ይቆረጣሉ።
“በዕፅዋት የበለፀጉ ምግቦች መመገብ” የልቀት መጠንን “በከፍተኛ ደረጃ እንደሚቀንስ” የአየር ንብረት ለውጥ በይነ መንግሥታት ጉባኤ ጠይቋል።
“ዕፅዋቶችን ብቻ መመገብ ለማይፈልጉ ወይም ለማይችሉ እንደ ዶሮ እርባታ፣ እንቁላል ወይም የአሳ እርባታ ያሉ ብዙ ልቀትን የሚቀንሱ አማራጮች አሉ” ሲሉ የኮንሴፕሲዮን ዩኒቨርሲቲ የሥርዓተ ምግብ እና የአየር ንብረት ተጽዕኖ ባለሙያ የሆኑት ዶክተር ማግዳሌና የንሰን ይናገራሉ።

ጉዳይ 2፡ ከዕፅዋት የሚገኝ ምግብ ጤናማ አይደለም
በሺህዎች የሚቀጠሩ ተመልካቾች ባገኘ የቲክ ቶክ ቪዲዮ ላይ አንድ ሥጋ መብላትን የሚደግፍ ሰው “ሰዎች ዕፅዋትን እንዲበሉ አልተፈጠሩም” በማለት በስህተት ተናግሯል።
“ተክሎች ሊገድሉህ ይችላሉ” እስከ ማለት ድረስ አትክልቶችን መመገብ በሰዎች ጤና ላይ ጉዳት ሊያደርስ እንደሚችል ጠቁሟል።
እነዚህ አመለካከቶች በብዙ የሕክምና ባለሙያዎች ድጋፍ የላቸውም።
የዓለም ጤና ድርጅት ጤናማ የአኗኗር ዘይቤ አካል አድርጎ “አነስተኛ ጨው፣ ስብ እና ስኳር ያለው በዕፅዋት ላይ የተመሠረተ” አመጋገብን ይመክራል።
ቀይ ሥጋን እና የተቀነባበሩ ሥጋዎችን (እንደ ቋሊማ ያሉትን) አለመመገብም የልብ ህመምን፣ ካንሰርን ወይም የስኳር በሽታን ለመከላከል ይረዳል ይላል።
“የዕፅዋት ምግቦች እና አነስተኛ የእንስሳት ምግቦች ለጤና ብቻ ሳይሆን ሌሎችም ጥቅሞች ይሰጣሉ” ብለዋል የአመጋገብ ኤክስፐርት የሆኑት ዶ/ር አፍተን ሃሎራን።
እነዚህ ምግቦችም አደጋ ሊኖራቸው ይችላል።
“የዕፅዋት ምግቦችን የሚወስዱ ግለሰቦች የምግብ አለመመጣጠን ሊያስከትል ስለሚችለው አደጋ ማወቅ አለባቸው” ብለዋል።
ሁሉም የዕፅዋት ምግቦች ተመሳሳይ ዓይነት የጤና ጥቅም ይሰጣሉ ማለት አይደለም። እንደ ሥጋ አማራጭ ተደርገው የሚቀርቡ አንዳንድ የዕፅዋት ምግቦች እጅግ በጣም የተቀነባበሩ ሊሆኑ ይችላሉ።
ይህ ማለት የጨው፣ የስብ እና የስኳር ይዘታቸው ብዙ ሊሆን ይችላል። እነዚህም ለልብ በሽታዎች እና ለሌሎችም የጤና ችግሮች ተጋላጭነትን እንደሚያሳድጉ ተረጋግጧል።

ጉዳይ 3፡ የዕፅዋት ምግቦች ለአየር ንብረት ችግር
“[እነሱ] ሥጋ መመገብ ለፕላኔታችን መጥፎ ነው ይላሉ” ከላይ ያለው የኤክስ ጽሑፍ።
“ነገር ግን ካሊፎርኒያ ውስጥ አንድ አልመንድ 12 ሊትር፣ ሙዝ 160 እና አንድ ኪሎ አቮካዶ ደግሞ 2 ሺህ ሊትር ውሃ እንደሚፈልግ አይናገሩም።”
እነዚህ ዓይነት ጽሑፎች የአየር ንብረትን በሚያውቁ ሰዎች የሚመረጡ ምግቦች ከሥጋ ይልቅ ለአካባቢ የከፉ እንደሆኑ ይጠቁማሉ። ይህ ግን ላይሆን ይችላል።
አቮካዶን እንደ ምሳሌ እንውሰድ።
በኔዘርላንድ የሚገኘው አይኤችኤ ዴልፍት የውሃ ትምህርት ኢንስቲትዩት ባደረገው ጥናት መሠረት አንድ ኪሎ አቮካዶን ለማምረት ወደ 2 ሺህ ሊትር ውሃ (በአማካይ) እንደሚያስፈልግ ገልጿል።
በየትኛውም መለኪያ ቢታይ ይህ ብዙ ውሃ የሚባል ነው። እንደ ፔሩ እና ቺሊ ባሉ አገራት የአቮካዶ ምርት በውሃ ሃብት ላይ ከፍተኛ ጫና እንደፈጥር ይታወቃል።
አንድ ኪሎ ግራም የበሬ ሥጋ ለማምረት ግን ከዚህ የበለጠ ውሃ ሊፈልግ ይችላል። በአማካይ ወደ 15 ሺህ 500 ሊትር ገደማ ውሃ እንደሚያስፈልግ ዋተር ፉትፕሪንት ኔትወርክ አስታውቋል።
ከፍተኛ መጠን ያለው የዓለም አቮካዶ የሚመረተው ከላቲን አሜሪካ ነው። ይህ ማለት ደግሞ ተመጋቢዎች ጋር ለመድረስ ረዥም ርቀት መጓዝ አለባቸው ማለት ነው። የሚጠቀሟቸው የመጓጓዣ ዘዴዎች ደግሞ እንደ ነዳጅ ያሉትን ነው።
ይህም ለአየር ንብረት የሚሟገቱ ሸማቾች በአገር ውስጥ የማይበቅሉ ምግቦችን በመምረጣቸው “ግብዝ” ተብለው በአንዳንድ የማኅበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች አንዲፈጠሩ አድርጓል።
ነገር ግን በየቀኑ ከፍተኛ መጠን ያለው የበሬ ሥጋ ወደ ዓለም ይሠራጫል። በዓመት በሺህዎች የሚቆጠር ቶን ሥጋ ወደ ቻይና የምትልከውን ብራዚልን መመልከት በቂ ነው።
ለአብዛኞቹ የምግብ ምርቶች መጓጓዣ ከ10 በመቶ ያነሰ የሙቀት አማቂ ጋዝ ልቀት እንደሚወጣ ልብ ሊባል የሚገባው ጉዳይ ነው።
“ከተመረተበት አገር ይልቅ የምንበላው ነገር የበለጠ አስፈላጊ ጉዳይ ነው” በማለት በዘላቂ የምግብ ሂደት ላይ ባለሙያ የሆኑት ዳንኤል ብሉም ተናግረዋል።

ጉዳይ 4፡ “የልሂቃን” ሴራ
የአመጋገብ ለውጦችን ከሴራ ትንታኔዎች ጋር በተሳሳተ መንገድ የሚያገናኙ ሃሳቦችም በተለያዩ ቋንቋዎች ይገኛሉ።
ከላይ ያለው በሩሲያ ቋንቋ የተጻፈ የኤክስ መልዕክት “ልሂቃን” ሕዝቡን “ትኋኖችን እንዲበሉ ለማሳመን እየሞከሩ ነው” ይላል። “የአመጋገብ ሥርዓታችንን ለመቀየር የሚደረገው ግፊት ከምን የመነጨ ነው?” ሲልም ያክላል።
እንደዚህ ያሉ ጽሑፎች ሀብታም እና ኃያላን ግለሰቦች በምሥጢር የሰዎችን ነፃነት ለመገደብ እያሴሩ ነው የሚለውን ታዋቂ የሴራ ትንተና ያነሳል።
ሰዎች ትኋኖችን እና ነፍሳትን እንዲበሉ በማስገደድ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም የሚረዱ ምግቦችን መመገብ እንዲጀምሩ ማድረግ እንደ መጥፎ ዕቅዳቸው ተደርጎ ይታያል።
እነዚህን ሃሳቦች የሚደግፍ ምንም ማስረጃ የለም። እንደ እውነቱ ከሆነ እንደ ታይላንድ፣ ሜክሲኮ ወይም ጋና ባሉ አገራት ውስጥ ነፍሳት ለረጅም ጊዜ ለሰዎች ምግብነት ይውሉ ነበር።
አንዳንድ ዝቅተኛ ገቢ ባላቸው አገራት የተመጣጠነ ምግብ በማይኖርበት ጊዜ ሥጋ እና የወተት ተዋጽፆዎች የፕሮቲን እና ማይክሮ ኤለመንቶች ቁልፍ ምንጮች ሆነው ቆይተዋል። በሌሎች ዘንድ ደግሞ ሥጋን መመገብ ለሃብታሞች ብቻ የተተው የቅንጦት ምግብ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል።
በዚህ ምክንያት ፖለቲከኞች፣ መንግሥታት ወይም ዓለም አቀፍ ተቋማት ሰዎች አመጋገባቸውን እንዲቀይሩ ጥሪ ሲያቀርቡ አንዳንዶች ጥሪዎቹን ኢፍትሃዊ፣ ለልሂቃን ሲባል የተደረገ ወይም የአዲስ ቅኝ ግዛት ዘዴ እንደሆኑ ሊሰማቸው ይችላል።
“ጥሪውን ከዘላቂነት እና ከሥነ ምግባራዊ አተያይ አንጻር መረዳት የሚቻል ቢሆንም አሁን ባለው ዓውድ ሙሉ በሙሉ ሊሠራ የሚችል አይደለም” ይላሉ በዛምቢያ የምግብ ሥርዓት ባለሙያ የሆኑት ሪቻርድ ካቹንጉ።
ጥናቶች እንደሚያሳዩት የሥጋ ፍጆታን በመገደብ ሊደርስ የሚችለውን ኢኮኖሚያዊ ጉዳት በድሃ አገራት ላይ ያልተመጣጠነ ሊሆን ይችላል። ምክንያቱም እርሻ እና የእንስሳት እርባታ አሁንም ወሳኝ የገቢ ምንጭ ሊሆኑ ስለሚችሉ።
በኬንያ ለትርፍ ያልተቋቋመው የሌክ ሪጅን ፉድ ሲስተምስ ኔትዎርክ ባልደረባ የሆኑት ኢቫንስ ሙስዋሂሊ ላዴማ በበኩላቸው “መጀመሪያ ከፍተኛ እና መካከለኛ ገቢ ባላቸው አገሮች ውስጥ የሥጋ ፍጆታን በከፍተኛ ሁኔታ መቀነስ ያስፈልጋል” ብለዋል።
በእነዚያ አገራት ውስጥ የአመጋገብ ለውጥ በአብዛኛው የግል ምርጫ ጉዳይ ሆኖ ቆይቷል። እስካሁን ድረስ በአየር ንብረት ምክንያት ሥጋን ወይም የወተት ተዋጽፆዎችን መጠቀምን የሚከለክል መንግሥት የለም።
ነገር ግን “የምንበላው ነገር መለወጥ አለበት” ብለዋል ዶክተር ሃሎራን።