
ከ 7 ሰአት በፊት
በኮሎምቢያ ዋና ከተማ ቦጎታ የምርጫ ቅስቀሳ ላይ የነበሩት የኮሎምቢያ ፕሬዚዳንታዊ ዕጩ ሦስት ጊዜ በተተኮሰባቸው ጥይት መመታታቸው ተገለፀ።
ፕሬዝደንታዊው ዕጩ ሁለት ጊዜ ጭንቅላቱ ላይ መመታታቸው ተነግሯል።
የ39 ዓመቱ ሚጌል ኡሪቤ ቱርባይ ጥቃት የደረሰባቸው ቅዳሜ ዕለት በአንድ መናፈሻ ውስጥ ለተሰበሰቡ ጥቂት ሰዎች ንግግር ሲያደርጉ ነው።
ፖሊስ በቦታው የ15 ዓመት ተጠርጣሪ በቁጥጥር ስር ማዋሉን የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።
ባለቤታቸው ማሪያ ክላውዲያ ታራዞና ሕዝቡን ፕሬዝዳንታዊው ዕጩ ሕይወታቸው እንዲተርፍ እንዲፀልይላቸው ተማጽነዋል።
“ሚጌል በአሁኑ ጊዜ በሕይወት ለመቆየት ጣር ላይ ነው። የሚያክሙት ዶክተሮችን እግዚአብሔር እንዲያግዛቸው እንጠይቀው” ብለዋል።
ፓርቲያቸው የፕሬዝዳንታዊው ዕጩ ላይ የደረሰውን ጥቃት አውግዞ “የፖለቲካ መሪን ሕይወት … ዲሞክራሲ እና በኮሎምቢያ ውስጥ ያለውን ነፃነት አደጋ ላይ ይጥላል” ብሏል።
በስልክ ተቀርጾ በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ የተጋራው ተንቀሳቃሽ ምስል ንግግር በሚያደርጉበት መካከል የተተኮሰባቸው ጥይት ጭንቅላታቸውን ሲመታ እና በዙርያቸው የተሰባሰቡ ተደናግጠው ሲሮጡ ያሳያል።
የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች በጉልበታቸው ላይ እና ሁለት ጊዜ ጭንቅላታቸው ላይ በጥይት መመታታቸውን ለኤኤፍፒ የዜና ወኪል ተናግረዋል።
የፕሬዝዳንታዊ ዕጩ ዕጣ ፈንታ ያሳሰባቸው ደጋፊዎቻቸው በሆስፒታሉ ዙርያ የተሰባሰቡ ሲሆን ለተሻለ ሕክምና ወደ ሳንቴ ፌ ክሊኒክ በሂሊኮፕተር ተወስደዋል።
ፕሬዚደንት ጉስታቮ ፔትሮ ጥቃቱን “በግለሰብ ላይ ብቻ ሳይሆን በዲሞክራሲ ላይ የተፈፀመ የኃይል እርምጃ” ሲሉ አጥብቀው እንደሚያወግዙ ገልጸዋል።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮም ጥቃቱን “ዴሞክራሲ ላይ የተቃጣ ቀጥተኛ አደጋ” ሲሉ አውግዘዋል።
ኡሪቤ በጥቅምት ወር ለሚካሄደው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ዕጩ እንደሚሆኑ አስታውቀው ነበር።
በኮሎምቢያ ፖለቲካ ውስጥ ተሳትፎ ካለው ቤተሰብ የተገኙት ኡሪብ፣ ከአገሪቱ ሊበራል ፓርቲ ጋር ግንኙነት አላቸው። አባታቸው ነጋዴ እና የንግድ ኅብረቱ መሪ ናቸው።
እናታቸው ጋዜጠኛ የነበሩ ሲሆን በ1991 በፓብሎ ኤስኮባር ይመራ በነበረው የሜዴሊን የአደንዛዥ እጽ ቡድን ታግተው ከተወሰዱ በኋላ ለማስለቀቅ በተደረገ ጥረት ወቅት ተገድለዋል።