ከዓይነ ምድር የተሰራ እንክብል

ከ 6 ሰአት በፊት

የዩናይትድ ኪንግደም ሐኪሞች በበረዶ የደረቀ የሰው ዓይነ ምድርን የያዙ ‘ፑ ፒልስ’ (poo pills) የተባለ እንክብልን በመጠቀም መድኃኒትን የሚቋቋሙ አደገኛ የባክቴሪያ ኢንፌክሽኖችን ለማከም እየሞከሩ ነው።

ለመድኃኒትነት የሚውሉት የዓይነ ምድር ናሙናዎች የሚወሰዱት ከጤናማ ለጋሾች ሲሆን፣ በጤማ ባክቴሪያዎችን የያዙ ናቸው ተብሏል።

የመጀመሪያ ደረጃ ጥናት ውጤቶች እንደሚያሳዩት መድኃኒትን የሚቋቋሙ አደገኛ ባክቴሪያዎች ከአንጀት ውስጥ ታጥበው በመውጣት በጤናማ የአንጀት ባክቴሪያ ይተካሉ።

ይህ መድኃኒት በየዓመቱ አንድ ሚሊዮን ሰዎችን ይገድላሉ ተብለው የሚገመቱትን ፀረ ባክቴሪያዎችን የሚቋቋሙ ኢንፌክሽኖችን ለማከም ጥቅም ላይ የዋለ አዲስ ዘዴ ነው።

ትኩረቱ በሰዎች ሆድ ውስጥ “ትልቁ ፀረ ባክቴሪያን የመቋቋም ክምችት በያዘው አንጀት ላይ ነው” ብለዋል።

በእንክብሎቹ ላይ በጋይ እና ሴንት ቶማስ ሆስፒታሎች ሙከራ መደረጉን ዶ / ር ብሌየር ሜሪክ ተናግረዋል።

መድኃኒት የሚቋቋሙ አደገኛ ባክቴሪያዎች መኖሪያቸው ከሆነው አንጀት ውስጥ በመውጣት፣ በሰውነት ውስጥ ባሉ የተለያዩ ክፍሎች፣ እንደ የሽንት ቱቦ እና የደም ዝውውር ኢንፌክሽኖች ያሉ የጤና እክልን ይፈጥራሉ።

“ስለዚህ ‘ከአንጀት ውስጥ ልናስወግዳቸው እንችላለን?’ የሚለው ጥያቄ ላይ ብዙ ፍላጎት አለ” ይላሉ ዶክተር ሜሪክ።

ከዓይነ ምድር የተሠሩ የመድኃኒት እንክብሎች እንደሚታሰቡት ሩቅ አይደሉም።

የዓይነ ምድር ንቅለ ተከላዎች፣ እንዲሁም የዓይነ ምድር ቅየራ (trans-poo-tion ) በመባልም የሚታወቀው የሕክምና ዘዴ በክሎስትሪዲየም ባክቴሪያ ምክንያት የሚመጣን ከባድ ተቅማጥ ለማከም ከዚህ ቀደም ፍቃድ አግኝቷል።

አዲሱ ጥናት ያተኮረው ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ መድኃኒት በተላመደ ባክቴሪያ የተጠቃ ኢንፌክሽን ባጋጠማቸው ታካሚዎች ላይ ነው።

ታካሚዎቹ ለዓይነ ምድር ባንክ ካበረከቱት ሰገራ የተሠሩ እንክብሎች ተሰጥቷቸዋል።

እያንዳንዱ የሰገራ ናሙና ምንም ዓይነት ጎጂ ባክቴሪያዎች አለመያዛቸውን ለማረጋገጥ ይሞከራል።

ያልተፈጨ ምግብ ተወግዶ ከደረቀ እና በዱቄት መልኩ ከተዘጋጀ በኋላ ማቀዝቀዣ ውስጥ ይቀመጣል።

ይህ ምንም ጉዳት ሳይደርስበት በሆድ ውስጥ አልፎ ወደ አንጀት ሊደርስ እና ከሰገራ የተዘጋጀውን ዱቄት በመልቀቅ አስፈላጊውን ሕክምና መስጠት በሚችል ክኒን ውስጥ ይቀመጣል።

ለትልቅ ጥናት መሠረት ለመጣል በለንደን ጋይስ እና ሴንት ቶማስ ሆስፒታሎች በ41 ታካሚዎች ላይ ሙከራ ተደርጓል።

ከዓይነ ምድር የተዘጋጀውን እንክብል በወሰዱ ህሙማን ሰገራ ውስጥ ከወር በኋላ በተደረገ ምርመራ የተሰጣቸው ጤናማ ባክቴሪያ ተገኝቷል።

ዶ/ር ሜሪክ እንዳሉት እንክብሎቹ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣውን መድኃኒት የሚቋቋሙ ባክቴሪያዎችን ችግር ለመግታት የሚረዱ ሲሆን፣ የተሰጣቸው ጤናማ ባክቴሪያዎች በአንጀት ሽፋን ላይ ባለው ምግብ እና ቦታ ላይ መድኃኒትን ከሚቋቋሙት ጋር ሲፎካከሩ ከሰውነት እንዲወጡ ወይም “ችግር ወደማያመጣ ደረጃ ዝቅ እንዲሉ” ለማድረግ እንደሚያስችል ተናግረዋል።

ጥናቱ እንደሚያመለክተው ከሕክምናው በኋላ የአንጀት ውስጥ ባክቴሪያዎች ስብስብ የበለጠ የተለያየ ይሆናሉ። ይህ የጥሩ ጤንነት ምልክት ሲሆን “ወረራን መቋቋምን እያበረታታ ሊሆን ይችላል” ስለዚህ ለአዳዲስ ባክቴሪያዎች ወደ ሰው አንጀት ዘልቆ መግባት በጣም ከባድ ያደርገዋል።

“በጣም የሚያስደስት ነው። ከ20 ዓመታት በፊት ጀምሮ ሁሉም ባክቴሪያዎች እና ቫይረሶች የሰውን ጤና ይጎዳሉ ተብሎ ከሚታሰበበት ዘመን የራቀ እውነተኛ ለውጥ አለ፤ አሁን ለአጠቃላይ ጤናችን ሙሉ በሙሉ አስፈላጊ መሆናቸውን በምንረዳበት ደረጃ ላይ ነን” ብለዋል ዶ/ር ሜሪክ።

በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ ሳይንቲስቶች ሰውነታችን የሚያገኛቸውን ከተወለድን በኋላ ባሉት ጥቂት ሰዓታት ውስጥ ጥሩ ባክቴሪያዎች አሳይተዋል ።

ይህም ጨቅላ ሕጻናት በሳንባ ኢንፌክሽን ወደ ሆስፒታል የመግባት እድላቸውን በግማሽ ይቀንሳል።