ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ
የምስሉ መግለጫ,ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ

ከ 7 ሰአት በፊት

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የአገሪቱ የመብት ጥበቃ ተቋም የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ባለፉት ዓመታት የተዛባ ሪፖርት ሲያወጣ ነበር ሲሉ ወቀሱ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ጋር ባካሄዱት ቃለ ምልልስ ላይ ከዚህ በፊት በመንግሥታቸው ባልተገለጸ ሁኔታ ኢሰመኮ ባለፉት ሦስት እና አራት ዓመታት “በተዛባ መንገድ” በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ ሪፖርት ሲያወጣ ነበር ሲሉ ተደምጠዋል።

በአራት ተከታታይ ክፍሎች በመንግሥት እና ለገዢው ፓርቲ ቅርብ በሆኑ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች በተመሳሳይ ሰዓት ሲተላለፍ በቆየው የጠቅላይ ሚኒስትሩ ቃለ ምልልስ የመጨረሻ ክፍል ላይ የኮሚሽኑን “የተዛባ” ያሉትን ሪፖርት መንግሥታቸው “በዝምታ ያለፈው” ለተቋም ግንባታ ሲል መሆኑን ተናግረዋል።

መንግሥት ለሰብዓዊ መብት “ከፍተኛ ኮሚትመንት [ቁርጠኝነት] አለው” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኮሚሽኑ “እዚችው አካባቢ ተቀምጦ [አዲስ አበባ] ሲያወጣ የነበረው ሪፖርት እያደመጠ ዝም የሚል መንግሥት መፍጠር መቻላችን ትልቅ እመርታ ነው” ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ መንግሥታቸው ለነጻ ተቋማት የከፈለውን “ዋጋ” ሲናገሩ “እንኳን ውሸት፣ እንኳን ቅጥፈት እንኳን ያልተስተካከለ ዳታ፣ የተስተካከለስ ቢሆን መንግሥት ሳያውቀው መንግሥትን መክሰስ እኮ [ከዚህ በፊት] አይቻልም” ሲሉ ተናግረዋል።

ነገር ግን ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን በየትኞቹ ጉዳዮች የተሳሳተ መረጃ ተጠቅሞ ሪፖርት እንዳወጣ ግን ያሉት የለም።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለውም “እኛ ነጻ ሆነው ይሥሩ ስንል የጠለፏቸው ቢሆንም ማለት ነው” ሲሉ በተቋሙ ውስጥ ሌሎች እጃቸውን አስገብተው እንደነበርም በደፈናው ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በኢትዮጵያ መንግሥት የተቋቋመ የሰብዓዊ መብት ድርጅት ሲሆን፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ወደ ሥልጣን መምጣታቸውን ተከትሎ በነጻነት እንዲሠራ መልሶ መዋቀሩ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ቀደም ሲል ከነበረው አሠራሩ በተለየ መልኩ የዜጎች መብት እንዲከበር በተደጋጋሚ ከመጠየቁ ባሻገር ለሰብዓዊ መብት ጥሰቶች መንግሥትን እና ተቋማቱን ተጠያቂ የሚያደርጉ ዝርዝር ሪፖርቶችን ሲያወጣ ቆይቷል።

በሰሜን ኢትዮጵያ ለሁለት ዓመታት በተካሄደው የእርስ በርስ ጦርነት ወቅት የተፈጸሙ ከባድ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን በተመለከተም ኮሚሽኑ ከተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብቶች ተቋም ጋር በመሆን ምርመራ አድርጎ ሰፊ ሪፖርት ማውጣቱ ይታወቃል።

ኢሰመኮ ምንም እንኳን መንግሥታዊ ተቋም ቢሆንም ብዙ ጊዜ የሚያወጣቸው ሪፖርቶች በመንግሥት መገናኛ ብዙኃን የማይዘገቡ ሲሆን፣ አንዳንድ ጊዜም ከፌደራል መንግሥት እና ከክልል ባለሥልጣናት በሪፖርቶቹ ላይ ጠንከር ያለ ትችት ሲቀርብበት ቆይቷል።

ኮሚሽኑ ከሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ጋር በተያያዘ የመብት ጥሰቶች፣ በሰብአዊነት ላይ የተፈጸሙ ወንጀሎች እና የጦርነት ወንጀሎችን በተመለከተ ሪፖርቶች ሲያወጣ ነበር።

ከዚያም በኋላ በአማራ እና በኦሮሚያ ክልሎች ከሚካሄዱ የትጥቅ ግጭቶች ጋር በተያያዘ በመንግሥት ኃይሎች እና በታጣቂዎች የሚፈጸሙ ጥቃቶች እና የመብት ጥሰቶችን በተመለከተ የመንግሥት አካላትን ያላስደሰቱ ሪፖርቶችን ሲያወጣ ቆይቷል።

በተጨማሪም የፀጥታ ኃይሎች እና ሌሎች የመንግሥት መዋቅሮች በሰላማዊ ዜጎች ላይ ይፈጽሟቸዋል የተባሉ የመብት ጥሰቶችን የሚመለከቱ ዝርዝር ሪፖርቶችን ከማውጣት ባሻገር ሕጋዊ እና የማስተካከያ እርምጃዎች እንዲወሰዱ ሲጠይቅ ይታወቃል።

በተለያዩ ጊዜያት በአገሪቱ ውስጥ የተፈጸሙ የመብት ጥሰቶችን በሚመለከት ከኢሰመኮ ባሻገር ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተቋማትም ተመሳሳይ ሪፖርቶችን ማውጣታቸው ይታወቃል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባለፉት ጥቂት ዓመታት የተዛባ ሪፖርት ሲያወጣ ነበር ያሉትን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽንን በኮሚሽነርነት ሲመሩ የቆዩት በራሳቸው የተሾሙት ታዋቂው የመብቶች ባለሙያ ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር) ነበሩ።

በዓለም አቀፉ የሰብአዊ መብቶች ተቆርቋሪው ድርጅት ሂዩማን ራይትስ ዋች የአፍሪካ ክፍል ዋና ዳይሬክተር ሆነው ሲሠሩ የነበረ ሲሆን፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ ነበር የኢሰመኮ ኮሚሽነር ሆነው የተሾሙት።

ዳንኤል (ዶ/ር) ለአምስት ዓመታት የቆዩበትን የኮሚሽነርነት የኃላፊነት ጊዜያቸውን ባለፈው ዓመት ማብቂያ ላይ አጠናቀው ሲሰናበቱ፣ የቀድሞው የመንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣን እና የሕግ ባለሙያው አቶ ብርሃኑ አዴሎ በዚህ ዓመት የኮሚሽነርነቱን ቦታ መረከባቸው ይታወቃል።