
ከ 8 ሰአት በፊት
የአሜሪካው ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ በሎስ አንጄለስ ለተቃውሞ የወጡ ሰነድ አልባ ስደተኞች የፈጠሩትን አለመረጋጋት ለመቆጣጣር 2000 ወታደሮችን አሰማሩ።
ትራምፕ ስደተኞችን ከአሜሪካ እንዲያባርሩ በዋናነት የሚደግፉት ቶም ሆርማን ቅዳሜ ዕለት ለፎክስ ኒውስ “ሎስ አንጀለስን ደህንንቷ የተጠበቀች እናደርጋታለን” ብለዋል።
ቅዳሜ ዕለት በሎስ አንጀለስ ከፍተኛ የደቡብ አሜሪካ ዜጎች በሚኖሩባቸው አካባቢዎች ለሁለተኛ ጊዜ ከፍተኛ ተቃውሞ ተቀስቅሷል።
ተቃውሞ ሠልፈኞቹ ከፌደራል የስደተኞች እና የጉሙሩክ ፖሊሶች ጋር ተጋጭተዋል።
በፓራማውንት ዲስትሪክት ተቃውሞ ሠልፈኞቹን ለመበተን አስለቃሽ ጋዝ እና ዱላ ጥቅም ላይ ውሏል።
በዚህ ሳምንት ብቻ ሰነድ አልባ ስደተኞችን ከግዛቲቱ ለማስወጣት በተወሰደ እርምጃ 118 ሰዎች በቁጥጥር ስር ውለዋል።
የካሊፎርኒያ ግዛት አስተዳዳሪ ጋቪን ኒውሶም የፖሊስን እርምጃ “ጨካኝ” ሲሉ አውግዘውታል።
ኒውሶም ቅዳሜ ዕለት ትራምፕን በስልክ ለ40 ደቂቃ ያህል ማነጋገራቸውን የገዥው ቃል አቀባይ በአሜሪካ የቢቢሲ ሚዲያ አጋር ለሆነው ለሲቢኤስ ኒውስ ተናግረዋል።
ሁለቱ ባለስልጣናት በምን ጉዳይ ላይ እንደተወያዩ ይፋ አልሆነም።
በአሁኑ ወቅት ፓራማውንት በጣም የተረጋጋ ቢሆንም ነገር ግን በተቃዋሚዎች እና በሕግ አስከባሪዎች መካከል ግጭቶች ቀጥለዋል።
የሎስአንጀለስ ካውንቲ ፖሊስ አባላት ተቃዋሚዎችን ለማባረር በየጥቂት ደቂቃዎቹ አስለቃሽ ጭስ ይተኩሱ ነበር።
በአካባቢው የሚኖሩ እና ተቃዋሚዎች በአካባቢው የንግድ ሱቆች ውስጥ ለመውጣት በመፍራት ዘግተው የተቀመጡ ስደተኞች እንዳሉ ይናገራሉ።
የፓራማውንት ነዋሪ ከ80 በመቶ በላይ የሂስፓኒክ ተወላጆች ናቸው።
ዋይት ሐውስ ባወጣው ጋዜጣዊ መግለጫ “ሰሞኑን አመፀኛ ቡድኖች በሎስ አንጀለስ፣ ካሊፎርኒያ ሰነድ አልባ ስደተኞችን በቁጥጥር ስር ለማዋል የተንቀሳቀሱ የፌደራል የጸጥታ ሠራተኞች እና የፌደራል ሕግ አስከባሪዎች ላይ ጥቃት ሰንዝረዋል።
“ይህ እርምጃ ሕገወጥ ወንጀለኞችን ወደ ዩናይትድ ስቴትስ የሚያደርጉትን ወረራ ለማስቆም እና ለመቀልበስ ወሳኝ ነው። በዚህ ብጥብጥ ወቅት የካሊፎርኒያ ደካማ የዲሞክራት መሪዎች ዜጎቻቸውን የመጠበቅ ኃላፊነታቸውን ሙሉ በሙሉ ትተዋል።ለዚህም ነው ፕሬዝዳንት ትራምፕ እየተባባሰ የመጣውን ሕገ ወጥነት ለመቆጣጣር 2,000 የጸጥታ ኃይሎችን ለማሰማራት ትዕዛዝ የፈረሙት።”
ሆመን በሎስ አንጀለስ የፀጥታ ኃይሎች የሚሰሩትን ለመከታተል በአካል ተገኝተው ሲናገሩ “አሁን ይህንን በምናገርበት ወቅት ተጨማሪ ኃይል እየመጣ ነው።ዛሬ ማታ የጸጥታ ኃይሎች ይመጣሉ። ስራችንን መስራታችንን እንቀጥላለን ።”
በግል ንብረት ላይ ለሚደርስ ማንኛውንም ጥቃት ወይም ጥፋት “ምንም ትዕግስት የለንም” ሲሉ አስጠንቅቀዋል።
የኤፍቢአይ ምክትል ዳይሬክተር ዳን ቦንጊኖ በኤክስ ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት ጽሑፍ እንዲሁ ተቃዋሚዎችን “እናንተ ትርምስ ትፈጥራላችሁ፣ እኛ ደግሞ ለእጃችሁን ካቴና እናመጣለን። ሕግ እና ስርዓት ይሰፍናል” ሲሉ አስጠንቅቀዋል።
“ዘመቻውን ያደናቀፉ” በርካታ ግለሰቦች መታሰራቸውንም ገልጸዋል።
የመከላከያ ሚኒስቴሩ ፔት ሄግስ በኤክስ ገጻቸው ላይ መሥርያ ቤታቸው “በሎስ አንጀለስ የሚገኘውን የፌዴራል ሕግ አስከባሪ አካላትን ለመደገፍ የብሔራዊ ጥበቃን በፍጥነት አሰማርቷል።”
አክለውም “እናም አለመረጋጋቱ ከቀጠለ በካምፕ ፔንድልተን የሚገኙ የባህር ኃይሎችም ይንቀሳቀሳሉ። በከፍተኛ ተጠንቀቅ ላይ ናቸው” ብለዋል።
የሎስ አንጀለስ አስተዳዳሪ ኒውሶም አርብ ዕለት በሰጡት መግለጫ “በካሊፎርኒያ በዘፈቀደ የእስር ኮታ ለማሟላት የቀጠለው የፌደራል ኃይሎች ትርምስ ግድየለሽ መሆን ብቻ ሳይሆን ጨካኝም ነው” ብለዋል።
“የዶናልድ ትራምፕ ቀውስ እምነትን እየሸረሸረ፣ ቤተሰብን እያፈራረሰ እና የአሜሪካን ኢኮኖሚ የሚደግፉትን ሠራተኞችና ኢንዱስትሪዎች እያዳከመ ነው።”
የሎስ አንጀለስ ከንቲባ ካረን ባስ ቀደም ሲል ሰነድ አልባ ሰዎችን በቁጥጥር ስር የሚያውሉ የጸጥታ አባላት በአሜሪካ ሁለተኛ ትልቅ ከተማ ውስጥ “ሽብር እየዘሩ ነው” ሲል ከስሰዋል።
የኤፍቢአይ እና የአገር ውስጥ ደህንነት ኃላፊዎች የከንቲባው አስተያየት የፌደራል ወኪሎችን አደጋ ላይ የጣለ ነው ብለዋል።
የካሊፎርኒያ አስተዳዳሪ የፌደራል የጸጥታ አካላት መሰማራታቸውን “የካሊፎርኒያ ብሔራዊ ዘብ ስራን በመውሰድ 2000 ወታደሮች ማሰማራት ሆን ተብሎ ጠብ አጫሪነት ነው” ካሉ በኋላ “ውጥረትን ያባብሳል” ሲሉ ተናግረዋል።
ኒውሶም በበኩላቸው “የሎስአንጀለስ ባለስልጣናት የሕግ አስከባሪ አካላት እርዳታ በጠየቁበት አፍታ ማግኘት ይችላሉ” ብለዋል።
ትራምፕ በትሩዝ የማኅበራዊ ሚዲያቸው ላይ የሎስ አንጀለስ አስተዳዳሪን እና ባስን ስራቸውን መስራት ካልቻሉ “ተቃዋሚ ሠልፈኞች እና ዘራፊዎቹን መፍትሄ መስጠት በሚኖርብን መንገድ የፌደራል መንግሥት ገብቶ ችግሩን ይፈታዋል” ብለዋል።