
ከ 7 ሰአት በፊት
በደቡባዊ ጋዛ በሚገኘው የእርዳታ ማከፋፈያ ማዕከል አቅራቢያ የእስራኤል ወታደሮች በከፈቱት ስድስት ፍልስጤማውያን ሲገደሉ በርካቶች መቁሰላቸውን በሃማስ የሚመራው የሲቪል መከላከያ ኤጀንሲ ገለጸ።
ተኩስ በተጀመረበት ቅዳሜ ጠዋት ሰዎች እርዳታ ለመውሰድ ተሰብስበው እንደነበር የኤጀንሲው ቃል አቀባይ ተናግረዋል።
የዓይን እማኝን ጠቅሰው የወጡ ዘገባዎች እነደሚያሳዩት የእስራኤል ወታደሮች ሰዎች ወደ ስፍራው ለማምራት ሲሞክሩ ተኩስ ከፍተዋል።
የእስራኤል ጦር በአስጊ ሁኔታ ወደ እነርሱ በቀረቡ ተጠርጣሪዎች ላይ የማስጠንቀቂያ ተኩስ መክፈቱን ተናግሯል።
በዚህ ሳምንት ብቻ ወደ ማከፋፈያው ማዕከል ለመድረስ ሲሞክሩ በደርዘን የሚቆጠሩ ፍልስጤማውያን ሲገደሉ በመቶዎች የሚቆጠሩ ደግሞ ቆስለዋል።
ማዕከሉን የሚያስተዳድረው በአሜሪካ እና በእስራኤል የሚደገፈው የጋዛ ሰብዓዊ ፋውንዴሽን መጨናነቅን ለመቋቋም እና ደህንነትን ለማሻሻል ስራውን ማቆሙን አስታውቋል።
ነገር ግን ሰዎች በእስራኤል ወታደራዊ ቀጠና ጠርዝ ላይ ባለው አደባባይ ወደ እርዳታ ማከፋፈያው ለመድረስ በዚያ ማለፍ አለባቸው ።
የእስራኤል መከላከያ ሠራዊት ባወጣው መግለጫ፣ አካባቢው በሌሊት የውጊያ ቀጠና መሆኑን ለጋዛውያን ማሳወቃቸውን ተናግሯል።
የጋዛ ሰብዓዊ ፋውንዴሽን በሃማስ ቀጥተኛ ዛቻ ምክንያት ቅዳሜ ዕለት ምግብ ማከፋፈል እንዳልቻለ የገለፀ ቢሆንም ቡድኑ ግን ውንጀላውን አስተባብሏል።
ጉዳዩ ምንም ይሁን ምን አዲሱ ክስተት በእርግጠኝነት በአዲሱ የስርጭት ሞዴል ላይ ዓለም አቀፍ ትችቶችን ያጠናክራል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ፍልስጤማውያንን ለአደጋ እንደሚያጋልጥ እና የጋዛን ሰብዓዊ ቀውስ ለመቋቋም በቂ ምግብ እና መድሃኒት እንደማይሰጥ ገልጿል።
የሲቪል መከላከያ ቃል አቀባይ ማህሙድ ባሳል እስራኤል በጋዛ ከተማ በሚገኝ የመኖሪያ ቤት ላይ ባደረሰችው የአየር ድብደባ ቢያንስ 15 ሰዎች መሞታቸውን ገልጸዋል።
የእስራኤል ጦር በጥቃቱ የሙጃሂዲን ብርጌድ በመባል የሚታወቀውን የፍልስጤም ታጣቂ ቡድን መሪ ተወግዷል ብሏል።
እስራኤላውያን ቡድኑን መስከረም 26 በሃማስ መሪነት በተፈፀመው ጥቃት ሰለባ የሆኑትን የታይላንድ ዜጋ ናታፖንግ ፒንታ ጨምሮ የተወሰኑትን በመግደል እና በማፈን ወንጅለዋል።
አስከሬኑ በደቡባዊ ጋዛ ራፋህ አካባቢ አርብ ዕለት በተደረገ ልዩ ዘመቻ ተገኝቷል።
እስራኤል ከሦስት ወራት እገዳ በኋላ በጋዛ ሰብዓዊ ፋውንዴሽን በኩል እንዲሰራጭ ቅድሚያ በመስጠት የተወሰነ እርዳታ ወደ ጋዛ እንዲገባ በቅርቡ ፈቅዳለች።
ፋውንዴሽኑ ግን በውዝግብ ውስጥ ተዘፍቋል።
የሕክምና ባለሙያዎች እና የአካባቢው የጤና ባለስልጣናት እንደገለፁት ስራ ከጀመረ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ከ60 በላይ ፍልስጤማውያን በተከፈተባቸው ተኩስ ተገድለዋል።
ለግድያው በርካታ ምስክሮች የእስራኤል ወታደሮችን ተጠያቂ አድርገዋል።
የእስራኤል ጦር በመጀመሪያዎቹ ሁለት ቀናት የማስጠንቀቂያ ተኩስ መተኮሱን እና በሦስተኛው ላይ ወደ ወታደሮቹ እየገሰገሱ በነበሩ ፍልስጤማውያን ተጠርጣሪዎች አቅራቢያ ጥይት መተኮሱን ገልጿል።
የስርጭት ጣብያው በጋዛ ውስጥ በጋዛ ሰብዓዊ ፋውንዴሽን ከሚንቀሳቀሱ አራት ማዕከላት አንዱ ነው።
እስራኤል ሃማስ ወደ ተዋጊዎቹ አቅርቦቱን እንዳያዞር መከላከል አልቻለም ስትል የከሰሰችውን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን ለመዘወር ያለመ አዲስ የእርዳታ ስርዓት ሲሆን በሰብዓዊ ቡድኖች በሰፊው የተወገዘ ነው።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሚሰጠውን ዕርዳታ ተጠያቂ ማድረግ እንደሚችል እና የጋዛ ሰብዓዊ ፋውንዴሽን ስርዓት የማይሰራ እና ስነምግባር የጎደለው መሆኑን በመግለጽ እነዚህን ክሶች ውድቅ አድርጓል።
በጦርነቱ ወቅት በጋዛ ቢያንስ 54,677 ሰዎች መሞታቸውን የጋዛ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አስታውቋል።