ሦስት የተለያዩ እጆች የተለያዩ መተግበርያዎች የሚያሳዩ ስማርት ስልኮችን ይዘው የሚያሳይ ምስል

ከ 5 ሰአት በፊት

ያለንበት ዘመን በሁሉም መስኩ የጥድፊያ ዘመን ነው። አንዱን አጣጥመው ሳይጨርሱ ወረቱ አልፎ በሌላ ይተካል።

ረዥም ነገር ማየት ልብ የሚጎትት ነገር እየሆነ መጥቷል። እጥር፣ ምጥን፣ ቅልጥፍ ያለ ነገር የዘመኑ መገለጫ ነው።

በዚህም የተነሳ ነው ቲክቶክ እንዲህ የአፍላ ጎረምሳው እና የአዛውንቱ መናኽሪያ የሆነው።

ትውልዱ በአጫጭር ተንቀሳቃሽ ምሥሎች ፍቅር የተለከፈ ይመስላል። ይህንን ደግሞ ቻይናውያን ጠንቅቀው ተረድተዋል።

አዲሱ የቻይና አጫጭር የቪድዮ መተግበሪያ የዓለም ቀልብን እየገዛ መጥቷል።

የአንድ ወይንም የሁለት ደቂቃ ርዝመት ያላቸው የአጭር አጭር ድራማዎችን (አጭሬ ድራማዎችን) የሚያሳዩ የሞባይል መተግበሪያዎች በበርካታ አገራት በብዛት ወደ ተንቀሳቃሽ ስልኮች መጫናቸውን መረጃዎች ያሳያሉ።

በመተግበሪያዎቹ ላይ የሚቀርቡት ድራማዎች ፈጣን እና ተከታታይ የሶፕ ኦፔራ መልክ ያላቸው አንዳንዴም የሚያሳፍሩ ናቸው።

ርዕሶቹም ቢሆኑ የሰውን ቀልብ ለመግዛት ተብለው የተበጃጁ እንደ “ቢሊየነሩ ባሌ እና ውሽሞቹ” ዓይነት ናቸው።

ተመልካቾች ከአንድ ሰዓት ባነሰ ጊዜ ውስጥ የ100 ሰዓታት ተከታታይ ድራማን እንዳዩ ዓይነት በፍላተ ስሜት ሊሞሉ፣ በልብ ሰቀላው በጥፍራቸው ሊቆሙ ይችላሉ።

አንድ ተጠቃሚ ሬዲት በተባለው የማኅበራዊ ሚዲያ መድረክ ላይ “እወደዋለሁ” ሲል ጽፏል።

“ምንም ጊዜ አያባክኑም ወዲያውኑ መሳሳም ይጀምራሉ” ሲልም ያለውን እውነታ ይናገራል።

በመላው ዓለም ከመቶ ሚሊዮን በላይ ጊዜ ተጭኗል

እስካለፈው መጋቢት ድረስ እነዚህ አጭሬ ድራማ የሚቀርቡባቸው መተግበሪያዎች በመላው ዓለም 950 ሚሊዮን ጊዜ ተጭነዋል።

መቀመጫውን በብራሰልስ ያደረገው ብሩጌል ውስጥ ከፍተኛ የምጣኔ ኃብት ባለሙያ የሆኑት አሊሺያ ግራሲያ ሄሬሮ ድራማዎቹን “ተደራሽ፣ ተንቀሳቃሽ፣ ፈጣን እና ሱስ አስያዥ ናቸው” ሲሉ ይገልጿቸዋል።

ከእነዚህ የአጭር አጭር ድራማን የሚያቀርቡ መተግበሪያዎች ጀርባ ያሉት ኩባንያዎች መቀመጫቸውን ያደረጉት አሜሪካ እና ሲንጋፖር ቢሆንም መነሻቸው ግን ቻይና ነች።

የተወሰኑት ድራማዎች በቻይንኛ ተቀርጸው ወደ እንግሊዝኛ የተተረጎሙ ናቸው።

ነገር ግን በዩናይትድ ኪንግደም እና በአሜሪካም መቀረጽ ጀምረዋል።

መቀመጫዋን ለንደን ያደረገችው እና እንደ አውሮፓውያኑ በ2024 አጫጭር ድራማዎችን ለመሥራት ኩባንያ ያቋቋመችው ፕሮዲውሰር ሉኡ ሻንሻን፣ ለተለያዩ መተግበርያዎች 15 ተከታታይ የአጭር አጭር ድራማዎችን ሠርታለች።

በአማካይ አንዱ ምዕራፍ ድራማ 20 እስከ 50 ክፍሎች ይኖሩታል።

ይህንንም ለመቅረጽ ከሰባት እስከ 10 ቀናት ይፈጃል ትላለች።

ተዋንያኑም ቢሆኑ ብሪታንያውያን ሲሆኑ ከቀረጻው ጀርባ ያሉት ባለሙያዎች ደግሞ ብሪታንያውያን እና ቻይናውያን ናቸው።

የፊልም ካሜራ

በቅርቡ ለዕይታ የበቃው የፍቅር ድራማ ባለ 58 ክፍል ነው።

‘ምሥጢራዊው የንጉሣዊ ቤተሰብ አፍቃሪዬ’ ይሰኛል ርዕሱ።

ዋና ገጸባህሪው የውድስበሪ መስፍን ሲሆን፣ ተዋንያኑ ደግሞ በብሪታንያ የቴሌቪዥን ድራማ ተመልካቾች ዘንድ የታወቀው ‘ሜድ ኢን ቼልሲ’ ላይ በመተወን ዝናን ያተረፈው ዲግቢ ኤድግሊ ነው።

ተዋንያኑ አጭሬ ድራማዎች ላይ በመሳተፍ ወደ ትወና መግባቱን ይናገራል።

“ለተዋንያን በጣም ምርጥ ልምድ ይመስለኛል” ይላል ኤድግሊ። “እጅግ በጣም፣ በጣም ፈጣን ነው።”

በቻይና ደግሞ አጭሬ ድራማዎችን የሚሠሩ ተቋማት የበለጠ ፈጣን አድርገዋቸዋል።

በቻይና የሚታተመው ‘ዘ ፔፐር’ በአንድ ሳምንት እስከ 100 ክፍሎች ሊቀረጹ ይችላሉ ይላል።

እንደ ቻይና ኔትካስቲንግ ሰርቪስስ አሶሲየሽን መረጃ ከሆነ ባለፈው የአውሮፓውያኑ ዓመት ከ30 ሺህ በላይ አጭሬ ድራማዎችን ለተመልካች ቀርበዋል።

እነዚህም በአጠቃላይ 7 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ያስገኙ ሲሆን፣ ይህም የቻይናን ቦክስ ኦፊስ ገቢ በእጅጉ አልፎ የሄደ ሆኗል።

የቻይና የሳንሱር መቀስ

ተመልካች በፍቅር የሚንሰፈሰፍላቸውን እነዚህን ድራማዎች የሚሠሩ ኩባንያዎችን አብጠርጥረው የሚፈትሹ የቻይና ባለሥልጣናት አልጠፉም።

በየካቲት ወር ከ1200 በላይ አጭሬ ድራማዎች ከቻይና መተግበሪያዎች ላይ እንዲወርዱ ተደርገዋል።

ይህ በቻይና የቲክቶክ አቻ ከሆነው ‘ዶዩን’ ላይ ጭምር የሆነ ነው።

የአጭር አጭር ድራማዎች “አዲሶቹ ቻናሎች እሴቶቻችንን በሚያሳድጉ እና በሚያሰፉ ነገሮች ላይ ማተኮር አለባቸው” ብሏል የቻይና ብሔራዊ የሬድዮ እና የቴሌቪዥን አስተዳደር።

“ወሲብ እና አመጽ ቀስቃሽ” የሆኑ ነገሮችን ከማገድ ባለፈ “ፀያፍ እና የማይመጥኑ” የተባሉትም ጭምር በመንግሥታዊው ተቆጣጣሪ አካል እንዲስተካከሉ ይደረጋል።

ሳንሱር የሚያደርገው አካል “ፀያፍ” ላለው ጉዳይ ግን ግልጽ ብያኔ ያላስቀመጠ ቢሆንም፤ አንድ ቢሊየነር የኩባንያ ባለቤት ከጽዳት ሠራተኛው ጋር ወይንም ከአማቹ ጋር ፍቅር ሲወድቅ በአማቹ የሚሰነዘረው ስድብን ግን ተገቢ ያልሆነ በሚል እንዲስተካከል አድርጎ ያውቃል።

በዩናይትድ ኪንግደም በሚገኘው ኬንት ዩኒቨርስቲ መምህር የሆኑት ኦስካር ዞሁ የአጭር አጭር ድራማዎች በፍጥነት ከተስፋፉ በኋላ የቻይና የሳንሱር መቀስ ከፍጥነታቸው አንጻር እነሱ ላይ ለመድረስ “እያለከለከ ነው” ብለዋል።

“ኢንዱስትሪው አዲስ ነው፤ ስለዚህ ሳንሱሩም እንደዚሁ፤ ስለዚህ ሁሉም ሥርዓት ከኋላቸው እያዘገመ ነው።”

ባለፈው ኅዳር ወር ላይ ከዶዩን አንዲወርድ የተደረገው ተከታታይ ድራማ “የዓለማችን ሐብታም አባቴ ነው” ይሰኛል ርዕሱ።

ድራማው “ቁሳዊነትን ሰባኪ እንዲሁም አባካኝ እና ቅንጡ ሕይወትን አበረታች” ነው በሚል ነው ከመተግበሪያው ላይ የወረደው።

ይሁን አንጂ ተመሳሳይ ጭብጥ እና ሴራ ያላቸው ሌሎች ድራማዎች በቻይና በሚታዩ መተግበሪያዎች ላይ አሁንም አሉ።

ድራማው በቻይና በ2023 ከተለቀቀ በኋላም ወደ እንግሊዝኛ የተተረጎመ ሲሆን፣ በዩቲዩብ ላይ 4 ሚሊዮን ተመልካቾችን ማግኘት ችሏል።

በጣም ዝነኛ ከመሆኑ የተነሳ ድራማውን የሠራው ኩባንያ ባለፈው ዓመት በጃፓን ገበያ ለማስፋት በሚል በጃፓንኛ ቋንቋ ተደግሞ ሠርቶታል።

ከጃፓን ባሻገር ኢንዶኔዢያ፣ ታይላንድ፣ ማሌዢያ የኩባንያው የገበያ መዳረሻዎች መሆናቸውን እና እንደ አገሩ ሁኔታ ድራማዎችን እንደሚሠሩ የኩባንያው የበላይ ኃላፊ ሊኡ ዢን ሎንግ ተናግረዋል።

ሌላ ‘ሪልሾርት’ የተሰኘ ኩባንያ በበኩሉ የላቲን አሜሪካ ተዋንያንን በመጠቀም በርካታ ድራማዎችን በስፓኒሽ ቋንቋ ሠርቷል።

‘ለመጨረሻ ጊዜ ሳመኝ’ የተሰኘው ድራማ ማስታወቂያው ብቻ በኢንስታግራም እና በቲክቶክ ላይ ሚሊዮኖች ተመልክተውታል።

እንደ ‘ሴንሰር ታወር’ መረጃ አሜሪካ አትራፊ የገበያ መዳረሻ ብትሆንም በ2025 የመጀመሪያ ሦስት ወራት ብቻ በላቲን አሜሪካ 100 ሚሊዮን የመተግበሪያው ተጠቃሚዎች ተገኝተዋል።

በደቡብ ምሥራቅ እስያ ደግሞ ይህ ቁጥር 87 ሚሊዮን ደርሷል።

የቻይና የመረጃዎች ምርምር ኩባንያ ‘ዳታአይ’ እንደሚለው ኩባንያዎቹ ወደ መካከለኛ ምሥራቅ እና አፍሪካ ለመግባት ገበያውን እያጠኑ ናቸው።

አንዲት በካሜሮን የምትኖር የአጭር አጭር ድራማዎች አድናቂ የቻይና አጭሬ ድራማዎችን ማስታወቂያ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ በ2023 ካየች በኋላ መከታተል እንደ ጀመረች ትናገራለች።

ባለፈው ዓመት ብቻ 60 ተከታታይ ክፍሎችን አይቻለሁ፣ በአጭሩ “ተለክፌያለሁ። ያንን ማለት ብቻ ነው የምችለው” ትላለች።