ህይወቱ ያለፈው አልበርት ኦጅዋን

ከ 4 ሰአት በፊት

የኬንያ ገለልተኛ የፖሊስ ተቆጣጣሪ ተቋም፤ “ሀሰተኛ መረጃ በማሰራጨት ” ተጠርጥሮ በእስር ላይ የነበረውን ኬንያዊ ግድያ በተመለከተ ምርመራ መክፈቱን የሀገሪቱ ፖሊስ አስታወቀ።

በኤክስ ገጹ ላይ ባጋራው ልጥፍ ምክንያት በቁጥጥር ስር የዋለው አልበርት ኦጅዋን፤ በምዕራባዊ የሀገሪቱ ክፍል በምትገኘው ሆማ ቤይ ከተያዘ በኋላ በ350 ኪሎ ሜትር ርቆ ወደ ናይሮቢ ከተማ መወሰዱን አባቱ ሜሻክ ኦፒዮ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።

ፖሊስ ባወጣው መግለጫ፤ “ተጠርጣሪው በቁጥጥር ስር እያለ ጭንቅላቱን ከእስር ቤቱ ግድግዳ ጋር በማጋጨቱ የጭንቅላት ጉዳት ደርሶበታል” ብሏል።

ወደ ሆስፒታል ቢወሰድም “እንደደረሰ ህይወቱ ማለፉ ተረጋግጧል” ሲልም አክሏል።

የሰብአዊ መብቶች ተሟጋቹ ተቋም አምነስቲ ኢንተርናሽናል የኬንያ ቅርንጫፍ ዳይሬክተር፤ መምህር እና ጦማሪ የሆነውን ኦጅዋን ሞት “እጅጉን አጠራጣሪ” ሲሉ ገልጸውታል።

አምነስቲ ባወጣው መግለጫ የግለሰቡ ሞት “በአስቸኳይ፣ በጥልቀት እና በገለልተኝነት መመርመር ያለባቸውን አሳሳቢ ጥያቄዎች ያስነሳል” ብሏል።

የከፍተኛ የፖሊስ መኮንን የሆኑት ስቴፈን ኦካል፤ በእስር ቤት ውስጥ የተፈጠረው “ራስን የማጥፋት ሙከራ” እንደሆነ መናገራቸውን የኬንያው ስታር ጋዜጣ ዘግቧል።

አልበርት ኦጅዋንን ለእስር የዳረገው “ሀሰተኛ መረጃ” ምን እንደሆነ ግልጽ አልሆነም። አባቶ ኦፒዮ ለሲቲዝን ዲጂታል የዜና ምንጭ እንደተናገሩት እስሩን የፈጸመው የፖሊስ አባል “አልበርት ኤክስ ላይ አንድ ከፍተኛ ሰውን ተሳድቧል” በማለት መናገሩን አስረድተዋል።

የአምነስቲ ኢንተርናሽናል የኬንያ ዳይሬክተሩ ኢሩንጉ ሆውተን ስለ እስሩ ሁኔታ ሲናገሩ፤ ኦጅዋን በቁጥጥር ስር ከዋለ በኋላ በአቅራቢያ የሚገኝ ፖሊስ ጣቢያ አለመታሰሩ እና ረጅም ርቀት እንዲጓዝ መደረጉ “እጅግ አስደንጋጭ” መሆኑን ገልጸዋል።

በናይሮቢ ከተማ የሚገኘው ፖሊስ ጣቢያ “የወንጀል ስፍራ” በማለት የጠሩት ዳይሬክተሩ፤ ገለልተኛ መርማሪዎች ይህንን ፖሊስ ጣቢያ እንዲጠብቁ ጥሪ አቅርቧል።

ፖሊስ በበኩሉ ኦጅዋን “በህጋዊ መንገድ እንደታሰረ” ገልጿል።

የአልበርት ኦጅዋን እስር እና ሞት የተሰማው መንግስት ላይ ትችት ሚያቀርቡ ግለሰቦች የሚስተናገዱበትን መንገድ በተመለከ ስጋቶች እየተነሱ ባሉበት ወቅት ነው።

ባለፈው ሳምንት ሶፍትወር አበልጻጊ የሆነችው እና የመንግስትን የፋይናንስ ቢል ለመቃወም የሚውል መገልገያ የሰራችው ሮዝ ንጃሪ፤ የሳይበር ወንጀል ህግን በመጣስ ተከስሳለች።