የክልሉ ፕሬዝዳንት ሙስጠፌ መሐመድ

ከ 6 ሰአት በፊት

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አስተዳደር ወደ ሥልጣን መምጣትን ተከትሎ በከፍተኛ ኃላፊነት መንግሥትን ከተቀላቀሉ ሰዎች መካከል አንዱ ናቸው፤ የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሙስጠፌ መሐመድ።

አቶ መስጠፌ፤ ከሰሞኑ በኬንያ ተገኝተው የሶማሊ ማኅበረሰብ ተወካዮች፣ እንዲሁም ኬንያ ከሶማሊያ ጋር ከምትዋስንበት ጋሪሳ ካውንቲ ባለሥልጣናት ጋር ውይይት አድርገዋል።

የርዕሰ መስተዳድሩ የናይሮቢ ጉብኝት፤ “በኢትዮጵያ እና ኬንያ የሚገኙ የሶማሊ ማኅበረሰቦችን ትብብር እና መረዳዳት ለማጠናከር” የሚል ዓላማ እንዳለው ተገልጿል።

አቶ ሙስጠፌ በኬንያ ቆይታቸው ከቢቢሲ ሶማሊኛ እና ቢቢሲ አማርኛ ጋር ቃለ መጠይቆችን አድርገዋል።

የቢቢሲ ጋዜጠኞች አቶ ሙስጠፌ በሚያስተዳድሩት የሶማሌ ክልል ውስጥ ያሉ ወቅታዊ ሁኔታዎችን፣ በክልሉ የሚፈጸሙ እስሮችን፣ የተቃዋሚውን የኦጋዴን ብሔራዊ ነፃነት ግንባርን (ኦብነግ) የተመለከቱ ጥያቄዎችን አንስተውላቸዋል።

ቢቢሲ – እርስዎ ናይሮቢ እያሉ በቀደመው አስተዳደር ላይ የሰላ ትችት ይሰነዝሩ ነበር። በይፋም፣ ይፋዊ ባልሆነ መንገድም። በተለይ በክልሉ በነበሩ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ላይ ድምጽዎትን ያሰሙ ነበር። ሥልጣን ከተያዘ በኋላ እንደ መተቸት ቀላል ነው ወይ? ካለፈው ሥርዓት በተለየ ምን አሳኩ?

ሙስጠፌ – መደበኛ ፖለቲካ ባለበት አገር ይሄ ጥያቄ ምናልባት፤ ውስጥ ስትገባ እና ውጭ ስትሆን የተለያየ ነው ሊያስብል ይችላል።

እርግጠኛ ነኝ፤ ወደ ፖለቲካ አመራር ከመጣህ በኋላ ድሮ ውጭ ሆነህ የማይታዩህ ብዙ ውስብስብ ነገሮች እንዳሉ፣ ነገሮች ሁሉ ነጭ እና ጥቁር እንዳልሆኑ ይበልጥ ይገባሃል።

ያኔ ስተች ከነበረው ሁኔታ አንጻር ግን ምንም የተለየ ነገር የለውም። በጣም ሥር የሰደደ አሰቃቂ የሰብአዊ መብት ጭፍጨፋ በሚደረግበትን ሁኔታ ውስጥ ገብቼ ሳየው፤ ያንን ማስቆሜ፣ ያ እንዳይኖር ማድረጌ የሞራል እረፍት ይሰጠኛል። እንጂ፤ ውጭ ሆኜ ስተች የነበረውን ‘ምን አልባት ተሳስቼ ነበር’ ወይም ‘አካብጄ ነበር’ አልልም።

በእስር ቤት ሰው ይማቅቃል፣ ሰው በሐሳብ ምክንያት ይገደላል፣ የጅምላ መቃብር ይኖራል። አላህ ረድቶኝም፤ ባለው አንጻራዊ ሰላም ወደዚያ ሁኔታ ውስጥ እንዳንገባ ስላደረግሁ ከፍተኛ የሞራል፣ የሕሊና እርካታ ይሰማኛል። እንጂ፤ ‘ያኔ ስተች የነበረው አንዳንዴ አብዝቼው ነበር እንዴ?’ አልልም።

ቢቢሲ – ከአብዲ ኢሌ አስተዳደር አንጻር ያለፉትን ሰባት ዓመታት ሲገመግሙ፣ ምን ዓይነት ስሜት ይሰማዎታል? ‘ብዙ ለውጫለሁ’ ብለው የስኬት ስሜት ነው የሚሰማዎት? ‘እንዳሰብኩት አልሄደልኝም?’ ብለው ጸጸት ነው የሚሰማዎት? ትክክለኛው ስሜትዎ በእርግጥ የትኛው ነው?

ሙስጠፌ – በከፍተኛ ደረጃ ስኬት እና የአእምሮ እረፍት ነው የሚሰማኝ። ለምሳሌ አጠር ለማድረግ፤ የሰብአዊ መብት ጥሰት ነበር፤ አሁን የለም። የሰላም እጦት ነበር፤ አሁን የለም። ክልሉ ውስጥ ሰላም አለ።የሶሻል ሚዲያ ዘመን ስለሆነ በሚዲያ ላይ የሚባለው እንዳለ ኾኖ፤ ከልማት አንጻር ክልል ከተመሠረተ ወዲህ በ30 ዓመት ከተሠሩ ሥራዎች የሚወዳደሩ ሥራዎችን በሁሉም መስክ ሠርተናል።ጊዜ ቢኖረን ኖሮ፤ በቁጥር፣ በዳታ ባስቀምጥልህ የበለጠ ተአማኒነት ያገኝ ነበር።

ቢቢሲ – ሙስና ግን በክልሉ አሁንም በከፍተኛ ሁኔታ አለ።

ሙስጠፌ – የለም። የሶማሌ ክልል ከ30 ዓመታት በፊት ከተፈጠረ ወዲህ ንጹህ የሆነውን (the cleanest) አስተዳደር እየመራሁ ነው ያለሁት። ንጹህ [አስተዳደር ነው] ብዬ አምናለሁ። ምክንያቱም ገንዘብ እየተበላ አይሠራም። እኛ ክልል ለምንድነው ሙስና የሚወራው? አንድ ነገር አለ። ‘ሲስተማቲክ’ ባይሆንም ሁሉም ቦታ ችግሮች ይኖራሉ።

ሁለተኛ ግን ይህንን አጀንዳ አድርጎ ማራገብ ስለተፈለገ ነው። ለምሳሌ፤ ‘ሙስና አለ’ የሚባለው ከማን ጋር ተወዳድሮ ነው?

ከእኔ ቀደም ከነበረው ሥርዓት ጋር ከተወዳደረ፤ በንግድ ጭምር የተቆጣጠረበት፣ ሰው የማይነግድበት፣ የጨረታ ሂደት የሌለበት፣ ክልሉ ከበጀቱ ውስጥ 15 በመቶውን ብቻ የሚያወጣበት፣ 85 በመቶ በፌደራል የድጎማ ድጋፍ የሚንቀሳቀስበት ሁኔታ ነበር።

ዛሬ ባለው ሁኔታ ክልሉ ከገቢው 45 በመቶ በራሱ ይሸፍናል። የዘንድሮውን በጀት ብናይ 40 ቢሊዮን ብር ነው። 23 ቢሊዮን አካባቢ የፌደራል [ድጎማ] ነው፤ 17.6 [በመቶውን] ክልሉ ነው ያወጣው።

ስለዚህ በመለኪያዎች (parameters) እና በዳታ ከታየ፤ በከፍተኛ ደረጃ ሙስናን ከመታገል አንጻር አሠራሮችን ዘርግተናል። እኔ ክልል ስሄድ የሀገር ሽማግሌ፣ ወጣት ሁሉም ኮንትራክተር የሆነበት ጊዜ ነው የነበረው። ዛሬ ይሄ የለም፤ የጨረታ ሥርዓት አለ። እንደውም ሰሞኑን የኤሌክትሮኒክ ግዢ ሥርዓት ተዘርግቷል።

ቢቢሲ – የቀድሞው የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አብዲ መሐመድ ኡመር (አብዲ ኢሌ) ከስድስት ዓመት እስር በኋላ ባለፈው ዓመት ተፈትተዋል። የቀድሞውን ርዕሰ መስተዳድር ከእስር መለቀቅ እንዴት ተመለከቱት?

ሙስጠፌ – አብዲ ሙሐመድ ኡመር የታሰረው በሐምሌ 28/2010 [ክስተት] ምክንያት ነው። የዛኔ በነበረው ሁከት እና ብጥብጥ ምክንያት ነው የታሰረው። የታሰረውም በፌደራል መንግሥት ነበር። አጠቃላይ ሂደቱንም በሙሉ የሚቆጣጠሩት እነሱ ናቸው። ነገር ግን ክልሉ ውስጥ የነበረውን ችግር [በተመለከተ] በእኛ በኩል እስካሁን ምርመራ ላይ ነን።

ቢቢሲ – ከእስር ቤት ለመለቀቁ የእናንተ እጅ አለበት?

ሙስጠፌ – የለበትም።

ቢቢሲ – መለቀቁ ትክክል ነው ብለው ያስባሉ?

ሙስጠፌ – አይ፤ ትክክል አይደለም ብዬ ነው የማስበው። ነገር ግን ሀገሪቱ በዚህ ሰዓት ውስጥ ሌሎች ፖለቲካዊ ችግሮች ስላሉ በዚህ ወቅት ላይ ይህንን ማውራት ተገቢ አይደለም።

ቢቢሲ – እርስዎ የሚመሩት አስተዳደር ወደ ሥልጣን በመጣ ወቅት በኩራት ከሚያነሳቸው ጉዳዮች መካከል አንዱ የሚዲያ ነጻነት ነበር። በአሁኑ ሰዓት ግን ፌስቡክ ላይ በሰጡት አስተያየት እና ባደረጉት ቃለ መጠይቅ ምክንያት የታሰሩ ሰዎች አሉ። በዚህ ጉዳይ ላይ ምላሽዎ ምንድነው?

ሙስጠፌ – መልሴ፤ መጀመሪያ [መገናኛ ብዙኃን ላይ የሚሠራ ሰው] የጋዜጠኝነት ክህሎት እና ዕውቀቱን ማሳደግ አለበት የሚል ነው። የሰማውን ነገር ብቻ ዝም ብሎ መውሰድ የለበትም። በ[ፌስቡክ] ኮመንት ምክንያት ልትታሰር ትችላለህ። ፖስት እና ኮመንት አንድ ናቸው። በቴክስት ሚሴጅም [በአጭር መልዕክት] ጭምር ልትታሰር ትችላለህ። መታየት ያለበት የመልዕክቱ ይዘት ነው። ለምሳሌ ‘ፕሬዝዳንቱ ይገደል’ ካልክ በፖስትም ይሁን፣ በሚሴጅም በኮመንትም አንድ ዓይነት ነው።

ቢቢሲ – ‘ፕሬዝዳንቱ ይገደል’ ያለ ሰው አለ?

ሙስጠፌ – የለም፤ እንደ ምሳሌ ነው ያነሳሁት። በኮመንት የታሰረ ሰው ካለ ስሙን ይቅረብልኝ እና ከዚህ ቃለ መጠይቅ በኋላ ጠይቀኝ። በኮመንት [በአስተያየት] የታሰረ ሰው እንደሌለ አውቃለሁ፤ ውሸት ነው።

ሁለተኛ፤ የተሳሳተ አስተያየት ከሆነ ሊታሰር ይችላል፤ ነውር አይደለም። እዚህ ኬንያ ውስጥ፣ አሜሪካ ውስጥም እንደዚህ ዓይነት እስር አለ። ነገር ግን ግልጽ የማደርገው በኮመንት የታሰረ ሰው የለም። የታሰረ ሰው ከነበረም ከእርምጃ በኋላ ተለቅቋል።

ቢቢሲ – ቢያንስ አራት ሰዎች በዚህ ዓይነት ሁኔታ ለእስር እንደተዳረጉ መረጃ አለን። ከእነዚህም መካከል አንዱ ጋዜጠኛ ነው። የቀድሞ የክልሉ ወጣቶች እና ስፖርት ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ እና የማኅበራዊ ጉዳዮች አክቲቪስትም አሉበት። የተወሰኑት በፍርድ ቤት ተፈርዶባቸዋል። የእስሩ ምክንያትም ከፌስቡክ ጋር የተያያዘ እንደሆነ ተነግሯል። እርስዎ በፌስቡክ ምክንያት የታሰረ ሰው የለም ነው የሚሉት?

ሙስጠፌ – አራቱም አሉ። ‘ከፌስቡክ ጋር በተያያዘ የታሰረ ሰው አለ’ ከተባለ አራቱ ሰዎች ናቸው። አራቱ፤ ጋዜጠኛ፣ አሁን የመንግሥት ኃላፊነት የሌለው የቀድሞ ባለሥልጣን እና ሁለት አክቲቪስቶች ናቸው። አራቱ ብቻ ናቸው፤ አምስተኛ ሰው የለም።

ሙስጠፌ መሐመድ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ መሐመድ ጋር

ቢቢሲ – ለምንድነው የታሰሩት?

ሙስጠፌ – እመጣልሃለሁ። የታሰሩት በዚህ ወር ነው። ከዚህ በፊት ግን በዚህ ሁኔታ የታሰረ ሰው አልነበረም። ምን አልባት ታስረው የተለቀቁ አንዳንድ ሰዎች ነበሩ። ማሰርም ይቻላል።

እነዚህ አራቱ ሰዎች የተከሰሱት የፀጥታ ኃይሎችን ስም በማጥፋት፣ የክልሉ እስር ቤቶች ሁኔታን በተመለከተ የተሳሳተ መረጃ በመስጠት፣ እስር ቤት ውስጥ በበሽታ የሞተውን ልጅ ጉዳይ ለራሳቸው ጥቅም ለማዋል፣ ሕዝብን የሚያሳስት እና የሚያነሳሳ ሥራ እየሠሩ ስለነበር [ነው]።

በዓለም አቀፍ እና በአገር ውስጥ ሕግ ፊት መቅረብ የሚችል ነገር ነው። የታሰሩት አራቱ ናቸው። ይህ በክልሉ የሚዲያ ነጻነት የለም የሚያስብል አይደለም።

ቢቢሲ – ከጠቀሷቸው ግለሰቦች መካከል አብዲ ባሩድ አንዱ ነው። ከእስር ቤት ከተለቀቁ ሰዎችን ጋር ባደረገው ቃለ መጠይቅ ምክንያት. . .

ሙስጠፌ – እኔ የማውቀው ‘እስር ቤት ውስጥ ብዙ የተጎዱ ሰዎች አሉ’ ብሎ እንደጻፈ ነው። ይህም ብቻ አይደለም፤ ይህ የታሰረበት አንዱ ምክንያት ነው። ጉዳዩን ለፍትሕ ቢሮ ነው የምተወው። እኛ መንግሥት ነን፤ ፌስቡክ ላይ ፍርድ ቤት እና ጠበቃ ማቋቋም አንችልም። እነዚህ ወጣቶች ቤተሰብ አላቸው፣ ጠበቃ አላቸው፣ እኔ ራሱ ጠበቃ ላቆምላቸው እችላለሁ።

ቢቢሲ – የእነዚህ ክሶች ትክክለኛነት እንዴት ነው ያረጋገጣችሁት?

ሙስጠፌ – እኔ አላረጋግጠውም። የታሰሩት በእኔ አይደለም። ፖሊስ ነው ያሰራቸው።

ቢቢሲ – አንድ ሰው ቅሬታ ሲኖረው፣ ያልተስማማበት ነገር ሲያስረዳ ወይም ስለ እስር ቤቶች ሁኔታ ሲናገር መንግሥት ጉዳዩን የማየት ኃላፊነት አለበት። አሁን ግን ሰዎች ቅሬታ የሚያቀርቡበት እና የሚታሰሩበት ጊዜ አንድ ሆኗል። ስለዚህ ‘መንግሥት ትኩረት የሚያደርገው የተነሳውን ነገር ላይ ሳይሆን ጉዳዩን ያነሱ ሰዎች ላይ ነው’ የሚሉ ሰዎች አሉ። ለዚህ ወቀሳ ምላሽ አለዎት?

ሙስጠፌ – ይኸውልህ፤ እኛ መላዕክት አይደለንም። ፖሊስ እና ዐቃቤ ሕግም መላዕክት አይደሉም። እኔ እየተናገርኩ ያለሁት ስለ ትክክለኛነታቸው እና ስለ ስህተታቸው አይደለም። የማወራው፤ አንድ ዜጋ ታስሯል አይደል? ፖሊስ ሌቦችን እየተከተለ እያለ የተተኮሰበት ሰው አለ አይደል? [እነዚህን ጉዳዮች መፍታትን በተመለከተ የእኔ አቋም] የፍትሕ ሥርዓቱን እንደግፈው [የሚል ነው]።

አንተ ካነሳሃቸው ሰዎች መካከል አንዱ የእኔ ዘመድ ነው። የእርሱ ቤተሰብ ደግሞ ጅግጅጋ ውስጥ ናቸው። ይምጡ እና ይሞግቱኝ፤ እኔ ዝግጁ ነኝ። ወደ ፍርድ ቤት ይሂዱ፣ ወደ አዲስ አበባ ጭምር አቤቱታቸውን ይውሰዱ። የሕግን ነገር ፖለቲካ ማድረግ ግን ተገቢ ነው?

ከዚህ በፊት ሰዎች ከመኪና ላይ ይወረወሩ የነበረበት ክልል፣ ሴቶች የሚደፈሩበት ክልል፣ እንዲያውም ብዙ ቦታዎች የጅምላ መቃብር የነበረበት ክልል [ነው]። እኔ ከመምጣቴ በፊት የተለቀቁ ሰዎች እያሉ እንኳን ወደ እስር ቤት ስሄድ ሰባት ሺህ ሰዎች ታስረው ነበር። እስር ቤቱ 500 ታራሚ ለመያዝ ታስቦ የተዘጋጀ ነበር።

ዛሬ እኔ እና አንተ የምንከራከረው ስለ አራት ሰዎች መታሰር ከሆነ ለውጥ እንዳለ ያሳያል። ዜጎች ናቸው፤ መብታቸውን ለመጣስ አይደለም። እኔ ኃላፊነት እወስዳለሁ፤ ምሕረት የሚያስፈልግበት ጊዜ ሲመጣ ውሳኔ የምሰጥበት ጉዳይ ይሆናል።

የክልሉ ፕሬዚዳንት ሙስጠፌ መሀመድ

ቢቢሲ – ሶማሌ ክልል ውስጥ ያሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ቅሬታ አላቸው። ከፓርቲዎቹ መካከል አንዱ ኦጋዴን ብሔራዊ ነፃነት ግንባር (ኦብነግ) ነው። ከዚህ ቀደም ቢቢሲ ቃለ መጠይቅ ያደረገላቸው የፓርቲው ሊቀመንበር አቶ አብዲራህማን መህዲ ካነሷቸው ቅሬታዎች መካከል አንዱ በጅግጅጋ ከተማ እና በሌሎች የክልሉ ዞኖች የሚገኙ የፓርቲው ጽሕፈት ቤቶች ‘ጥቃት ደርሶባቸዋል፣ ተዘግተዋል፣ በዚህም ምክንያት ፍራቻ ተፈጥሮባቸዋል’ የሚሉት ይገኙበታል። ‘መንግሥት እንደገና ወደ ጫካ ለመግባት እያስገደደን ነው’ የሚል ቅሬታም ያቀርባሉ። ስለዚህ ቅሬታ ምን ይላሉ?

ሙስጠፌ – ይህንን ክርከር እንተወውና፤ በጅግጅጋም ሆነ በሌሎች ዞኖች የታሰረ አንድም የዚህ ፓርቲ አባል የለም። ይሄ ነገር ፍራቻ ከሆነ ፍርሃታቸውን መተው አለባቸው። እኔ ልሰጣቸው የምችለው ምክር ብቻ ነው። አንድም የታሰረ ሰው የለም።

ቢቢሲ – ጽሕፈት ቤታቸው ግን ተዘግቷል።

ሙስጠፌ – እርሱን እመጣበታለሁ። ቃለ መጠይቁ መጯጯህ እንዳይሆን፤ መናገር ያለብኝ ትክክለኛውን ነገር ነው። የታሰረ ሰው ካለ እናያለን፤ ግን የለም ነው የምልህ። እነሱም ‘አለ’ ማለት አይችሉም። አንድም የተዘጋ ቢሮ የለም። ነገር ግን ከአንድ ወር በፊት ለመንግሥት ያላሳወቁት ስብሰባ [ተካሂዶ] ነበር።

በዚያ ወቅት ደግሞ ‘አንድ ልጅ ተገድሏል’ እየተባለ ነበር። ፖሊሶችም ይህንን ስብሰባ እንዲያራዝሙ እየነገሯቸው ነበር። መንግሥት በዚህ ጉዳይ ግዴታ አለበት።

ፖሊስ ወደ ቦታው የሄደው ስብሰባው ካለቀ በኋላ ነው። ይህንን ስብሰባ በዚህ ሰዓት ማድረግ ትክክል እንዳልሆነ ነገራቸው። የተወሰነ መገፈታተር ተፈጥሯል። የተያዙ ሰዎች ከተወሰኑ ቀናት በኋላ ተፈትተዋል። ከዚህ የዘለለ ነገር የለም።

አንዳንድ ቦታዎች ለምሳሌ በኤረር ዞን ወደ ቢሮ ለመግባት ተከለከልን የሚል ቅሬታ ነበራቸው። እርሱም ቢሆን ተፈትቷል።

ኦብነግ በሀገሪቱ ሕገ መንግሥት ሥር ነው። የአብዲራህማን መህዲ ራሱ ሊቀመንበር የሆነው ከምርጫ ቦርድ በተሰጠ ደብዳቤ ነው። አሁን [ከሊቀ መንበርነት] ያነሳውም ምርጫ ቦርድ ነው። ከኦብነግ ስብሰባ በኋላ የእርሱ ምክትል ፓርቲውን እንዲመራ የወሰነው ምርጫ ቦርድ ነው። ስለዚህ ዛሬ በጅግጅጋም ሆነ በሌሎች ዞኖች አንድ ቢሮ ይዘጋ አይዘጋ የሚለውን የሚወስነው አዲሱ ጊዜያዊ ሊቀ መንበር ነው።

ሰኔ ላይ ጠቅላላ ጉባኤ እስከሚያደርጉ ድረስ ሊቀ መንበሩ የአሁኑ ጊዜያዊ ሊቀመንበር ነው። አሁን እውቅና ያለው፣ ሀገር ውስጥም ያለው ሊቀመንበር አብዲከሪም ሼክ ሙሴ ካልቢደጋህ ነው። እርሱ ቅሬታ ካለው ለማስተናገድ ዝግጁ ነን። ቅሬታው የሚመጣው ከተገነጠለው ክንፍ ከሆነ መብታቸው ነው፤ ግን እውነት አይደለም።

ቢቢሲ – ስለዚህ በአቶ አብዲራህማን መህዲ የሚመራው ኦብነግ በጅግጅጋ ከተማ ያለው ጽሕፈት ቤት ‘ክፍት ነው’ እያሉ ነው?

ሙስጠፌ – የኦብነግ ቢሮዎች ክፍት ናቸው። ሕጉ፤ የአብዱራህማን ቢሮ፣ የካልቢደጋህ ቢሮ፣ የእከሌ ቢሮ አይልም። ኦብነግ ፓርቲ ነው። በዚህ ሰዓት የአብዱራህማን ታማኞችም ሆነ፤ አንድም የተዘጋ ቢሮ የለም። ግን ‘የትኛውን ቢሮ እንዘጋለን፤ የትኛውን እንከፍታለን’ የሚለውን የሚወስነው በጠቅላላ ጉባኤ የተሾመ ሊቀመንበር ነው።

ቢቢሲ – በእርስዎ አገላለጽ መሠረት ጅግጅጋ ውስጥ ያሉት ሁለት የተለያዩ የኦብነግ ቢሮዎች ናቸው ማለት ነው?

ሙስጠፌ – አዎ፤ ጅግጅጋ ውስጥ ሁለት የተለያየ ቢሮ አላቸው። እውነቱን መናገር አለብን፤ ይህ ነገር የመጣው ሊቀመንበሩ እና ምክትል ሊቀመንበሩ በመጣላታቸው ነው። መንግሥት በዚህ ጉዳይ ውስጥ ምንም እጁ የለበትም። ከውጭ ሆነን እየተመለከትን ነበር። ምክንያቱም እንደ አብዱራህማን ክስ እንዳይመጣ እጃችንን ሰብስበናል። ከዚህ በኋላ ከመንግሥት ጋር መሥራት የሚችሉት ፓርቲው አንድ ሆኖ በጠቅላላ ጉባኤ ሊቀመንበር ከሾሙ በኋላ ነው።

ቢቢሲ – አቶ አብዲራህማን መህዲ ከቢቢሲ ጋር በነበራቸው ቃለ መጠይቅ፤ ከስድስት ዓመት በፊት በኤርትራ አሥመራ ከተማ ከመንግሥት ጋር ከተፈረመው ስምምነት ነጥቦች መካከል ‘ትጥቅ ማስፈታት’ ከሚለው ውጪ አንዱም እንዳልተፈጸመ ተናግረዋል። አሁን በአቶ አብዲራህማን መህዲ የሚመራው ክንፍ እንደገና ጫካ ለመግባት የሚወስን ከሆነ ጉዳዩ ያሳስብዎታል?

ሙስጠፌ – እኔ እንደ ግለሰብ ይሄ ጉዳይ የሚያሳስበኝ ነገር አይደለም። አብዲራህማን እና የእርሱ ቡድን ጫካ ከገቡ፤ ከዚህ በፊትም ጫካ ነበሩ። ግን የሚያስጨንቀኝ ከሀገር ቤት ተነጥለው ወደ ውጭ ሀገር መሄዳቸው ነው። እኔ የምፈልገው ከእኛ ጋር ሆነው ሀገራቸው ላይ እንዲዝናኑ ነው።

ሶማሌ ክልል ውስጥ ኦብነግ ወደ ጫካ እንዲገባ የሚያስገድድ ነገር የለም። የሚያስጨነቀኝ ነገር አይደለም፤ ግን ከመጣ እንዴት እንደምናስተናግደው እናውቃለን። በፍጹም የሚያሳስበኝ ነገር አይደለም። ሕዝቡም ይህንን እየፈቀደ አይደለም። በእርግጥ አንድ ግለሰብ ትክክለኛ ያልሆነ ሐሳብ ይዞ ከግብፅ ወይም ከሌላ ሀገር ድጋፍ አግኝቶ ሊሆን ይችላል። ግን እኔ የመጣሁበት ሕዝብ እንደዚህ ዓይነት ነገር አይቀበልም።

ቢቢሲ – የአቶ አብዲራህማን መህዲ ቡድን ‘ከሌላ ሀገር ድጋፍ እያገኘ ነው’ የሚል ክስ እያቀረቡ ነው?

ሙስጠፌ – አዎ፤ ኦብነግ ‘ጫካ እንገባለን’ የሚለው ሌሎች ሀገራት እና ሌሎች ቡድኖች በተለይ በሰሜን ኢትዮጵያ ያሉ ኃይሎች እያበረታቱት ነው ብዬ አምናለሁ።

ቢቢሲ – ከዚህ ቀደም ከኦብነግ ጋር የተደረሰው ስምምነት የተፈረመው በኤርትራ ነው። ከኤርትራ መንግሥትም ድጋፍ ያገኙ ነበር። አሁን ኤርትራ እንደ ግብፅ ሁሉ ኦብነግን እየደገፈች ነው የሚል ጥርጣሬ አላችሁ?

ሙስጠፌ – አዎ፤ ሊሆን ይችላል። እኔ ያለኝን መረጃ ነው የምናገረው። ማንኛውም የኢትዮጵያ ጠላት ሀገራት ኢትዮጵያ ውስጥ የሚካሄደውን ጦርነት ለማበረታታት እየሞከሩ [እንደሆነ]፣ ሕዝቡን ለመቀስቀስ ዕቅድ እንዳላቸው እናውቃለን። ስለዚህ የትኛውምን ተቃዋሚ ቡድን ይጠቀማሉ።

ቢቢሲ – የሶማሌ ክልል በቆዳ ስፋት ሰፊ ነው፣ ሕዝቡም ብዙ ነው። ነገር ግን ለዓመታት ‘አጋር’ ተደርጎ ነበር የሚታየው። በኢትዮጵያ የፖለቲካ ሜዳ ግንድ አልነበረም፤ ቅርንጫፍ ሆኖ ነው የሚታየው። እርስዎ ከመጡ ወዲህ የሶማሌ ሕዝብ የኢትዮጵያዊነት ስሜቱ ከፍ ብሏል? በፌደራል ደረጃስ የሚገባውን ውክልና አግኝቷል? በዚህ ረገድ ምን ሠርተዋል?

ሙስጠፌ – እኔ ከመጣሁ በኋላ የሶማሌ ሕዝብ ድሮ የነበሩት ስሜቶች እየተቀረፉ በኢትዮጵያዊነቱ እያመነ፣ በኢትዮጵያዊነቱ ሲያምን ደግሞ የይስሙላ ሳይሆን ‘ከኢትዮጵዊነት እጠቀማለሁ፣ ሰላም አለኝ፣ ልማት እየመጣልኝ ነው፣ ውክልናዬ እየተሻሻለ ነው፣ የአገር ባለቤትነቴ እየተረጋገጠ ነው’ የሚል ስሜት አለው። ይህንን በክልሉ ያለው የሃይማኖት፣ የብሔር መቻቻል በተግባር ያሳያል።

ይህንን ሁሉ እየጠበቀ ያለው መንግሥት ብቻ አይደለም። አንዳንዴ ሚዲያ ላይ እንደሚባለው አንድ አመራር ወይም የተወሰኑ አመራሮች ጥሩ ሰዎች ስለሆኑ ወይም ስላሉ አይደለም። ሕዝቡ [ውስጥ] ጭምር ያለ ስሜት ስለሆነ ነው። ኢትዮጵያውያን ነን፣ አብረን መኖር አለብን፣ ሃይማኖትን ማክበር አለብን የሚል ስሜት ስለመጣ ነው።

ዛሬ፤ የመገንጠል ስሜት የነበረው ሁኔታ ከሞላ ጎደል [almost] ቀርቷል ማለት ይቻላል። ያውም በሶሻል ሚዲያ ዘመን፤ ሚዲያ ላይ የለም። አሁን ሚዲያ ላይ ሌሎች አጀንዳዎች ናቸው [ያሉት]፤ እየተራገበ አይደለም። ስለዚህ ድሮ ዳር ሆነን እናኮርፍ የነበረውን ስሜት ትተን፤ አሁን መሀል ሄደን፤ ‘መሀሉ የእኛ ነው፤ መሀል መሆን አለብን’ ወደሚል አስተሳሰብ ተቀይሯል።

ይህንን የሚያግዝ ደግሞ የፌደራል ውክልና አግኝተናል። የፓርቲ ጽህፈት ቤት ኃላፊ እና ምክትል የፓርቲ ኃላፊ፣ ፋይናንስ ሚኒስቴር ከሶማሌ ክልል ነው። ከውክልና አንጻር ቁጥር ብቻ ሳይሆን በፌደራል ደረጃ ያላቸው ሚዛን ጥሩ ነው።

ከውክልና አንጻር ድሮ አጋር ነን አሁን በዋና ፓርቲ ውስጥ 23 ማዕከላዊ ኮሚቴ አለን፣ አራት ሥራ አስፈጻሚ፣ እስከ ፓርቲው ምክትል ፕሬዝዳንት ነው ያለነው። ይሄ ለሶማሌ ክልል በተጨባጭ ተሳትፏችን፣ ድምጻችን ማደጉን ነው የሚያሳየው።

ይህንን ስንል ‘ውክልና ይበቃኛል’ የሚል ማንም የለም። ቀሪ መግባት ያሉብን ቦታዎች አሉ።

ፀጥታ ዘርፍ ላይ ተሳትፏችን ዝቅተኛ ነው። የፌደራል ቢሮክራሲ ላይ ተሳትፏችን ዝቅተኛ ነው። ተከልክለን አይደለም። አንዳንዱ ተፈጥሯዊ እንቅፋቶች (natural barriers) አሉ። የቋንቋ እንቅፋት፣ አንዳንድ ነገሮች አሉ። አንዳንዱ ደግሞ እኛ አካባቢ ያሉ. . . መሥራት ያለብንን ባለመሥራታችን ምክንያት [የመጣ] አለ።

በአጠቃላይ ግን የሶማሌ ሕዝብ ኢትዮጵያዊነቱን ጠመንጃ ሳይፈራ፤ ከእኔ በፊትም የነበረው አስተዳደርም እኮ ያስጨበጭባል፣ ‘ኢትዮጵያዊ ነኝ’ ይላል። ሰው በሚፈራበት፣ ነጻነት በሌለበት ሁኔታ ከልቡ ይሁን አይሁን በምን ይታወቃል?

ቢቢሲ – ስለ ፌደራል ስናነሳ፤ እርስዎ ወደ ፌደራል መንግሥት ኃላፊነት እንዲመጡ አስተያየቶች ይሰነዘራሉ። እንደዚህ ዓይነት ምኞት አለዎት? ጥያቄስ ቀርቦልዎት ያውቃል? ወደ ክልል ከመሄድዎ በፊት መጀመሪያ ‘ፕሬዝዳንት እንዲሆኑ ጥያቄ ቀርቦላቸው ነበር’ ይባላል።

ሙስጠፌ – እኔ ወደዚህ ኃላፊነት እንድመጣ የወሰነው የአገሪቱ አመራር ነው። በተለይም ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ናቸው በዚህ ጉልህ ሚና የሚኖራቸው። በነበረው ሂደት የክልሉ አመራር ችግር ውስጥ ሲገባ ክልሉን ሊያረጋጉ የሚችሉ ምሁራን ሲፈለጉ በዚያ ሂደት ውስጥ እንድካተት ስላደረጉ ማለት ነው። ቀጥሎ ያለው ሂደት በፓርቲ መዋቅር ውስጥ የተፈጸመ ነው።

አሁን ባለው ሁኔታ የፓርቲ አባል ነኝ። ስለዚህ እኔ ክልል ልመደብ፣ ፌደራል ልመደብ አልመደብ አይደለም። ዋናው በተመደብኩበት ሥራ፣ የተሰጠኝን የሥራ ኃላፊነት መወጣት እና ውጤት ማምጣት ነው። የእኔ ዓላማ ውጤት ማምጣት ነው። ያንን ግምገማ የማደርገው እኔ አይደለሁም። ፓርቲው፣ ሕዝቡ ነው የሚያደርጉት። እዚያ ላይ ያለውን የስኬት ዝርዝር (score sheet) አመራሮች የሚወስኑት ነው። ያንን ገምግመው በዚህ ቦታ መቀጠል አለብህ ተብሎ የሚሰጠኝን ተልዕኮ ለመወጣት ዝግጁ ነኝ። እስካሁን ወደ ፌደራል አካባቢ እንድመጣ የቀረበልኝ አስተያየት የለም።

ቢቢሲ – የግል ፍላጎትስ አለ?

ሙስጠፌ – አዎ አለኝ። ዕድሜ ልኬን ሶማሌ ክልል ውስጥ አልቀመጥም መቼም።

ቢቢሲ – ፍላጎቱ ካልዎት በካቢኔ ውስጥ የሚመርጡት፣ ቢሆን የሚሉት ቦታ አለ?

ሙስጠፌ – አልመርጥም። አስተዋጽኦ የማደርግበት፣ አቅሙ ያለኝ. . .

ቢቢሲ – እርሱ የትኛው ማለት ነው?

ሙስጠፌ – አሁን በማላቀው የሥራ መስክ ብገባና ብዙም የማልጠቅምበት ከሆነ፤ የማውቀው ነገር ቢሆን እመርጣለሁ። ለምሳሌ ሙያዬ ‘አግሪካልቸራል ኢኮኖሚክስ’ [የግብርና ምጣኔ ሃብት] ነው። ተያያዥ የሆኑ ሥራዎች፤ [በእርግጥ] የፖለቲካ ሹመት ግዴታ በትምህርት ሙያህ ብቻ አይደለም። ነገር ግን ያግዛል ባይ ነኝ። በባለሙያ ብቻ ከመታገዝ የምታውቀውን ብትሠራ የተሻለ ነው የሚል እምነት ስላለኝ አልመርጥም። ግዴታም ሚኒስቴርነት መሆን የለበትም። በምመደብበት ቦታ ሁሉ ለመሥራት ዝግጁ ነኝ።

ቢቢሲ – የፌስቡክ ገፅዎ ላይ ሰዎች ኮሜንት መስጠት እንዳይችሉ ገድበዋል። ለምንድን ነው?

ሙስጠፌ – አልገደብኩም። ሰዎች ኮመንት [አስተያየት] መስጠት ይችላሉ። የፌስቡክ ገጼ እንደ ራሴ ቤት ነው። አንተም ገብተህ የጻፍኩትን ነገር ማየት ትችላለህ። ለምሳሌ አሁን ስለ ጅግጅጋ ከተማ ‘እንዲህ ዓይነት ነገር አከናውናለሁ’ ብዬ ከጻፍኩ አንተ እዛው ላይ ኮመንትህን መስጠት የምትፈልግ ከሆነ ሼር አድርገህ ‘ፕሬዝዳንቱ የጻፈው ነገር ትክክል አይደለም’ ማለት ትችላለህ። ለሁለታችንም ጥቅም ነው።

በእኔ እና በሰዎች መካከል አለመግባባት የሚፈጥረው ነገር ምንድነው? እኔ የምለው ‘ሼር አድርጋችሁ እዛ ላይ ሐሳባችሁን ጻፉ’ [ነው]። እነሱ የሚሉት ‘እምቢ፤ ዕይታችንን የምንጽፈው ባንተው ፌስቡክ ላይ ነው’ የሚል ነው።

አንዳንድ ሰው የገዛ ቤቱን መቃሚያ ሊያደርግ ይችላል። ሌላ ሰው ደግሞ ከዚህ ተቃራኒ የቤቱን ንፅህና ሊጠብቅ ይችላል። አንዳንድ ‘ኮሜንት መስጫውን ክፈት’ የሚሉ ሰዎች የእኔ የፌስቡክ ገጽ ላይ ስለ ብሔርተኝነት፣ የጥላቻ ንግግር ማውራት የሚፈልጉ ሰዎች ናቸው፤ እኔም አልፈልግም።

እኔ የምፈልገው፤ በዕይታ ከእኔ የሚለይ ነገር ያለው ሰው ፌስቡክ አለው፤ በራሱ ፌስቡክ ይጻፍ። ማንም አይከለክለውም። ስለዚህ ከሚዲያ ነጻነት ጋር የሚቃረን ነገር የለውም። ግን እኔ የገጹን ሥነ ምግባር እየጠበቅኩ ነው። የዓለም መሪዎችም ይህንን ነገር ይፈልጋሉ ብዬ አስባለሁ። ግማሾቹ አሁንም ያደርጉታል።

ቢቢሲ – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ጋር በቅርብ ከመሥራትዎ ጋር ተያይዞ እንዴት ይገልጿቸዋል? ስለእርሳቸው ሕዝብ አያውቀውም የሚሉትን ነገር ይንገሩን።

ሙስጠፌ – በዚህ አጭር ጊዜ የመጣልኝን ልንገርህ። ሶማሌ ክልል ለመጣው ሰላም ትልቅ አስተዋጽኦ ያደረገው ድሮ የነበረው ጣልቃ ገብነት አለመኖር ነው።

ትክክለኛ ፌዴራሊዝም ከመተግበር አንጻር ራሳችን ነን የምንወስነው። ማን ይግባ ማን ይውጣ [እኛ ነን ወሳኞቹ]።

እርግጥ በአገር አቀፍ ደረጃ የሚሰጡ ስትራቴጂክ ሥራዎች አሉ። አተገባበር ላይ ግን በሙሉ ነጻነት ነው የምንሠራው። ከዚህ አንጻር ጠቅላይ ሚኒስትሩ አንድ ቀን በሥራዬ ገብተውብኝ አያውቁም።

ቢቢሲ – እውነትዎን ነው?

ሙስጠፌ – እውነቴን ነው።

ቢቢሲ – እንትናን አንሳው፣ እንትናን ሹመው የሚል ነገር የለም?

ሙስጠፌ – እየነገርኩህ ነው። [ይህን ስናገር] እውነቱን ነው ብሎ የሚያምን ብዙ ሰው ላይሆን ይችላል። ሰው ይመን አይመነው አይደለም። እኔ ሕሊናዬ የሚነግረኝን ነው መናገር ያለብኝ። እንደ ፖለቲከኛ ደግሞ አለመታመን ከሙያው ጋር ተያይዞ የሚመጣ ጉዳት (Occupational Hazard) ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጣልቃ ገብተውብኝ አያውቁም።

ይሄን ነጻነት እንደሚሰጡ ብዙ ሰው አያውቅም። ብዙ ጊዜ ሚዲያ ላይ የሚቀርበው ሁሉም ነገር በእሳቸው ቁጥጥር የሚደረግ ተደርጎ ነው። ይሄን ነገር ዛሬ አይደለም፣ ከመንግሥት ሥራ ከወጣሁ በኋላም የምመሰክረው ነገር ነው።