ተሟጋቾችን የጫነችው መርከብ

ከ 3 ሰአት በፊት

ከበባ ውስጥ ባለችው ጋዛ እርዳታ ለማስገባት ከተለያዩ አገሮች የተውጣጡ ሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችን ጭና ወደ ጋዛ እያቀናች የነበረችው ማድሊን የተሰኘችው መርከብ እንዲሁም ተሟጋቾቹ በእስራኤል ኃይል መያዛቸው ተገለጸ።

መርከቧ በዓለም አቀፍ ውሃ ውስጥ ከተያዘች በኋላ ተሟጋቾቹ ወደ እስራኤል መወሰዳቸውን የእስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገልጿል።

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ማድሊን መርከብ በባለስልጣናቱ እንደተጠለፈች አረጋግጧል።

ተሟጋቾቹ እስራኤል የጣለችውን እገዳ በመቃወም ነበር እርዳታን ጭነው ወደ ጋዛ እያቀኑ የነበሩት።

መርከቧ በእስራኤል ጦር እንድትቆም የተደረገችው ከጋዛ በ160 ኪሎሜትር ርቀት ላይ እያለች እንደሆነ ተገልጿል።

ጉዞው የተዘጋጀው የእስራኤል ኢሰብዓዊና ህገወጥ እገዳን ለማጉላት የተቋቋመው ‘ፍሪደም ፍሎቲላ’ በተሰኘው የዓለም አቀፍ ጥምረት ነው።

የአየር ንብረት ተሟጋቿ ግሬታን ቱንበርግን ጨምሮ ፈረንሳያዊቷ የአውሮፓ ፓርላማ አባል በመርከቧ ውስጥ ከተሳፉሩት መካከል ይገኙበታል።

የአውሮፓ የፓርላማ አባሏ ሪማ ሐሰን እና ተሟጋቾቹ “በእስራኤል ጦር በአለም አቀፍ ውሃ ላይ” ሌሊት ስምንት ሰዓት ላይ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ቡድናቸው ገልጿል።

ከዚያ ቀደም ብሎ ሪማ “አልታጠቅንም። ሰብዓዊ እርዳታ ብቻ ነው የያዘነው” ሲሉ ለኤኤፍፒ የዜና ወኪል ተናግረው ነበር።

ስዊድናዊቷ ተሟጋች ግሬታ “እስራኤልን በሚደግፉ ኃይሎች መርከቧ መጠለፏን እና ተሟጋቾችም መታገታቸውን” ባስተላለፈችው መልዕክት አስፍራለች።

ፍሎቲላ የተሰኘው ዓለም አቀፍ እጥረት ከአንድ ወር በፊት ‘ኮንሺየንስ የተሰኘች’ መርከብ ወደ ጋዛ ልኮ ነበር። መርከቧ በማልታ ወደብ ላይ በእሳት የተያያዘች ሲሆን ተሟጋቾች በእስራኤል ድሮኖች በዓለም አቀፍ ውሃ ላይ ተመትታለች ብለዋል።

እስራኤል ጥቃቱን እየመረመረች እንደሆነ ገልጻለች።

የእስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቀደም ሲል እንዳስታወቀው የሃገሪቱ የባህር ኃይል መርከቧ አቅጣጫዋን እንድትቀይር ትዕዛዝ አስተላልፏል።

በኋላ ላይ መርከቧ “ወደ እስራኤል የባህር ዳርቻ በሰላም እየሄደች ነው” ብሏል።

በዚች የእርዳታ መርከብ ላይ የብራዚል፣ ፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ ኔዘርላንድስ፣ ስፔን፣ ስዊድን እና ቱርክ ዜጎች አሉበት።

ማድሊን መርከብ ወደ ጋዛ የምታደርገውን ጉዞ ያቀናጁት ‘ፍሪደም ፍሎቲላ ኮኦሊሽን’ አባል የሆነችው የጀርመን ሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ከመርከቧ ላይ ሆና ቀድሞ የተቀረጸ የቪዲዮ መልዕክት አስተላልፋ ነበር።

ተሟጋቾችን የጫነችው መርከብ

መርከቧ በባህር ላይ እንደተጠለፈችና እሷና ሌሎች መብት ተሟጋቾች “በእስራኤል ወራሪ ኃይሎች ወይም በፍልስጤም ዘር ጭፍጨፋ በንቁ እየተሳተፉ ካሉ አንደኛው አጋራቸው ታግተናል” ስትል በቪዲዮዋ አስፍራለች።

ባለፉት ጥቂት ሰዓታት ውስጥ የፍሪደም ፍሎቲላ ኮኦሊሽን በማድሊን ተሳፍረው ከሚገኙ ተሟጋቾች ቀደም ብለው የተቀረጹ ቪዲዮዎችን በቴሌግራም ቻናሉ በተከታታይ አውጥቷል።

ሚኒስትሩ መርከቧ “በሰላም ወደ እስራኤል ዳርቻ እየሄደች ነው” ሲል በኤክስ ገጹ አጋርቷል።

ጽሁፉ ግሬታ እና ሌሎች ተሟጋቾችን ታዋቂነት ለማግኘት የሚዲያ ቅስቀሳ እያደረጉ ነው ሲል ወንጅሏቸዋል።

በተጨማሪም በባለፉት ሳምንታት በጋዛ በቂ እርዳታ እየገባ ነው ብሏል።

ሆኖም እስራኤል ከረጅም ጊዜው እገዳ በኋላ እርዳታ እንዲገባ ብትፈቅድም የእስራኤል ጦር እርዳታ በሚጠብቁ ፍልስጤማውያን ላይ በተደጋጋሚ ተኩስ ከፍቶባቸዋል።በዚህም በቅርቡ እሁድ የተገደሉትን 13 ፍልስጤማውያንን ጨምሮ በርካታ ፍልስጤማውያን ተገድለዋል።

በእስራኤል በኃይል በተያዙ የፍልስጤም ግዛቶች የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብት ልዩ መልዕክተኛ ፍራንቼስካ አልባኔዝ በቀጣናው የሚገኙ ጀልባዎች የእስራኤል የባህር ላይ እገዳ በመቃወም ወደ ጋዛ እርዳታ እንዲወስዱ ጥሪ አድርገዋል።

ልዩ መልዕክተኛዋ አክለውም በማድሊን መርከብ ላይ የዩናይትድ ኪንግደም መንግሥት “በአስቸኳይ ሙሉ ማብራሪያ እንዲጠይቅ እና መርከቧ እና ተሳፋሪዎቿ መፈታታቸውን” እንዲያረጋግጥ ጠይቀተዋል።

በተባበሩት መንግሥታት ድጋፍ በተደረገው ግምገማ መሰረት በጋዛ ከ 2 ሚሊዮን በላይ ነዋሪዎች ለረሃብ ተጋልጠዋል።

እስራኤል በከበባ ውስጥ ባስገባቻት ጋዛ ከሶስት ወር እገዳ በኋላ የተወሰነ እርዳታ ጋዛ ሂውማኒታሪያን ፋውንዴሽን በሚባል ድርጅት አማካኝነት እንዲሰራጭ ፈቅዳ ነበር።

ድርጅቱ በአሜሪካ እና በእስራኤል የሚደገፍ ሲሆን በቅርቡም እርዳታ ሊቀበሉ ወደ ማዕከሉ በተሰባሰቡ ፍልስጤማውያን ላይ ተኩስ ተከፍቶ በርካቶች ተገድለዋል።

እርዳታ ሊቀበሉ በቆሙ ፍልስጤማውያን ላይ የእስራኤል ጦር በከፈተባቸው ተኩስ ስድስት ፍልስጤማውያን መገደላቸውን በሐማስ የሚመራው የሲቪል ዲፌንስ ኤጀንሲ ገልጿል።

በመቶዎች የሚቆጠሩ ፍልስጤማውያን ተጎድተዋል።