
ከ 1 ሰአት በፊት
በኬንያ የሚሰለጥን የዩናይትድ ኪንግደም ወታደር አንዲት ሴትን ደፍሯል በሚል በቁጥጥር ስር መዋሉ ተገለጸ።
ግለሰቧ የተደፈረችው በአገሪቱ የዩናይትድ ኪንግደም የጦር ማሰልጠኛ ካምፕ አቅራቢያ እንደሆነ ተገልጿል።
ከዚህ ቀደም በዚህ ስፍራ የሚሰለጥን ወታደር አንዲት ኬንያዊትን በመግደል ክስ እንደቀረበበት ይታወሳል።
የባቱክ የጦር ሰፈር የተቋቋመው አገሪቱ ከቀድሞ ቅኝ ገዥዋ ነጻነትዋን ከተጎናጸፈች በኋላ በአውሮፓውያኑ 1964 ሲሆን፣ ስፍራውም ከናይሮቢ 200 ኪሎሜትት ርቀት ላይ በምትገኘው ኛኙኪ ነው።
ወታደሩ ድርጊቱ ከተፈጸመ በኋላ በቁጥጥር ስር ውሎ በፖሊስ ምርመራ እንደተከተፈተበት ተገልጿል። ወታደሮቹ በከተማዋ የሚገኝ አንድ መጠጥ ቤት ከጎበኙ በኋላ መደፈሩ መፈጸሙም ተነግሯል።
በዩናይትድ ኪንግደም እና በውጭ አገራት በወታደሮች ተፈጽመዋል የተባሉ ወንጀሎችን የሚመረምረው የዩኬ የመከላከያ ከባድ ወንጀል ክፍል የሆነው የወታደራዊ ፖሊስ ምርመራ እየተካሄደ እንደሆነ ገልጿል።
የዩኬ የመከላከያ ሚኒስትር በኬንያ አንድ “ወታደር” በቁጥጥር ስር መዋሉን አረጋግጧል።
“ተቀባይነት የሌለው እና የወንጀል ባህርይ በመከላከያ ሰራዊታችን ውስጥ ምንም ቦታ የለውም። የትኛውም ከባድ ወንጀል በአገልግሎት ሰጭዎቻችን ላይ ሪፖርት ከተደረጉ ከዕዝ ሰንሰለታቸው በጸዳ መልኩ ምርመራ ይደረጋል” ብሏል።
በኬንያ በሥልጠና ላይ ባሉ የዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) ወታደሮች ጥሰቶች ተፈጽሞብናል የሚሉ ኬንያውያን ምስክርነታቸውን በባለፈው ዓመት መስጠታቸው ይታወሳል።
በኬንያ በመሰልጠን ላይ የነበሩት እና ባቱክ የተሰኙት የዩናይትድ ኪንግደም ወታደሮች አድርሰዋቸዋል የተባሉ ግፎችን እና በደሎችን ለማጣራት ነው ይህ ሕዝባዊ አጣሪ ቡድን የተቋቋመው።
ለዚህ አጣሪ ኮሚቴ መነሻ የሆነው ከአስራ ሁለት ዓመታት በፊት በዩናይትድ ኪንግደም ወታደሮች ተገድላ ተጥላ የተገኘችው ኬንያት የአግነስ ዋንጂሩ አስደንጋጭ ሁኔታ ነው።
በ21 ዓመቷ የተገደለችው አግነስ ዋንጂሩ አስከሬኗ በማዕከላዊ ኬንያ በሚገኝ ሆቴል በሽንት ቤት ፍሳሽ ማጠራቀሚያ ውስጥ የተገኘ ሲሆን፣ ይህ የሆነው ከዩኬ ወታደሮች ጋር አንድ ምሽት ላይ ስትዝናና ከታየች ከሦስት ወራት በኋላ ነው።
የአምስት ወር ጨቅላ እናት የነበረችው ሟቿ ዋንጂሩ ለመጨረሻ ጊዜ የታየችው ከሁለት የብሪታኒያ ወታደሮች ጋር ከመጠጥ ቤት ስትወጣ ነበር።
ታዲያ ከጊዜ በኋላ ወታደሮቹ ከቆዩበት ክፍል በስተጀርባ የአካል ክፍሎቿ ጎድለው እና በስለት ቆስለው አስከሬኗ ተገኝቷል።
እንደ አውሮፓውያኑ በ2019 የኬንያ ፍርድ ቤት ግራ ቀኙን ተመልክቶ ዋንጂሩ በአንድ ወይም በሁለት የብሪታኒያ ወታደሮች ተገድላለች የሚል ብያኔ ሰጥቷል።
የኬንያ የወንጀል ምርመራ ዳይሬክቶሬት በግድያዋ ላይ ምርመራ ቢከፍትም የተከሰሰ ሰው የለም፤ እንዲሁም ኬንያ ተጠርጣሪዎች ተላልፈው እንዲሰጧት አልጠየቀችም።
ሰንደይ ታይምስ በአውሮፓውያኑ 2021 የዩናይትድ ኪንግደም መከላከያ ሚኒስቴር ግድያውን ለመሸፋፈን እየሞከረ ነው በሚል መዘገቡን ተከትሎ ሚኒስቴሩ ከኬንያ ባለስልጣናት ጋር በምርመራው ላይ ትብብር እያደረገ መሆኑን ገልጿል።
ዩኬ ተጠርጣሪዎች ተላልፈው እንድትሰጥ የሚቀርብ ማንኛውንም ጥያቄ እንደማትቃወም ጠቁማለች።
ሌሎች በጦሩ አባላት ተፈጽመዋል ከተባሉ ምስክርነቶችም መካከል ጦሩ በመኪና ገጭቶ ለአካል ጉዳተኛ የደረጋት ወጣት ነፍሰ ጡር፣ በሠራዊቱ የማሠልጠኛ ስፍራ ወታደሮቹ አስነስተውታል በተባለ እሳት ቤታቸውን አጥተው በአንበሳ ጉዳት የደረሳባቸው ሰዎች ይገኙበታል።
የባቱክ የጦር ሰፈር ከኬንያ መንግሥት ጋር በተደረገ ስምምነት በየዓመቱ እስከ ስድስት የሻለቃ ጦር ለስምንት ሳምንታት ወታደራዊ ልምምዶችን ያደርጋሉ።