
9 ሰኔ 2025
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በ12 አገራት ላይ አዲስ የጉዞ ዕገዳ ጥለዋል። ከእነዚህ ውስጥ ሰባቱ በአፍሪካ ይገኛሉ።
በአህጉሪቱ ያሉ ሰዎች የሚጠይቋቸውን በጎግል ትሬንድ እና በቢቢሲ ኒውስ አፍሪካ ማኅበራዊ መድረኮች ላይ ስንከታተል ቆይተናል።
ከሚነሱ ዋና ዋና ጥያቄዎች እና ስጋቶች መካከል ጥቂቶቹን እነሆ።
በአዲሱ የጉዞ ዕገዳ ውስጥ የተካተቱት አገራት የትኞቹ ናቸው?
በአዲሱ የአሜሪካ የጉዞ ዕገዳ ከተጎዱት 12 አገራት ሰባቱ በአፍሪካ ይገኛሉ።
- ኤርትራ፣ ሱዳን፣ ሶማሊያ፣ ቻድ፣ ኮንጎ ብራዛቪል፣ ኢኳቶሪያል ጊኒ እና ሊቢያ
ሌሎቹ አፍጋኒስታን፣ ምያንማር፣ ሄይቲ፣ ኢራን እና የመን ናቸው።
ዕገዳው የሚከተሉትን ጨምሮ በተለያዩ አገራት ላይ ከፊል ገደቦችን ይጥላል፡-
- በአፍሪካ ብሩንዲ፣ ቶጎ እና ሴራሊዮን፣ እንዲሁም ኩባ፣ ላኦስ፣ ቱርክሜኒስታን እና ቬንዙዌላ።
የእነዚህ አገራት ዜጎች ለተወሰኑ የቪዛ ምድቦች ማለትም እንደ የተማሪ እና የቱሪስት ቪዛ ያሉ ማመለከት የታገዱ ሲሆን ሌሎች የቪዛ ዓይነቶችን አሁንም ሊያገኙ ይችላሉ።
ዕገዳው ቀነ ገደብ አለው? እንዲነሳስ አገሮች ምን ማድረግ ይችላሉ?
ዕገዳው ሰኞ ሰኔ 2/2017 ዓ.ም. ጀምሮ ተግባራዊ ይሆናል።
ዕገዳው የሚያበቃበት ቀነ ገደብ የለውም፤ ነገር ግን ትዕዛዙ ከዚህ ቀን በፊት የተሰጠ ቪዛ እንደማይሰረዝ በግልጽ አስቀምጧል።
የአሜሪካው ፕሬዝደንት ዝርዝሩ አገራት “የሚሻሽሏቸው ነገሮች” ካሉ እንደሚቀየር እና “በዓለም ላይ ስጋት እየፈጠረ የሚመጣ” ካለ ደግሞ ተጨማሪ አገራት ሊካተቱ እንደሚችሉ ገልፀዋል።
እነዚህ ውስን የአፍሪካ አገራት ለምን ዒላማ ተደረጉ?
ትራምፕ ዕገዳ የጣሉባቸው አገራት ፓስፖርት እና የግለሰብ ሰነዶችን በመስጠት ረገድ አጠራጣሪ ብቃት እንዳላቸው ወይም ከዚህ ቀደም ከአሜሪካ የተባረሩ የራሳቸውን ዜጎች ለመቀበል ፈቃደኛ አለመሆናቸውን ተናግረዋል።
ከተጠቀሱት ሌሎች ምክንያቶች መካከል ደግሞ ዕገዳ ከተጣለባቸው አገራት የመጡ ሰዎች የአሜሪካን ቪዛ ሕግ መጣስ እንዲሁም ለአሜሪካውያን የፀጥታ እና የሕዝብ ደኅንነት ስጋቶች ናቸው ተብሏል።
የዋይት ሐውስ ቃል አቀባይ አቢጌይል ጃክሰን ዕገዳው “አሜሪካውያንን ከአደገኛ የውጭ ተዋናዮች ይጠብቃል” ብለዋል።
ቃል አቀባይዋ ለቢቢሲ የአሜሪካ አጋር ሲቢኤስ እንደተናገሩት “እነዚህ ገደቦች አገራትን ነጥለው የተመለከቱ እና ትክክለኛ የማጣራት ችግር ያለባቸው፣ ከቪዛቸው ቀን በላይ የመቆየት መጠን የሚያሳዩ ወይም የማንነት እና ስጋት መረጃዎችን የማያጋሩ አገራትን ያጠቃልላል” ብለዋል።https://flo.uri.sh/visualisation/23666587/embed?auto=1
ውሳኔው የሚያያዘው ከደኅንነት ወይስ ከፖለቲካ ጋር?
ፕሬዝዳንት ትራምፕ በቅርቡ በቦልደር ኮሎራዶ ተፈጽሟል የተባለውን የሽብር ጥቃት በመጥቀስ “በትክክል ካልተጣራ” የውጭ ዜጎች ሊያስከትሉ የሚችሉትን አደጋ አጉልቶ ያሳያል ብለዋል።
ይኹን እንጂ በዚያ ክስተት ተጠርጣሪው የግብፅ ዜጋ ቢሆንም፣ ግብፅ በአዲሱ የጉዞ ዕገዳ ከተጣለባቸው አገራት መካከል አይደለችም።
ተቺዎች ዝርዝሩ ግልጽነት የጎደለው እና በፖለቲካዊ ወይም በዘር ላይ የተመሠረተ ይመስላል ብለዋል።
አክለውም በተለይ ሁሉም የፀጥታ ችግር ያለባቸው አገራት በዕገዳው ውስጥ ያልተካተቱ መሆናቸውን የጠቀሱ ሲሆን፣ ዕገዳው የተጣለባቸው አገራት ከአሜሪካ ጋር በተያያዘ የቅርብ ጊዜ የሽብር ታሪክ የላቸውም ብለዋል።
የአፍሪካ ኅብረት “እነዚህ እርምጃዎች ሊያስከትሉ የሚችሉት አሉታዊ ተፅእኖ አሳስቦኛል” ያለ ሲሆን፣ ዩናይትድ ስቴትስ “ከሚመለከታቸው አገራት ጋር. . . የበለጠ የምክክር አካሄድ” እንድትከተል ጠይቋል።
አምነስቲ ኢንተርናሽናል ዩኤስኤ ድርጊቱን “አድሏዊ፣ ዘረኛ እና ግልጽ የወጣ ጭካኔ” ሲል ገልጾታል።
መቀመጫውን አሜሪካ ያደረገው ሂውማን ራይት ፈርስት ደግሞ በፕሬዚደንቱ “ሌላ ፀረ ስደተኛ እና የቅጣት እርምጃ ተወሰደ” ሲል አውግዞታል።
በአሜሪካ የሶማሊያ አምባሳደር በሰጡት መግለጫ “የተነሱትን ችግሮች ለመፍታት መንግሥታችን ውይይት ለማድረግ ዝግጁ ነው” ብለዋል።
ሶማሊያ በፕሬዝደንት ትራምፕ “የአሸባሪዎች መሸሸጊያ ስፍራ” ተብላ ተፈርጃለች።
ዕገዳው በአሜሪካ ባሉ ቤተሰቦች እና ስደተኞች ላይ ምን ተጽእኖ ይኖረዋል?
በአዲሱ የጉዞ ክልከላ፣ በአሜሪካ ውስጥ በሚኖሩ አንዳንድ ስደተኞች እና ቤተሰቦች ላይ የሚያሳድረውን ተጽእኖ የሚቀንሱ በርካታ ነጥቦች ተዘርዝረዋል።
- ግሪን ካርድ ያላቸው እገዳው የማይመለከታቸው ሲሆን ወደ አሜሪካ መግባት ይችላሉ።
- በአሜሪካ ዜጎች በማደጎ የተወሰዱ ልጆች
- ሁለት ዜግነት ያላቸው፤ የአሜሪካ ዜግነት ያላቸው ዕገዳው አይመለከታቸውም።
- የአሜሪካ ዜጎች የቅርብ ቤተሰብ አባላት የትዳር አጋሮች፣ ልጆች እና ወላጆች ለቪዛ ማመልከት ይችላሉ።
- ቢያንስ ለ15 ዓመታት በውጭ አገራት ለአሜሪካ መንግሥት ያገለገሉ አንዳንድ የውጭ አገር ዜጎች፣ የትዳር አጋሮቻቸው እና ልጆቻቸው።
- በኢራን ውስጥ ስደት ለሚደርስባቸው በቁጥር አነስተኛ የሆኑ የጎሳ እና የሃይማኖት ማኅበረሰብ አባላት እና የስደተኛ ቪዛ የያዙ ሰዎችም ከዕገዳ ነጻ ናቸው።
- ልዩ የስደተኛ ቪዛ ያላቸው የአፍጋኒስታን ዜጎችም እንዲገቡ ተፈቅዶላቸዋል።
ምንም እንኳ ዕገዳው ከ12 የአፍሪካ አገራት ወደ አሜሪካ መግባትን የሚገድብ ቢሆንም በእነዚህ ምድቦች ውስጥ የሚካተቱ ግለሰቦች ግን ዕገዳው አይደረግባቸውም።
በዚህ አዲስ ዕገዳ ላይ የሕግ ተግዳሮቶች ሊኖሩ ይችላሉ?
በዋይት ሐውስ የሮይተርስ ጋዜጠኛ ጄፍ ሜሰን ለቢቢሲ እንደተናገረው አዲሱ ዕገዳ በአውሮፓውያኑ 2017 በትራምፕ የመጀመሪያው የሥልጣን ዘመን ከወጣው እና በርካታ የሙስሊም አገራትን ካካተተው ጋር ተመሳሳይ ነው።
በእርግጥ በዚህ ዕገዳ ሰፋ ያለ አገራት በዝርዝሩ ውስጥ ተካትተዋል።
ሜሰን እገዳው የወጣው በፕሬዝዳንታዊ ትዕዛዝ ነው ብሏል። አስተዳደሩ ይህን እርምጃ የመተግበር ሥልጣን እንዳለው ያምናል።
ይኹን እንጂ አዲሱ ዕገዳ ልክ እንደ ቀዳሚው ሁሉ ሕጋዊ ተግዳሮቶች ሊገጥሙት እንደሚችሉ ጠቅሶ፣ እገዳው በተጣለባቸው አገራት በሚገኙ ሰዎች ላይ ስላለው ተጽእኖ ጥያቄዎችን ሊያስነሳ ይችላል ብሏል።
የዕገዳው አስገራሚ ጉዳዮች
ባለፉት ዓመታት ትራምፕን በቅርበት ለሚከታተሉ ሰዎች የአሁኑ እርምጃ ምንም አያስደንቅም።
ትራምፕ ወደ ዋይት ሐውስ ዳግም ከተመለሱ በኋላ ስደተኞች እና ሰነድ አልባ ነዋሪዎች ላይ ዘመቻ ጀምረዋል።
ይህ እርምጃም የዚያ አካል ተደርጎ ይቆጠራል።
እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2017 የመጀመሪያ የሥልጣን ዘመናቸው ወቅትም ተመሳሳይ ዕገዳን ተግባራዊ አድርገው ነበር።
አሁን በአዲሱ ዝርዝር ውስጥ የተካተቱ ሶማሊያ እና ቻድ እንዲሁ በመጀመሪያው የሥልጣን ዘመናቸውም ዒላማ ሆነው ነበር ።
ዕገዳው በዓለም ዋንጫ የሚሳተፉ ቡድኖች ላይ ተጽእኖ ይኖረዋል?
የትራምፕ ፕሬዝዳንታዊ ትዕዛዝ ለአትሌቶች፣ ለቡድን አባላት፣ ለአሠልጣኞች፣ ለደጋፊ ሠራተኞች እና ለቅርብ ዘመዶቻቸው እንደ ዓለም ዋንጫ እና ኦሊምፒክ ላሉ ዋና ዋና የስፖርት ዝግጅቶች የሚጓዙትን በግልጽ ነጻ ማድረጉ ለፊፋ መልካም ዜና ነው።
ይህ ማለት ለ2026 የዓለም ዋንጫ ያለፈችው ኢራን ቡድኗን እና አስፈላጊ ደጋፊ ሠራተኞቿን ወደ ውድድር መላክ ትችላለች።
ሆኖም የኢራን ተጫዋቾች ጓደኞቻቸውን ወይም የቤተሰብ አባላትን ወይም የሩቅ ዘመዶቻቸውን እንዲያመጡ አይፈቀድላቸውም ።
የቅርብ ዘመዶቻቸውን ብቻ ይዘው መምጣት ይችላሉ።
ትራምፕ ከዚህ ቀደም ከጣሉት የጉዞ ዕገዳ በምን ይለያል?
ፕሬዝዳንት ትራምፕ በመጀመሪያ የሥልጣን ዘመናቸው በሰባት ሙስሊም በሚበዙባቸው አገራት ላይ ያነጣጠረ የጉዞ ዕገዳ አውጥተው ነበር።
ይህንንም ተቺዎች “የሙስሊም ዕገዳ” የሚል ስያሜ ሰጥተዋል።
ትዕዛዙ ብዙ የሕግ ተግዳሮቶች ስላጋጠመው በ2018 በአሜሪካ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ከመጽደቁ በፊት ብዙ ጊዜ ተሻሽሏል።
ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በ2021 ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ ዕገዳውን ሰርዘዋል።
አዲሱ ዕግድ የበለጠ ስልታዊ በሆነ መንገድ የተዘጋጀ ነው። የቢቢሲ የሰሜን አሜሪካ ዘጋቢ ጄክ ኩውን እንደገለጸው፣ አመክንዮውን ከሃይማኖት ወደ የቪዛ ቆይታን ማራዘም እና የፖለቲካ አለመረጋጋት ወደመሳሰሉ ጉዳዮች ለውጧል።
እንደ ኢራን፣ ሊቢያ እና ሶማሊያ ያሉ አገራት በሁለቱም ዝርዝሮች ውስጥ ሲገኙ፣ አዲሱ ዕገዳ ወደ 12 አገራት ከፍ ብሏል።
ከ90 እስከ 120 ቀናት ከተገደበው ከመጀመሪያው ዕገዳ በተለየ ይህ ዕገዳ የተወሰነ የማብቂያ የጊዜ ገደብ የለውም።