ጉግል

ከ 7 ሰአት በፊት

ከወራት በፊት የአሜሪካ ምርጫ ከመካሄዱ አስቀድሞ አሜሪካውያን ድምጻቸውን ለማን እንደሚሰጡ ለመወሰን ጉግልን እያማከሩ ነበር።

‘ካማላ ሃሪስ ጥሩ የዴሞክራት ዕጩ ናት?’ ሲሉ ጉግልን ጠይቀዋል። ጉግልም እንዴት ካማላ ጥሩ የፕሬዝዳንት ዕጩ እንደሆኑ የሚገልጽ መረጃ ሰጥቷል።

ብዙም ሳይቆይ ጉግል ተቃራኒ መረጃ አቅርቧል።

‘ፒው ሪሰርች ሴንተር’ መረጃ ሲያስስ ያገኘው እና አሶሽየትድ ፕሬስ የሠራው ዘገባ ላይ ስለ ካማላ የተባለው የተለያየ ይዘት አላቸው።

‘ካማላ እንዴት መጥፎ እንደሆነች መርሳት ቀላል ነው’ የሚል ዘገባ በ’ሪዝን’ መጽሔት ወጥቷል።

ዩኤስ ኒውስ ኤንድ ወርልድ ሪፖርት ደግሞ ‘ካማላ አሜሪካ ከገጠሟት ሰዎች የከፋችው ናት’ ይላል።

ሌላው ጉግል የሚያቀርበው አል ጀዚራ ላይ የወጣ ዘገባ ‘ካማላ ሃሪስን የማልመርጥበት ምክንያት’ ይሰኛል።

በተመሳሳይ ስለ ዶናልድ ትራምፕ መረጃ ቢያስሱ ተቃራኒ ጽሑፎች፣ የሴራ ትንታኔዎች እና የፖለቲካ ክርክሮች ያገኛሉ።

አንዳንድ ባለሙያዎች እንደሚሉት፣ ጉግል የምንፈልገውን ዓይነት መረጃ ነው የሚሰጠን። ለእኛ ዕሳቤ ቅርብ የሆኑ መረጃዎችን በማቅረብ ሐሳባችንን ያጠናክራል።

በዩኒቨርስቲ ኦፍ ሳውዝ ፍሎሪዳ ተባባሪ ፕሮፌሰር ቫሮል ካይሀን፣ “ማግኘት የምንፈልገውን መረጃ የሚሰጠን ጉግል ነው። በጉግል ቸርነት ነው የምንኖረው ማለት ይቻላል” ይላሉ።

በድራገን ሜትሪክስ ተቋም የዲጂታል ማርኬቲንግ ባለሙያ ሳራ ፕሬስች እንደሚሉት፣ ጉግል ዋነኛ ግቡ ሰዎች ማግኘት የሚፈልጉትን መረጃ መስጠት ነው።

“ሆኖም ግን ሰዎች ያስፈልገናል የሚሉት መረጃ ብቻ ያስፈልጋቸዋል ማለት አይደለም” ይላሉ።

‘ድራገን ሜትሪክስ’ እንዴት ድረ ገፆች በጉግል ላይ የተሻለ ዕይታ ማግኘት እንደሚችሉ ያማክራል።

ይህንን በሚሠሩበት ወቅት ጉግል እንዴት መረጃዎችን እንደሚያዋቅር ተረድተዋል።

ጉግል በተለይም ከጤና ጋር የተያያዙ መረጃዎችን የሚያቀርብበት መንገድ ጥያቄ ያስነሳል።

“ፈጣን ምላሽ ለመስጠት በሚል ከድረ ገፆች የተገኘ መረጃ ያቀርባል” በማለት ባለሙያዋ ይገልጻሉ።

‘በቡና እና በደም ግፊት መካከል ያለው ትስስር’ በሚል ጉግል ሲደረግ፣ ማዮ ክሊኒክ ከሚለው ድረ ገጽ መረጃ ይመጣል።

ጉግል በዋናነት የዚህን ድረ ገጽ መረጃ ነው የሚያቀርበው።

መረጃው “ቡና ለአጭር ጊዜ የደም ግፊትን ሊጨምር ይችላል” ይላል። ሆኖም ግን በዚያው ድረ ገጽ ላይ “ቡና በዘላቂነት በደም ግፊት ላይ የሚያሳድረው ጫና የለም” የሚል ተቃራኒ መረጃ ሰፍሯል።

ጉግል

ጉግል ስለ ፖለቲካም የሚሰጣቸው ምላሾች ተቃርኖ ያላቸው ናቸው።

ባለሙያዋ እንደሚሉት፣ ጉግል ሰዎች የሚፈልጉትን መረጃ ተከትሎ ያንን የሚያጠናክር ተጨማሪ መረጃ ይሰጣል።

ጉግል የሚሰጠው መረጃ የተዛባ እንዳልሆነ ይገልጻል። መረጃው ሰዎች በሚፈልጉት ላይ የተመሠረተ ቢሆንም ሚዛናዊ መሆኑን ያስረዳል።

ባለሙያዎች ግን ጉግል ሚዛናዊነቱን የጠበቀ አይደለም ይላሉ።

“ሰዎች የሚፈልጉትን መረጃ መነሻ አድርጎ ማንበብ የሚፈልጉትን ያቀርባል” ሲሉ ሳራ ፕሬስች ይከራከራሉ።

ለዚህ የጉግል ምላሽ “እንደ መረጃ ማሰሻ ተቋም፣ ሰዎች ለሚፈልጉት ነገር በቂ መረጃ እናቀርባለን” የሚል ነው።

ከተለያዩ ድረ ገጾች የተውጣጡ እና ለሰዎች ጠቃሚ ናቸው የተባሉ መረጃዎችን እንደሚያቀርብ ጉግል ይገልጻል።

ጉግል መረጃ የማቅረብ ኃላፊነቱን በአግባቡ እየተወጣ እንደሆነ ይከራከራል።

ቃል አቀባዩ “ሰዎች የሚፈልጉትን መረጃ ብቻ ጉግል ያቀርባል የሚለውን ሐሳብ ገለልተኛ ተመራማሪዎች ውድቅ አድርገውታል” ይላሉ።

ተጠቃሚዎች የሚፈልጉትን መረጃ ብቻ ማቅረብ የሚለው ሐሳብ ‘filter bubbles’ አልያም ‘echo chambers’ በሚሉ ርዕሶች ዋነኛ መነጋገሪያ አጀንዳ ሆኗል።

ተባባሪ ፕሮፌሰር ቫሮል ካይሀን በሠሩት ጥናት፣ መረጃ ማሰሻዎች ሰዎች ያላቸውን ዕሳቤ የሚያጠናክር መረጃ ያቀርባሉ? በሚለውን ፈትሸዋል።

በበይነ መረብ የምናየው መረጃ የፖለቲካ አቋማችንን ጨምሮ ዕሳቤያችን ላይ ተጽዕኖ እንደሚያሳድር መረጃዎች ይጠቁማሉ።

የጉግል ቃል አቀባይ እንደሚሉት፣ በ2023 የተሠራ ጥናት እንደሚጠቁመው፣ ሰዎች ለአስተሳሰባቸው ቅርብ የሆነ መረጃ የሚያነቡት ጉግል ስላቀረበላቸው ሳይሆን ምርጫቸው ስለሆነ ነው።

ሰዎች የሚያምኑበትን ነገር የሚያጠናክር መረጃ ይፈልጋሉ ሲሉ ያስረዳሉ።

ሆኖም ግን ጉግልም ገለልተኛ እና ሚዛናዊ መረጃ ብቻ ያቀርባል ማለት እንዳልሆነ ጥናቱ ያሳያል።

ጉግል በየሰከንዱ 6.3 ሚሊዮን ጥያቄዎች እንደሚያስተናግድ አንድ ጥናት ያሳያል።

በአንድ ቀን ውስጥ ዘጠኝ ቢሊዮን ገደማ ጥያቄዎች ይቀርቡለታል ማለት ነው።

ዋነኛ በኢንተርኔት ላይ የሚደረገው እንቅስቃሴ መነሻ ጉግል ነው።

ጉግል መጀመሪያ ላይ ከሚያቀርባቸው አምስት ድረ ገጾች በዘለለ ብዙዎች አይመለከቱም።

የጉግል ተጠቃሚዎችን የዓይን እንቅስቃሴ መነሻ በማድረግ የተሠራ ጥናት እንደሚጠቁመው፣ በርካቶች ጉግል መነሻ ላይ ከሚሰጠው መረጃ አልፈው አይሄዱም።

በበርሊን፣ ጀርመን መምህርት የሆኑት ሲልቪያ ክኖብሎች-ዌስትሪክ እንደሚሉት፣ ጉግል የሚያቀርባቸው መረጃዎች ውስንነት የሰዎችን ምርጫ ይገድባል።

ይሄንን በተመለከተ ቢቢሲ ለጉግል ጥያቄ ቢያቀርብም ምላሽ አላገኘም።

ጉግል

‘ኦልሶአስክድ’ የተባለው ድርጅት ድረ ገጾች በጉግል ላይ የተሻለ ተነባቢነት እንዲኖራቸው ይሠራል።

የዚህ ድርጅት መሥራት ማርክ ዊልያምስ-ኩክ እንደሚሉት፣ መረጃ ማሰሻዎች ያላቸውን ውስንነት ተጠቃሚዎች አይገነዘቡም።

የጉግል ሠራተኞች ስለ መረጃ ማሰሻው የተለዋወጧቸውን መረጃዎች ይፋ በማድረግ ጉግልን ማመን እንደማይቻል በአሜሪካ ክስ ተመሥርቷል።

አንድ የጉግል መሃንዲስ “ሐሰተኛ ሰነዶችን እናቀርባለን” ሲል እአአ በ2016 የጻፈው እንደ ማስረጃ ቀርቧል።

“በቀን ውስጥ ቢሊዮን ጊዜ ሰዎች መረጃ እንድንሰጣቸው ይጠይቃሉ። እኛ የምንከተለው ሰዎችን ሳይሆን ሰነዶችን ነው። ጥሩ ምላሽ ያገኘ ሰነድ ጥሩ ነው ብለን እንወስዳለን። ጉግል የሚሠራው እንደዚያ ነው። በቀጣይ መረጃ የሚፈልግ ሰው የሚያገኘው መረጃ መነሻው ቀድሞ የታሰሰ መረጃ ነው” በማለትም የድርጅቱ ሠራተኞች ጽፈዋል።

ሰዎች በአንድ መረጃ ደስተኛ ሲሆኑ ጉግል መረጃውን ወደፊት ገጹ ይወስደዋል ማለት ነው።

የጉግል ቃል አቀባይ እንደሚሉት፣ ይህ በ2016 የወጣው መረጃ ማሻሻያ ተደርጎበታል።

ሆኖም ግን የጉግል መሠረታዊ አሠራር አልተለወጠም። ጉግል ሰዎች የሚወዱትን ለመገመት ይሞክራል። ያንንም መረጃ ያቀብላል።

አጥኚዎች እንደሚሉት፣ ጉግል ጥያቄ ሲጠየቅ ከጉዳዩ ጋር የተያያዙ ማስታወቂያዎችን ሊያቀርብም ይችላል።

ተጠቃሚዎች ጉግል ያለውን ውስንነት በመረዳት መረጃ የሚያገኙበትን መንገድ እንዲያስተካክሉ ይመክራሉ።

ጉግል ቴክኒካዊ ውስንነቶቹን ለመቅረፍ እንደሚሠራ ቃል አቀባዩ ይናገራሉ።

ጉግል ስለሚሰጣቸው መረጃዎች የተሻለ ግንዛቤ እንዲኖር በሚል ስለ መረጃዎች ማብራሪያ የሚገኝበት መንገድ አመቻችቷል።

ከላይ የተጠቀሱትን ሁለት ምሳሌዎች ብንወስድ፣ ጉግል ስለ ካማላ ሃሪስ እንዲሁም በቡና እና በደም ግፊት መካከል ስላለው ትስስር የሚሰጠው መረጃ ወደ ሌሎች ድረ ገጾች የሚመራ ብቻ ሳይሆን ለጥያቄዎቹ ጉግል ያለውን መልስ የሚያስቀምጥም ጭምር ነው።

ማርክ ዊልያምስ-ኩክ እንደሚሉት፣ ጉግል መረጃዎቹን በራሱ መስጠት መጀመሩ የተለየ አካሄድ ተደርጎ ይወሰዳል።

ጉግል መረጃ የሚሰጠው ወይም ምላሽ የሚሰጠው በየትኞቹ ሁኔታዎች ውስጥ እንደሆነ በግልጽ የተቀመጠ ነገር የለም።

ባለሙያዎች እንደሚሉት፣ በዓለማችን ከፍተኛ ገንዘብ የሚያገኘው የመረጃ ማሰሻ የሆነው ተቋም ጉግል፤ ሰዎች ማግኘት ያለባቸውን መረጃ መወሰኑ ለብዙዎች ምቾች የሚሰጥ ነገር አይደለም ሲሉ ተባባሪ ፕሮፌሰር ቫሮል ካይሀን ይናገራሉ።

“ይሄንን ማስተካከል ያለበት ጉግል ነው? ጉግልስ ይህንን ያስተካክላል ብለን ማመን እንችላለን? ሊስተካከል የሚችስ ነው? የሚሉትን ጥያቄዎች ለመመለስ ከባድ ነው። አንድ ማለት የምችለው ነገር ጉግል ችግሩን ለመፍታት እያደረገ ያለው በቂ አይደለም” ይላሉ።