እርዳታ ተቀብለው የሚመለሱ ፍልስጤማውያን

ከ 4 ሰአት በፊት

በጋዛ የሚገኙ ፍልስጤማውያን ሰኞ ዕለት በእስራኤል እና በአሜሪካ በሚደገፈው የጋዛ የሰብዓዊ ፋውንዴሽን ወደ ሚተዳደረው የእርዳታ ማከፋፈያ ማዕከላት ሲያመሩ በድጋሚ ተኩስ እንደተከፈተባቸው ተናገሩ።

የዓይን እማኞች ለመጀመሪያ ጊዜ በደቡብ ራፋህ በምትገኘው ታል አል ሱልጣን አካባቢ በሚገኘው የእርዳታ ማከፋፈያ ማዕከል አቅራቢያ በፍልስጤም ታጣቂዎች እንደተተኮሰባቸው ተናግረዋል።

እነዚሁ ግለሰቦች የእስራኤል ወታደሮችም እንደተኩሱባቸው አክለው ተናግረዋል።

በጋዛ ሃማስ የሚመራው የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ለዕርዳታ ማሰባሰብያ በተመረጡት አካባቢዎች ስድስት ሰዎች ሲገደሉ 99 ቆስለዋል ብሏል።

የእስራኤል መከላከከያ የወጡ መረጃዎችን እየተመለከተ መሆኑን አስታውቋል።

የጋዛ ሰብዓዊ ፋውንዴሽን የታል አል ሱልጣን የእርዳታ ማከፋፈያን ሰኞ አለመክፈቱን አስታውቆ፣ በሌሎች ሁለት ጣቢያዎች ግን እርዳታ በሚከፋፈልበት ወቅት ምንም ዓይነት ተኩስ እንዳልነበረ ተናግሯል።

ይህ የተፈጠረው የእስራኤል ጠቅላይ ሚንስትር ሃማስን የሚቃወሙት የፍልስጤም ጎሳዎችን በማስታጠቅ ላይ መሆናቸውን ካመኑ ከቀናት በኋላ ነው።

የጋዛ ሰብዓዊ ፌውንዴሽን በግንቦት 26 ዕርዳታ ማከፋፈል ከጀመረ ጀምሮ በየቀኑ ለማለት በሚያስችል ሁኔታ እስካሁን ከከፈታቸው አራት ማዕከላት በአንዱ ወይም በሌላ ጥቃቶች ተፈጽመዋል።

የእስራኤል ወታደራዊ ቀጠና አቋርጦ በሚያልፈው በራፋህ ታል አል ሱልጣን አካባቢ ወደሚገኝ አንድ ቦታ ሲቃረቡ በርካታ ፍልስጤማውያን ተገድለዋል።

ከዚህ ቀደም በደረሱት ጥቃቶች የእስራኤል ወታደሮች በተሰበሰበው ሕዝብ ላይ ተኩስ እንደከፈቱ እማኞች ተናግረዋል።

የእስራኤል ጦር ወታደሮች በቦታው በነበሩ ሰላማዊ ዜጎች ላይ መተኮሳቸውን ቢያስተባብልም፣ ወታደሮቹ ግን የማስጠንቀቂያ ጥይቱን ችላ ብለው ወደ እነሱ የቀረቡ ተጠርጣሪዎች ላይ መተኮሳቸውን ተናግረዋል።

በሰኞው ክስተት፣ በቦታው የነበሩ ሰዎች የፍልስጤም ታጣቂዎች እንዲሁም የእስራኤል ወታደሮችም በእነሱ ላይ እንደተኮሱና ተናግረዋል።

ታጣቂዎቹ በአካባቢው ከሚንቀሳቀሱ የእስራኤል ጦር ጋር በትብብር የሚሰሩ ይመስላሉ ያሉ ሲሆን ወደ እስራኤል ወታደራዊ ቀጠና አቅራብያም ሲንቀሳቀሱ ማየታቸውን ተናግረዋል።

አንድ የዓይን እማኝ ለቢቢሲ አረብኛ መካከለኛው ምሥራቅ ዴይሊ ፕሮግራም እንደገለፀው ከ ርዳታ ማከፋፈያው እርዳታ ለመቀበል በአካባቢው ሲደርሱ የሲቪል ልብስ ለብሰው ፊታቸው ሙሉ በሙሉ የሸፈኑ ወጣቶችን ማየታቸውን ተናግረዋል።

ሂሻም ሰኢድ ሳሌም “መጀመሪያ ላይ በሂደቱ ላይ እገዛ የሚያደርጉ የፍልስጤም ወጣቶች ሊሆኑ እንደሚችሉ አስበን ነበር፤ ነገርግን በድንገት ተኩስ ጀመሩ” ብሏል።

“እርዳታ ለመቀበል የቻሉት እንኳን ዒላማ ተደርገዉ በጥይት ተመትተዋል። እነዚህ አጥቂዎች እነማን እንደሆኑ እስካሁን አናውቅም። ሁሉንም ነገር ከኛ ወስደዋል፤ አንዳንዶች በግርግሩ ወቅት ሳይቀር ሰርቀውናል።”

መሀመድ ሳኮት የተባለ ሌላ ግለሰብ “ከኋላዬ ብዙ ወጣቶች በጥይት ተመትተው ተገድለዋል፤ ከሞት ለጥቂት ነው ያመለጥኩት። ጥይቶቹ ጭንቅላቴን ለጥቂት ነው የሳቱኝ” ብሏል።

አክሎም “በመጀመሪያ በሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚተኮሰው የእስራኤል ጦር ነበር። ዛሬ ግን ወንበዴዎችና ሚሊሻዎች እንዳሉ ስናውቅ አስደንግጦናል።”

በአቅራቢያው በምትገኘው ካን ዮኒስ ከተማ ውስጥ በሚገኘው ናስር ሆስፒታል፣ አንገቱ ላይ በጥይት ተመትቶ ክፉኛ ተጎድቶ ሕክምና እየተደረገለት የሚገኘው ሞሐመድ ካባጋ ለአሶሼትድ ፕሬስ ሲናገር “እያስተባበሩ የነበሩ ጭምብል ያደረጉ የታጠቁ ሰዎች በቀጥታ ወደ እኛ መተኮስ ጀመሩ” ብሏል።

“እርዳታ ልንቀበል ነው የሄድነው። ተሰለፉ አሉን። ሰልፋችንን ይዘን ባለበት ድንገት ተኩስ ጀመሩ። እኔ ቆሜ እያለሁ ጥይት ሲመታኝ ገረመኝ፤ አዞረኝና ወደቅሁ” ብሏል።

የእስራኤል መከላከያ ሠራዊት ዘገባዎቹን እየመረመረ መሆኑን ለቢቢሲ ተናግሯል።

የሰብዓዊ ፋውንዴሽን በመግለጫው እንዳስታወቀው ሰኞ እለት በጋዛ ሰርጥ በሳዑዲ አጎራባች ራፋህ እና ዋዲ በሚገኙ ሁለት ቦታዎች ማከፋፈያ መክፈቱን እና “በሁለቱም ቦታዎች የእርዳታ ስርጭት ያለ ምንም ችግር ተካሄዷል” ብሏል።

የ ጋዛ ሰብዓዊ ፋውንዴሽን ቃል አቀባይ ስለ ታል አል ሱልጣን ጥቃት በቢቢሲ ሲጠየቁ “በማከፋፈያዎቹ ዙሪያ ምንም ነገር የለም” ብለዋል።

ይኹን እንጂ ሰኞ ከሰአት በኋላ በቡድኑ የፌስቡክ ገጽ ላይ የታል አል ሱልጣን ማዕከል “በተፈጠረ ትርምስ” ምክንያት ተዘግቷል ሲል ለጥፏል።

የ ሰብዓዊ ፋውንዴሽኑ ጊዜያዊ ስራ አስፈፃሚ ጆን አክሬ “በማከፋፈያ ጣቢያዎች ላይ ምንም ዓይነት ጉዳት ሳይደርስ ወይም ምንም ዓይነት የጎላ ችግር ሳይፈጠር” ከ11 ሚሊየን በላይ ምግቦችን አከፋፍለናል ብለዋል።

የጋዛ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ሆስፒታሎች በተመሳሳይ ጊዜ ውስጥ በድምሩ 127 ሰዎች መሞታቸውን እና 1,287 የተጎዱ ሰዎችን “ከእርዳታ ማከፋፈያ ቦታዎች” ተቀብለናል ብሏል።

መስከረም 26 2016 ዓ.ም. በደቡባዊ እስራኤል ላይ በሃማስ የሚመራው ጥቃት 1,200 የሚጠጉ ሰዎች ገድሎ 251 ሰዎች ካገተ በኋላ የእስራኤል ጦር መጠነ ሰፊ ወታደራዊ ዘመቻ ጀምሯል።

ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በጋዛ ቢያንስ 54,927 ሰዎች ተገድለዋል ሲል የግዛቱ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አስታወቋል።