
ከ 5 ሰአት በፊት
በእንግሊዝ መምህራን አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ (AI) በመጠቀም ፈተናዎችን ማረም፣ ለወላጆች ደብዳቤ መፃፍ ይችላሉ ተባለ።
ይህን አዲስ የመንግሥት ውሳኔ የሚያስተዋውቅ የስልጠና መመርያን ቢቢሲ መመልከት ችሏል።
በእንግሊዝ ለሚገኙ ትምህርት ቤቶች በተሰራጨው በዚህ መመርያ ላይ መምህራን ቴክኖሎጂውን ተጠቅመው “የተለመዱ ተግባራትን ለማገዝ” እንደሚችሉ እና በምትኩ “ጥራት ላይ እና ከተማሪዎች ጋር የሚያሳልፉት ጊዜ” ላይ ማተኮር ይችላሉ ይላል።
መምህራን የሰው ሰራሽ አስተውሎት አጠቃቀማቸው ላይ ግልጽ መሆን አለባቸው ያለው ይህ መመርያ፣ ሁል ጊዜም ውጤቱን ዳግም ማረጋገጥ እንደሚያስፈልጋቸው የትምህርት ሚኒስቴር አስታውቋል።
የትምህርት ቤቶች እና ኮሌጆች አመራሮች ማኅበር በበኩሉ ውሳኔው “ለገጽ ለገጽ ማስተማር ነጻ ጊዜ እንዲኖር ያደርጋል” ቢልም አሁን ግን መፈታት ያለበት “ትልቅ ጉዳይ” አለ ብሏል።
በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ላይ ፈቃድ ያለው ቢሲኤስ ውሳኔውን “ጠቃሚ እርምጃ” ሲል አድንቆ ነገር ግን መምህራን “ለወላጆች የቱ ጋር ሰው ሰራሽ አስተውሎት እንደተጠቀሙ መናገር እንደሚኖርባቸው ግልጽ መመርያ ያስፈልጋቸዋል” ብሏል።
መምህራን እና ተማሪዎች የሰው ሰራሽ አስተውሎትን መሞከር የጀመሩ ሲሆን ከዚህ ቀደም ትምህርት ሚኒስቴርም በመምህራን ዘንድ ጥቅም ላይ መዋሉን እንደሚደግፍ ገልጾ ነበር።
ሚኒስቴሩ የሰው ሰራሽ አስተውሎት እንደ አጫጭር መልስ የሚሰጥባቸው ጥያቄዎችን ወይንም የቤት ስራዎችን የመሳሰሉ “ቀላል መልመጃዎች” ለማረም ብቻ ጥቅም ላይ መዋል እንደሚችሉ ገልጾ ውጤቱን መምህራን ድጋሚ ማረጋገጥ እንደሚኖርባቸው አስታውቋል።
መምህራን ለወላጆች “ዘወትር” በሚጽፏቸው ደብዳቤዎችንም ኤአይ መጠቀም እንደሚችሉ ፈቃድ ሰጥቷል።
የስልጠናው አንደኛው ክፍል ለምሳሌ የጸጉር ቅማል መከሰትን በተመለከተ ደብዳቤ ለመጻፍ እንዴት ጥቅም ላይ እንደሚውል ያሳያል።
የትምህርት ሚኒስቴር መመሪያ ትምህርት ቤቶች በ ኤአይ ላይ ግልጽ ፖሊሲዎች ሊኖራቸው ይገባል ይላል።
መምህራን እና ተማሪዎች ሊጠቀሙበት የሚችሉበት እና የማይችሉበትን ጊዜ፣ እና ትክክለኛነቱ እንደገና በመምህራኑ ፍተሻ ማድረግ ተማሪዎች መኮረጅ አለመኮረጃቸውን ለመለየት እንደ መልካም መንገድ ተጠቁመዋል።
በተጨማሪም የተፈቀደላቸው መሳሪያዎች ብቻ ጥቅም ላይ መዋል አለባቸው ያለ ሲሆን፣ ተማሪዎች ስለ ዲፕፌክ እና ሌሎች የተሳሳቱ መረጃዎችን እንዲያውቁ መማር አለባቸው ይላል።
የትምህርት ሚኒስትሩ ብሪጅት ፊሊፕሰን መመሪያው “የሥራ ጫናዎችን ለመቀነስ” ያለመ ነው ብለዋል።