ከወገባቸው በታች የሚታዩ የሚራመዱ ሰዎች

ከ 5 ሰአት በፊት

የደቡብ ኮሪያ ፍርድ ቤት አንዲት ሴት የባልደረባዋን ሱሪ እና ሙታንታ በአጋጣሚ በባልደረቦቻቸው ፊት በማውለቋ ፆታዊ በደል በመፈጸም ቅጣት እንደጣለባት የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

ከ 2,100 የአሜሪካን ዶላር ቅጣት በተጨማሪ፣ በ50ዎቹ ዕድሜ ውስጥ የምትገኘው ሴት የስምንት ሰዓታት የጾታዊ ጥቃትን መከላከል ትምህርት እንድትወስድ ተወስኗል።

ክስተቱ ባለፈው ጥቅምት ወር በሰሜን ምሥራቅ በጋንግዎን ግዛት በሚገኝ ሬስቶራንት ኩሽና ውስጥ ተከስቷል ተብሏል።

የቹንቸዮን አውራጃ ፍርድ ቤት ቅዳሜ የሰጠው ብይን ሴትየዋ ድርጊቱ በ20ዎቹ ዕድሜው ውስጥ ባለው የሥራ ባልደረባዋ ላይ ጉዳት የማያስከትል ቧልት ነው ስትል ያቀረበችውን አቤቱታ ውድቅ አድርጎታል።

ፍርድ ቤቱ ግን ከዚህ ቀደም ምንም ዓይነት የወንጀል ጥፋት የሌለባት መሆኑን መጸጸቷን ግምት ውስጥ ማስገባቱን ገልጿል።

ዳኛው ሴትዮዋም የሥራ ባለደረባዋን እና ወላጆቹን ተንበርክካ ይቅርታ ጠይቃለች ብለዋል።

በቾሱን ዴይሊ በጉዳዩ ላይ ባቀረበው ዘገባ ስር አንድ አስተያየት “ለቀላል ቀልዶች ከባድ ቅጣት የተጣለባት ይመስላል” ብሏል።

ሌላ አንባቢ ግን ” ቅጣቱ ጨርሶ ከመጠን በላይ አይደለም። ለምን እንደዚህ አይነት ቀልድ መቀለድ አስፈለገ? ይህ ቀልድ ይመስላል?” ሲል ጠይቋል።

ሙታንታን ጨምሮ የአንድን ሰው ሱሪ ማውለቅ ወይም ዝቅ ማድረግ ብዙውን ጊዜ የጥቃት ዓይነት ነው ተብሎ ቢተችም እንደ የተለመደ ተግባራዊ ቀልድ ይታያል።

ይህ ድርጊት ሌሎች ሰዎችን ችግርም ውስጥ ከትቷል።

እንደ አውሮፓውያኑ በ2019 የደቡብ ኮሪያ ኦሊምፒክ የአጭር ርቀት ስኬቲንግ ሻምፒዮን ሊም ሀዮ-ጁን የአንድ ወንድ ጓደኛውን ሱሪ ከሌሎች ሴት ስኬተሮች ፊት ዝቅቀ ካደረገ በኋላ ለአንድ ዓመት ታግዷል።

እአአ በ 2021 በሰሜን ጄኦላ ግዛት የሚገኙ የአንደኛ ደረጃ ተማሪዎች የተጎጂው እናት ለፖሊስ የልጇን ሱሪ እንዳወለቀቡት ከተናገረች በኋላ፤ በዕድሜ ከእነሱ የሚያንስን ወንድ ልጅ መጫወቻ ቦታ ላይ በማጥቃት ምርመራ ተደርጎባቸዋል።