
ከ 4 ሰአት በፊት
ለክትባት ቀና ልብ የሌላቸው የዩናይትድ ስቴትስ የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ሮበርት ኤፍ ኬኔዲ ጁኒየር የበሽታ መከላከያ ክትባት ላይ ይፋዊ የመንግሥት ምክረ ሃሳቦችን የሚያቀርበውን ኮሚቴ 17 አባላት በሙሉ አባረሩ።
ውሳኔያቸውን በዎል ስትሪት ጆርናል ላይ በወጣው ኤዲቶሪያል ላይ ያስታወቁት ኬኔዲ Advisory Committee on Immunization Practices (Acip) የተሰኘው ኮሚቴ ላይ ያሉ የጥቅም ግጭቶች በክትባት ላይ ያለውን እምነት ለመሸርሸር ተጠያቂ ነው ብለዋል።
ኬኔዲ “የአሜሪካ ሕዝብ በተቻለ መጠን ደህንነቱ የተጠበቀ ክትባቶችን ማግኘቱን ማረጋገጥ” እንደሚፈልጉ ተናግረዋል።
ዶክተሮች እና የጤና ባለሙያዎች ኬኔዲ ለብዙ ክትባቶች ደህንነት እና ውጤታማነት ላያ ያላቸውን የቆየ አቋም ሲተቹ ቆይተዋል። ኬኒዲ ከሹመታቸው ማግስት በአሜሪካ ሴኔት ላይ ቀርበው አቋማቸውን እንደማይተዉ ተናግረዋል።
ሰኞ እለት ሁሉንም የኮሚቴውን አባላት “ጡረታ ማስወጣታቸውን” ገልጸዋል።
ከ17ቱ አባላት መካከል ስምንቱ የተሾሙት በጥር 2025፣ በፕሬዚደንት ባይደን የስልጣን ዘመን የመጨረሻ ቀናት ነው።
አብዛኛዎቹ አባላት ከዋና ዋና የዩኒቨርሲቲ ሕክምና ማዕከላት ጋር የተቆራኙ ዶክተሮች እና ባለሙያዎች ናቸው።
ኬኔዲ “ኮሚቴው ቀጣይነት ባለው የጥቅም ግጭት ተይዟል፤ እንዲሁም ለማንኛውም ክትባት ማህተም የሚመታ ሆኗል” ሲሉ ጽፈዋል።
የጤና ባለሥልጣናት እና የመድኃኒት ኩባንያዎችን “ሕዝብ አመኔታ ማጣት” ተጠያቂ ያደረጉ ሲሆን፣ አንዳንዶች “በሀሰተኛ መረጃ ወይም ፀረ ሳይንስ አመለካከቶችን” ለማብራራት እንደሚሞክሩ ተናግረዋል።
በኤዲቶሪያሉ ውስጥ፣ ኬኔዲ እአአ ከ1990ዎቹ እና 2000ዎቹ ምሳሌዎችን በመጥቀስ የጥቅም ግጭቶች እንደቀጠሉ ክስ አቅርበዋል።
በዎል ስትሪት ጆርናል ላይ “አብዛኞቹ የኮሚቴው አባላት ከፋርማሲዩቲካል ኩባንያዎች፣ እነዚያን የግብይት ክትባቶች ጨምሮ ከፍተኛ የገንዘብ ድጋፍ አግኝተዋል” ሲሉ ጽፈዋል።
እርምጃው ኬኔዲ በሴኔት ከሰጡት ማረጋገጫ ጋር የሚቃረን ይመስላል።
የሕክምና ባለሙያ የሆኑት በሉዊዚያና የሪፐብሊካን ሴናተር ቢል ካሲዲ፣ የጤና ሚኒስትሩ ኮሚቴው “ያለ ለውጦች” እንደሚቆይ ቃል መግባታቸውን ተናግረዋል።
ሰኞ ላይ ካሲዲ በኤክስ ገጻቸው “በእርግጥ አሁን ፍራቻው ኮሚቴው ከጥርጣሬ በስተቀር ስለ ክትባቶች ምንም በማያውቁ ሰዎች ይሞላል [የሚል ነው]” ሲሉ ጽፈዋል።
“አሁን ከኬኔዲ ጋር ተነጋግሬያለሁ፣ እናም ይህ እንዳይሆን ለማረጋገጥ ከእሱ ጋር መነጋገራችንን እቀጥላለሁ።”
የኮሚቴው አባላት የጥቅም ግጭቶችን ማሳወቅ እና ግጭት በሚፈጠርባቸው ውሳኔዎች ላይ ድምጽ ከመስጠት መቆጠብ ይጠበቅባቸዋል።
ኬኔዲ “ችግሩ የግድ የኮሚቴው አባላት ሙሰኞች መሆናቸው አይደለም” ሲሉ ጽፈዋል። “ብዙውን ዓላማ የሕዝብን ጥቅም በተረዱት መሰረት ማገልገል ነው።”
“ችግሩ በኢንዱስትሪ የተደገፈ ማበረታቻ እና ጠባብ ኢንዱስትሪን በመደገፍ የሚያስፈጽም ሥርዓት ውስጥ መዘፈቃቸው ነው”
የአሜሪካ ዶክተሮች የሙያ ማኅበር የሆነው የአሜሪካ ሜዲካል አሶሴሽን ፕሬዝዳንት ዶክተር ብሩስ ስኮት በጅምላ ከስራ መባረር “ስፍር ቁጥር የሌላቸውን ሕይወት መታደግ የቻለን ግልፅ ሂደት ያሰናክላል” ብለዋል።
“በቀጠለው የኩፍኝ ወረርሽኝ እና መደበኛ የህፃናት የክትባት መጠን እየቀነሰ በመጣበት ጊዜ የተላለፈው ይህ እርምጃ በክትባት ሊከላከሉ የሚችሉ ሕመሞች መስፋፋትን የበለጠ ያቀጣጥላል” ብለዋል ዶክተር ስኮት በሰጡት መግለጫ።
ኬኔዲ የቦርድ አባላትን ለመተካት ማንን እንደሚሾሙ አልተናገሩም። ኮሚቴው ከሰኔ 25 ጀምሮ የታቀደ ስብሰባ አለው፣በዚህም አባላት ለኮቪድ፣ ጉንፋን፣ ማኒንኮኮካል በሽታ፣ አርኤስቪ እና ሌሎች በሽታዎች በሚሰጡ ክትባቶችን ዙሪያ ለሚቀርቡ ምክረ ሃሳቦች ላይ ድምጽ ለመስጠት ቀጠሮ ተይዞላቸዋል።
ቢቢሲ የአሜሪካ የጤና እና የሰብዓዊ አገልግሎት ዲፓርትመንት እና የኮሚቴውን ሊቀመንበር ዶክተር ሄለን ኬፕ ታልቦትን አስተያየት እንዲሰጡ ጠይቆ ነበር።