የተቃውሞ ሠልፈኛ በወታደሮች ፊት

ከ 7 ሰአት በፊት

ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ ሰኞ ዕለት አራተኛ ቀኑን በያዘው የሎስ አንጀለስ ተቃውሞ ተጨማሪ 2000 የብሔራዊ ዘብ አላት ማሰማራታቸውን ባለስልጣናት ገለፁ።

ፔንታጎን ዶናልድ ትራምፕ ተጨማሪ 2000 የብሔራዊ ዘብ እና 700 የባሕር ኃይል አባላትን የፌደራል መንግሥቱ የተቃውሞ ሠልፉን ለመቆጣጠር እየወሰደ ያለውን እርምጃ ለማገዝ እንዲሰማሩ ማዘዛቸውን አረጋግጧል።

በሎስ አንጀለስ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ስደተኞችን ከአገር ለማባረር የያዙትን ፖሊሲ በመቃወም የተቀጣጠለው ተቃውሞ አራተኛ ቀኑን ይዟል።

ትራምፕ ከዚህ ቀደም ያሰማሯቸው 2000 የብሔራዊ ዘብ አባላት የፖለቲካ ውጥረት የፈጠሩ ሲሆን የካሊፎርኒያ አስተዳዳሪ ጋቪን ኒውስኮም እና የኤልኤ ከንቲባ ካረን ባስ የአካባቢ ፖሊስ ተቃውሞ ሠልፈኞቹን መቆጣጠር ይችላል ብለው ተከራክረዋል።

የአሜሪካ ወታደሮች በአገር ውስጥ ሕግ ማስከበር ውስጥ ሲሳተፉ ማየት የተለመደ አይደለም።

ዶናልድ ትራምፕ ስደተኞችን ከአገር የማባረር ፖሊስን በመቃወም ለተቃውሞ ጎዳና የወጡ ሠልፈኞችን ለመቆጣጣር የባሕር ኃይል አባላትን እንዲሁም ተጨማሪ የብሔራዊ ዘብ ወታደሮችን ለማሰማራት መወሰኑ ውጥረት ፈጥሯል።

በደቡብ ካሊፎርኒያ የአሜሪካ ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ ስደተኞችን ከአገር ለማባረር የያዙትን ፖሊሲ በመቃወም የተቀጣጠለው የሎስ አንጀለሱ ፍጥጫ ውጥረት እየጨመረ ነው።

የትራምፕ አስተዳደር በአገሪቱ በሕገ ወጥ መንገድ የሚኖሩ ስደተኞችን ከአገር ለማባረር ከወሰዳቸው እርምጃዎች ሁሉ ይህ ጠንከር ያለው ነው።

የባህር ኃይል አባላት እንደሚሰማሩ ይፋ የሆነው በተቃውሞው አራተኛ ቀን ላይ ነው።

ሰኞ አመሻሽ ላይ ፖሊስ በሎስ አንጀለስ መሃል በሚገኘው ከፌዴራል የስደተኞች ማቆያ ማዕከል ውጭ የተሰበሰቡ በመቶዎች የሚቆጠሩ ተቃዋሚዎችን መበተን ጀምሯል።

የብሔራዊ ዘብ አባላት እስረኞች ከሕንጻው እንዳይወጡ ለማድረግ ተጠጋግተው በመቆም ተከላክለው ነበር።

የሎስ አንጀለስ ፖሊስ በበኩሉ ተቃዋሚ ሠልፈኞች ከአካባቢው እንዲሄዱ ለማድረግ መግፋት የጀመረ ሲሆን “አነስተኛ ጥቃት አድራሽ” የሆኑ ጥይቶችን ተኩሷል።

ፖሊስ ከባለፈው ሳምንት አርብ ጀምሮ ተመሳሳይ ዘዴዎችን ተጠቅሟል።

የኤልኤ ፖሊስ ሰኞ ከሰዓት በኋላ አንዳንድ ተቃዋሚዎች እቃዎችን ወደ ፀጥታ አካላት መወርወር እንደጀመሩ እና ፖሊስ አስለቃሽ ጋዝ እና የጎማ ጥይቶች እንዲጠቀም እንደተፈቀደለት በኤክስ ገፁ ላይ ለጥፎ ነበር።

ካሊፎርኒያ የፌደራል ሕግን እና የግዛት ሉዓላዊነትን የሚጥስ መሆኑን በመግለጽ የብሄራዊ ጥበቃ እና የባህር ኃይል ወታደሮችን ለማገድ ሰኞ ዕለት የትራምፕ አስተዳደርን ከስሳለች።

የአሜሪካ የባህር ኃይል ወታደሮች በአገር ውስጥ የሚሰማሩት እንደ አደገኛ አውሎ ንፋስ እና የሽብር ጥቃቶች ሲደርሱ ነው።

የአሜሪካ ወታደሮችን ለአገር ውስጥ ሥርዓት ማስከበር ማሰማራት እጅግ በጣም አልፎ አልፎ የሚወሰድ እርምጃ ነው።

ፔንታጎን ሰኞ 2,000 የብሔራዊ ጥበቃ ጦር ሠራዊት አባላት እንዲሰማሩ መጠየቁን አረጋግጦ ይህም አሁን በሎስ አንጀለስ የተሰማሩ ወታደሮቸን ቁጥር ወደ 4,000 ከፍ ያደርገዋል።

ትራምፕ ሰኞ ዕለት አመፁ ከቁጥጥር ውጭ እንዳይሆን ለመከላከል የወታደሮችን ቁጥር ከመጨመር ሌላ ምንም አማራጭ እንደሌላቸው ተናግረው ነበር።

በሎስ አንጀለስ ጎዳናዎች የተሰማሩ ፖሊሶች

ትራምፕ የካሊፎርኒያ አስተዳዳሪ ጋቪን ኒውሶም አስተዳደሩ ሰነድ አልባ ስደተኞችን ከአገር ለማስወጣት የሚያወስዳቸውን እርምጃዎችን ለማስተጓጎል ሲሞክሩ ሊታሰሩ ይገባል ሲሉ ቶም ሆማን ያቀረቡትን ሀሳብ እንደሚደግፉ ተናግረዋል።

ትራምፕ ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት “ቶምን ብሆን አደርገው ነበር። በጣም ጥሩ [እርምጃ] ይመስለኛል” ብለዋል።

ዴሞክራቶች ትራምፕ ተቃውሞውን ለመቆጣጠር ወታደራዊ ኃይል ለማሰማራት መወሰናቸው የፕሬዚዳንቱን ስልጣን አላግባብ መጠቀም ነው ሲሉ የካሊፎርኒያ ግዛት ደግሞ ሕገ ወጥ ነው ሲል ተቃውሟል።

የኒውሶም የፕሬስ ቢሮ በኤክስ ገፁ ላይ “የቁጥሩ መጨመር ሙሉ በሙሉ ተገቢ ያልሆነ፣ አላስፈላጊ እና ከዚህ በፊት ታይቶ የማይታወቅ ነው” ብሏል።

በእስካሁኑ ሕዝባዊ ተቃውሞዎች በእሁድ አመሻሽ ላይ የተቃጠሉትን ተሽከርካሪዎችን ጨምሮ ጥቂት ሰዎች ለእስር ሲዳረጉ፣ በንብረት ላይም ጉዳት ደርሷል።

የሎስ አንጀለስ ፖሊስ ቅዳሜ እና እሁድ አምስት አባላቱ ላይ ቀላል ጉዳት እንደደረሰባቸው ገልጿል።

ሰኞ ዕለት ፖሊስ ጣልቃ ከመግባቱ በፊት በመቶዎች የሚቆጠሩ ተቃዋሚዎች ሰነድ አልባ ስደተኞች ከታሰሩበት የሎስ አንጀለስ ፌደራል እስር ቤት ውጭ በመሆን “ሁሉንም ነፃ ይውጡ” እያሉ መፈክር አሰምተዋል።

የትራምፕ አስተዳደር የፕሬዝዳንት ጆ ባይደን አስተዳደር ብዙ ስደተኞች ወደ አገሪቱ እንዲገቡ መፍቀዱን እና እንደ ሎስ አንጀለስ ያሉ በዲሞክራቶች የሚተዳደሩ ከተሞች ደግሞ እነሱን ለማስወጣት የሚደረገውን ጥረት ለማስተጓጎል አላግባብ ጣልቃ እየገቡ ነው ብሏል።

ትራምፕ በሕገ ወጥ መንገድ በአገሪቱ የሚኖሩ ሰዎችን ለማስወጣት እንዲሁም የአሜሪካ እና የሜክሲኮ ድንበርን ለመዝጋት ቃል በመግባት ቢያንስ በቀን 3,000 ሰነድ አልባ ሰዎችን በቁጥጥር ስር የማዋል ግብ አስቀምጠዋል።