
ከ 7 ሰአት በፊት
ውሃ ለሕይወት አስፈላጊ ነው። በርካታ ዓለም አቀፍ መመሪያዎች አንድ ሴት በቀን ሁለት ሊትር፣ ወንድ ደግሞ 2.5 ሊትር ውሃ ቢጠጣ ለጤና መልካም መሆኑን ይመክራሉ።
ሳይንቲስቶች ግን የምንጠጣው ውሃ በተለያየ መንገድ የሚፈለገውን ያህል ላይሆን ይችላል ይላሉ።
በቂ ውሃ አለመጠጣት ለድርቀት ያጋልጣል። ከዚያ በተቃራኒ ደግሞ ብዙ ውሃ መጠጣትም አደገኛ ነው።
ውሃ የሰውነታችንን ክብደት 60 በመቶ ይይዛል። ሴሎቻችን፣ የአካል ብልቶቻችን፣ ደማችን እንዲሁም በሰውነታችን የተለያዩ ክፍሎች ውስጥ ውሃ ይገኛል።
በስኮትላንድ የስተርሊንግ ዩኒቨርሲቲ የውሃ ባለሙያ የሆኑት ዶ/ር ኒዲያ ሮድሪግዝ ሳንቼዝ “ውሃ ንጥረ ነገር አለው” ይላሉ።
“ፕሮቲን፣ ቫይታሚን፣ ካርቦሃይድሬት እና ፋይበር ላይ እናተኩራለን። ውሃን በሕይወታችን ውስጥ እንደ ጠቃሚ ንጥረ ነገር አድርገን አናስብም።”
ውሃ በሁሉም የሰውነታችን ተግባራት ውስጥ ወሳኝ ሚና ይጫወታል። የሃርቫርድ የሕክምና ትምህርት ቤት የውሃን አንዳንድ ቁልፍ ሚናዎች እንደሚከተለው ዘርዝሯል።
በሰውነታችን ውስጥ የውሃ ወሳኝ ሚና
- ንጥረ-ነገሮችን እና ኦክስጂንን ወደ ሴሎች ማጓጓዝ
- ከሽንት ከረጢት ውስጥ ባክቴሪያዎችን ማስወገድ
- የምግብ መፈጨትን መርዳት
- የሆድ ድርቀትን መከላከል
- የደም ግፊትን መደበኛ ማድረግ
- መገጣጠሚያዎችን ማለስለስ
- የአካል ብልቶችን እና ጡንቻዎችን መከላከል
- የሰውነት ሙቀትን መቆጣጠር
- የኤሌክትሮላይት (ሶዲየም) ሚዛንን መጠበቅ

በቂ ውሃ ካልጠጣን ምን ይከሰታል?
ሰውነታችን በላብ፣ በሽንት እና አልፎ ተርፎም በምንተነፍስበት ወቅት ውሃን ያስወግዳል።
ሰውነታችን በአግባቡ እንዲሠራ ለማድረግ ይህ የሚወገድ ፈሳሽ መተካት አለበት። ይህም የሰውነት ውሃ ሚዛንን መጠበቅ በመባል ይታወቃል።
ሰውነታችን ከሚወስደው በላይ ውሃ ሲያስወግድ የሰውነት ድርቀት ሊከሰት ይችላል። ይህም ወደ ከባድ የጤና ችግሮች ሊያመራ ይችላል።
የድርቀት ምልክቶች፦
- ደማቅ ቢጫ እና በጣም የሚሸት ሽንት
- ከተለመደው በታች መሽናት
- የማዞር ስሜት
- ድካም
- የአፍ፣ የከንፈር እና የምላስ መድረቅ
- የዓይን መሰርጎድ
የዓለም ጤና ድርጅት ውሃ ሳንጠጣ ለረዥም ጊዜ የምንቆይ ከሆነ ግራ የመጋባት ስሜት እንደሚፈጠር፣ የአካል ክፍሎች ሥራ ማቆም እንዲሁም ፈጣን የልብ ምት ሊያስከትል እንደሚችል ይገልጻል።

ከመጠን በላይ ውሃ መጠጣት አደገኛ ሊሆን ይችላል?
አዎ፤ ውጤቱም ከባድ ሊሆን ይችላል።
በአጭር ጊዜ ውስጥ ከመጠን በላይ ውሃ መጠጣት ሃይፖናትሬሚያ (hyponatraemia) ሊያስከትል ይችላል። ይህም በውሃ መስከር በመባልም ይታወቃል።
ይህ የሚሆነው በደማችን ውስጥ ያለው የሶዲየም መጠን በከፍተኛ ሁኔታ ሲቀንስ፣ የሰውነታችን ሴሎች እንዲያብጡ ስለሚያደርግ ነው።
የሃይፖናትሬሚያ ምልክቶች፦
- ማቅለሽለሽ እና ማስመለስ
- ራስ ምታት
- ግራ መጋባት
- አቅም ማጣት፣ ድብታ እና ድካም
- አለመረጋጋት እና ብስጭት
- የጡንቻ መዛል፣ ቁርጠት ወይም ቁርጥማት
- ምንቀጥቀጥ
- የከፋ ሲሆን ራስን መሳት

እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2018 ጆሃና ፔሪ ከልጇ እና ከአማችዋ ጋር በለንደን ማራቶን ለመሳተፍ ልምምድ እያደረገች ነበር። ቀኑ በጣም ሞቃታማ በመሆኑ በጎ ፈቃደኞች ለሯጮች የሚሰጡትን ውሃ እየተቀበለች በተደጋጋሚ ስትጠጣ ነበር።
ለቢቢሲ ‘ዘ ፉድ ቼይን’ ፕሮግራም “የመጨረሻው የማስታውሰው ነገር የግማሽ ማራቶን ምልክቱን ነበር” ስትል ተናግራለች።
ጆሃና በፅኑ ሕክምና ውስጥ ለሦስት ቀናት ካሳለፈች በኋላ ነው የነቃችው።
በባለቤቷ የተቀረጸ ተንቀሳቃሽ ምሥል የውድድሩን የመጨረሻ መስመር አልፋ ስትገባ ቢያሳያትም እርሷ ግን ምንም የምታስታውሰው ነገር አልነበረም።
“የትዳር አጋሬ እና አንዳንድ ጓደኞቼ እዚያ ነበሩ። እጃቸው እያውለበለቡልኝ ነበር፤ እግሮቼ ከዱኝ። ወደ ቤት ከተመለስን በኋላ በጣም ታመምኩ፤ እናም ራሴን ሳትኩ” ስትል ታስታውሳለች።
“በጣም ብዙ ውሃ ስለጠጣሁ፣ አካሌ በአግባቡ ለመሥራት የሚያስፈልገውን ጨው እና ሌሎች ንጥረ ነገሮች ከውስጤ አጥቤ ነበር ያስወጣሁት።”
ጆሃና ያጋጠማት ከተገቢው በላይ ፈሳሽ ስንወስድ ምን እንደሚፈጠር አጉልቶ ያሳያል።
ፈሳሽ ነገሮች በፍጥነት ወደ ደም ውስጥ ይገባሉ። የተወሰደው ትርፍ ፈሳሽ በኩላሊቶቻችን በኩል ተጣርቶ በሽንት መልክ ይወገዳል።
ነገር ግን ኩላሊታችን በሰዓት አንድ ሊትር ፈሳሽ ብቻ ነው ማጣራት የሚችለው።

ሰውነታችን ምን ያህል ውሃ ያስፈልገዋል?
የጤና ባለሙያዎች ጤናን በአግባቡ ለመጠበቅ በቀን ከስድስት እስከ ስምንት ብርጭቆ ውሃ መጠጣት በቂ መሆኑን ይመክራሉ።
የአውሮፓ የምግብ ደኅንነት ባለሥልጣን ለሴቶች ሁለት ሊትር እና ለወንዶች ሁለት ሊትር ተኩል መጠጣት በቂ መሆኑን ይመክራል። ይህ ግን ከመጠጥ ብቻ ሳይሆን ምግብን ጨምሮ ከሁሉም ምንጮች የሚገኝን ውሃ ያጠቃልላል ።
አብዛኞቹ ምግቦቻችን ፍራፍሬ፣ አትክልት፣ ሩዝ እና ለውዝን ጨምሮ ውሃ ይይዛሉ። ለምሳሌ ሀብሀብ 92 በመቶ ውሃ ነው።
በስኮትላንድ የሚገኘው የአበርዲን ዩኒቨርሲቲ ባልደረባ የሆኑት ፕሮፌሰር ጆን ስፒክማን በ23 አገራት የሚገኙ ከ5,000 በላይ ሰዎች የውሃ አወሳሰድ መጠንን የተከታተለው ዓለም አቀፍ ጥናት አካል ነበሩ።
“ዕድሜያቸው በሃያ እና ስልሳ መካከል የሚገኙ ወንዶች ምናልባት በቀን 1.8 ሊትር ያህል ውሃ ያስፈልጋቸዋል። በተመሳሳይ የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ሴቶች ደግሞ ከ1.5 እስከ 1.6 ሊትር ያስፈልጋቸዋል። ዕድሜያቸው 85 ገደማ የሆናቸው ደግሞ በቀን አንድ ሊትር ብቻ ያስፈልጋቸዋል” በማለት ፕሮፌሰር ስፒክማን ያብራራሉ።
ነገር ግን አንድ ግለሰብ የሚያስፈልገው የውሃ መጠን እንደ የሰውነት ክብደቱ፣ እንደሚሠራው የአካል ብቃት እንቅስቃሴ መጠን፣ ዕድሜ፣ ፆታ እና የአካባቢ ሁኔታ ይወሰናል።
አክለውም “አንድ ሰው ምን ያህል የውሃ መጠን ያስፍልገዋል የሚለው የሚወሰነው ምን ያህል ግዙፍ ነው በሚለው ነው” ብለዋል።
“ሞቃታማ እና እርጥበት ባለበት ቦታ የሚኖሩ ከሆነ የውሃ ፍላጎትዎ በብርድ እና በደረቅ ቦታ ውስጥ ከሚኖር ሰው በጣም ከፍ ያለ ይሆናል።”
አንድ ሰው ውሃ ለመጠጣት የሚያሳያው ተፈጥሯዊ ምልክት መጠማት ነው። የሽንት ቀለም ሌላው ጥሩ በቂ ውሃ ማግኘታችን እና አለማግኘታችንን ጠቋሚ ነው።
ፈዛዛ ቢጫ በቂ ውሃ ማግኘታችንን ሲያመለክት፣ ደማቅ ቢጫ ደግሞ የውሃ እጥረት በሰውነታችን ውስጥ መኖሩን ያመለክታል።
ከዚህ በተጨማሪ ማስመለስ ወይም ተቅማጥ ካለዎት ብዙ ፈሳሽ መጠጣት ይኖርብዎታል።