
ከ 3 ሰአት በፊት
ከትግራይ ኃይሎች በመለየት ከአፋር ክልል ጋር በሚዋሰን አካባቢ የራሳቸውን ሠራዊት እየገነቡ መሆናቸውን የሚናገሩት ብርጋዴር ጄነራል ገብረ እግዚአብሄር በየነ (ወዲ አንጥሩ) “ከፓርቲ [ህወሓት] ነጻ የሆነ ኃይል” ለመፍጠር ወደ ነጻ መሬት መውረዳቸውን ተናገሩ።
ጄነራሉ ከቢቢሲ ትግርኛ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ “አዲስ ነገር ለመፍጠር” ወደ በረሃ መውደረዳቸውን ሲያብራሩ “ከፓርቲ ነጻ የሆነ ኃይል ለመፍጠር፣. . . ፓርቲ የማያዝዘው ሠራዊት ለመፍጠር ” እየተንቀሳቀሱ መሆኑን ተናግረዋል።
ህወሓትን የመጣል ዓላማ እንዳላቸው የተጠየቁት ጄነራሉ “እኛ የምንሠራው ፓርቲ፣ እኛ የምናቋቁመው ወታደራዊ መንግሥት የለም” ብለዋል።
በአፋር እና በትግራይ ክልሎች ውስጥ አራት ክፍለ ጦር ያለው ሠራዊት ማደራጀታቸውን የሚናገሩት ጄነራል ገብረ እግዚአብሄር በየነ፣ ከትግራይ ሠራዊት አመራሮች ጋር የተለያዩት ከጥር 15/20017 ዓ.ም. ጀምሮ መሆኑን ይናገራሉ።
የትግራይ ሠራዊት ከፍተኛ አመራሮች ጥር 15 ተሰብስበው በአቶ ጌታቸው ረዳ የሚመራውን ጊዜያዊ አስተዳደር ሲያወግዙ፣ ተቃውመው ስብሰባውን ረግጠው ከወጡ አመራሮች መካከል አንዱ ጄነራል ገብረ እግዚአብሄር በየነ ናቸው።
ይህንንም ተከትሎ የሠራዊቱ አመራሮች ጄነራል ገብረ እግዚአብሄር በየነን እና ሌሎች የሠራዊቱን ውሳኔ የተቃወሙትን ማገዳቸው ይታወሳል።
“አሁን በትግል ላይ ነን ያረጀነውም በትግል ነው” ያሉት ጄነራል ገብረ እግዚአብሄር “ከፓርቲ ጋር ተጣብቆ ማህተም የሚነጥቅ፣ ከፓርቲ ጋር ተጣብቆ የሚሾም እና የሚሽር ኃይል ለወጣቱ ትውልድ ትተን መሄድ አንፈልግም። ወገንተኛ ያልሆነ ፍትሃዊ ኃይል ለመፍጠር እንጂ፣ የሆነ ፓርቲ አሽከርነት የለንም፤ አናደርገውም” ብለዋል።
“የትግራይ ሕዝብ በነጻነት እና ወገንተኝነት በሌለበት መንገድ የመረጠውን አካል ነው የምናገለግለው” ብለዋል።
ከሌሎች የትግራይ ሠራዊት አመራሮች ጋር ያላቸው ልዩነት በንግግር ለመፍታት ሞክረው “እምቢ” እንደተባሉ የሚናገሩት ጄነራሉ፤ የተወሰዱ እርምጃዎችንም መቃወማቸውን ገልጸዋል።
መጀመሪያ ከኮር በላይ የሆኑ አመራሮች ተሰብስበው በአቶ ጌታቸው ረዳ የሚመራውን ጊዜያዊ አስተዳደር አውግዘው መግለጫ ሲያወጡ “አልቀበልም” በማለታቸው መታገዳቸውን ያስታወሱት ጄነራል ገብረ እግዚአብሄር “አንቀበልም ማለት መብታችን ነበር” ካሉ በኋላ “ባህሪያቸው ግን ማገድ ነው” ብለዋል።
“እኔ የህወሓት ደጋፊ አይደለሁም ማለት፣ ራሱን ይቻል አልሸከመውም ማለት፣ ሠራዊቱ መሸከም የለበትም ማለት ነው” ብለዋል።
“ራሱን ችሎ ወደ ሕዝብ ይግባ እና ይወዳደር፣ ህወሓት ይጥፋ አይጥፋ የራሱ ጉዳይ ነው። ይቀጥል አይቀጥል የራሱ ጉዳይ ነው። እኔን የሚመለከተኝ የትግራይ ሕዝብ ጉዳይ ነው።”
ለተቃውሟቸው ጠመንጃ ማንሳትን መምረጣቸው በጦርነት ውስጥ የቆየውን የትግራይ ክልል ዳግም ወደ ግጭት አዙሪት አይከተውም ወይ ተብለው የተጠየቁት ጄነራሉ “እኔ ኢንተርናሽናል ጄነራል ነኝ። ይህንን ሆኜ የህወሓት ሚሊሻ መሆን አልፈልግም። ህወሓት ፓርቲያችን ነው የሚሉ የእርሱን ሚሊሻ እንደሆኑ ነው የሚቆጥረው። ሚሊሻነትን ደግሞ አልቀበልም” ብለዋል።
ህወሓት ያለውን ካላደረግክ “ትጠፋለህ፤ መኖር አትችልም። ከትግራይ ትጠፋለህ” ያሉት ጄነራል ገብረ እግዚአብሄር በየነ ያላቸውን ልዩነት ለመፍታት “በጽሑፍ ሞክረናል” ብለዋል።
“ማኅተም መንጠቅ አያስፈልግም ማለት ያስቀጣል እንዴ? ጽህፈት ቤቶች በመዶሻ እየሰበርክ አስተዳዳሪዎች ማባረር ትክክል አይደለም ማለት ያስቀጣል እንዴ?” ሲሉ ይጠይቃሉ።
እኛ የታገልነው በሰላም እንድንኖር ነው ያሉት ጄነራሉ “በሰላማዊ መንገድ በጽሑፍ ሞከርን። ብዙ ጊዜ ሞከርናቸው እምቢ አሉ። የመጨረሻ ሊያስሩን መሆኑን ስናውቅ ወጣን። ሊያስሩን የፈለጉት ደግሞ ይህ አሁን የሚመኩበትን ሠራዊት እንደሚያጡት ላረጋግጥላቸው እፈልጋለሁ” ሲሉ አስጠንቅቀዋል።
ጄነራል ገብረ እግዚአብሄር በየነ በአፋር እና በትግራይ አካባቢ ይንቀሳቀሳል ያሉት የታጣቂ ቡድናቸው ስም ገና አለመወሰኑን እና ወደፊት እንደሚያሳውቁ ተናግረዋል።
“እስካሁን ሦስት አራት ግንባሮች አሉን” ያሉት ጄነራሉ በትግራይ ሠራዊት ውስጥም ብዙ ኃይሎች መኖራቸውን ተናግረዋል።
“የእኛ ሠራዊ ት ነው የሚሉት ሚሊሻ ከእኛ ጋር ነው ያለው። ከፍቶት ነው ያለው። ለውጥ ይፈልጋል። ጊዜው የወጣቶች እንዲሆን ነው የሚፈልገው። እንዲማር እንዲለወጥ ይፈልጋል። የተሻለ ገቢ እንዲኖረው ይፈልጋል። ወላጆቹ እና ቤተሰቦቹ ከውጊያ ወጥተው አሁን መልሶ ግንባታ እና ለውጥ ሰላም ይፍለጋል። ስለዚህ ወጣቱ ሠራዊት እኛ ጋር ነው። ብዙዎች ነን።”
ጄነራል ገብረ እግዚአብሄር በየነ ወደ ግጭት ከመግባታቸው በፊት የሚያሰቀምጡት ቅድመ ሁኔታ መኖሩን ተጠይቀው “እስካሁን ያናገረን ኃይል የለም” ብለዋል።
መቀመጫቸውን በአፋር እና በትግራይ ክልል ማድረጋቸውን የጠቀሱት ጄነራል ገብረ እግዚአብሄር “ወደ አፋር ወርደን እንድንደራጅ ያደረገን ምክንያት አፋር እና ትግራይ ቤተሰቦች ስለሆኑ ነው። የፈቀደልን መንግሥት የለም። ቸግሮን ነበር እዚያ አካባቢ ያሉት አካላት ለተቸገርን እዚህ እንደራጅ ወይ? እንሰንሰብ ወይ? ብለን ጠየቅናቸው። ተሰባሰቡ አሉን። ይህ እኮ ትልቅ ነገር አይደለም። ትግራይ ጫፍ ነው ያለነው። ፈቃድ መጠየቅም የለብንም” ብለዋል።
አራት ግንባር እንዳላቸው የሚጠቅሱት ጄነራል ገብረ እግዚአብሄር “ትልቁ ኃይላችን የሚገኘው ትግራይ ውስጥ ነው” ይላሉ።
ከፌደራል መንግሥቱ ጋር ስላላቸው ግንኙነት ተጠይቀው “እዚህ እንዳለን ያውቃሉ” ያሉ ሲሆን፣ የሚያገኙት ምንም ዓይነት ድጋፍ እንደሌለ ግን ተናግረዋል።
የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር የሆኑት ሌተናል ጄነራል ታደሰ ወረደ ሲሾሙ ጥያቄያቸውን ማቅረባቸውን እና ወገንተኛ ያልሆነ ሠራዊት መገንባት ካልተቻለ “እናንተ ደገፋችሁን አልደገፋችሁን ትግላችንን እንቀጥላለን” ብለው ማሳወቃቸውን ተናግረዋል።
ጥር 15/2017 ዓ.ም. የትግራይ ሠራዊት አመራሮች ውሳኔን ከእርሳቸው ጋር ተቃውመው የወጡ እና አሁን ሠራዊት እያደራጁ የሚገኙ አመራሮች እነማን እነደሆነ ተጠይቀው ስማቸውን ከመናገር ተቆጥበዋል።
በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል ውጥረት መኖሩን እና ግጭት ውስጥ ቢገባ ውሳኔያቸው ምን እነደሚሆን የተጠየቁት ጄነራሉ “አሰላለፋችን ከሕዝብ ጋር ነው። እነርሱ [የህወሓት አመራሮች] ከጌቶቻቸው ጋር ሊሄዱ ይችላሉ፤ እኛ ግን ከሕዝብ ጋር ነው የምነቀረው” ብለዋል።
በትግራይ ክልል ማዕከላዊ ዞን የተወለዱ ጄነራል ገብረ እግዚአብሄር በ1974 ዓ.ም. ህወሓት ወታደራዊውን አመራር ለመጣል የሚያደርገውን ትግል ተቀላለሉ።
በህወሓት ውስጥ ከተራ ወታደር እስከ ክፍለ ጦር አመራር ሆነው ያገለገሉት ጄነራል ገብረ እግዚአብሄር በመጨረሻም የፌደራል መንግሥቱ ሠራዊት የሰሜን ዕዝ አስተዳዳሪ እና ምክትል አዛዥ ነበሩ።
የትግራይ ጦርነት ከመጀመሩ ከጥቂት ወራት በፊት በጡረታ ከመከላከያ ሠራዊት የተሰናበቱት ጄነራሉ በትግራይ ጦርነት ውስጥ ወታደራዊ አመራር ሆነው ተሰልፈዋል። ጄነራሉ በትግራይ ሠራዊት ውስጥ አርሚ 50 የሚባለውን ልዩ ኮማንዶ ኃይል እንደገነቡም ይነገርላቸዋል።
በአሁኑ ወቅትም በአፋር ያለው የታጣቂ ቡድንን አመራሮች መካከል አንዱ ናቸው።