ጨቅላ ሕጻን በማቀፊያ ተጠቅልሎ
የምስሉ መግለጫ,በ14,000 ሰዎች ላይ በተደረገ ጥናት ከአምስቱ መካከል አንዱ የፈለጉትን ያህል ልጆች አለመውለዳቸውን ወይም መውለድ እንደማይችሉ ተናግረዋል

ከ 49 ደቂቃዎች በፊት

ናምራታ ናንጊያ እና ባለቤቷ የአምስት ዓመቷ ሴት ልጃቸው ከተወለደችበት ጊዜ ጀምሮ ሌላ ልጅ የመውለድን ሀሳብ ሲያወጡ እና ሲያወርዱ ቆይተዋል።

ነገር ግን ሁልጊዜ አንድ ጥያቄ ወደ አእምሯቸው ይመላለሳል።

‘አቅማችንን ይፈቅድ ይሆን?’

ናምራታ ኑሮዋ ሕንድ ሙምባይ ውስጥ ሲሆን፣ በመድኃኒት አምራች ኩባንያ ውስጥ ትሠራለች። ባሏ ደግሞ በጎማ ፋብሪካ ውስጥ ነው የሚሠራው።

ነገር ግን ባላት ላይ አንድ ልጅ መጨመር በርካታ ተያያዥ ወጪዎች አሉት።

የትምህርት ቤት ክፍያ፣ የትራነስፖርት አገልግሎት፣ የዋና ትምህርት እንዲሁም የሕክምናው ወጪ ሲሰላ በጣም ውድ ነው።

በእርግጥ ናምራታ ስታድግ ሁኔታዎች በዚህ መልክ አልነበሩም።

“በትምህርት ቤት ከመደበኛ ትምህርት ውጨ ምንም ነገር የለም፤ አሁን ግን ልጄን ዋና ማስተማር ይኖርብኛል፤ እጇን እንድታፍታታም ወደ ሥዕል ትምህርት ቤት መላክ አለብኝ፤ ከትምህርት ባሻገር ሌላ ምን መሥራት እንደምትችል ክህሎቶቿን መፈተሽ ይኖርብኛል።”

የተባበሩት መንግሥታት የሥነ ሕዝብ ፈንድ (ዩኤንኤፍፒኤ) የተባበሩት መንግሥታት የሥነ ተዋልዶ መብት ኤጀንሲ ባወጣው አዲስ ሪፖርት መሠረት የናምራታ ሁኔታ የዓለም እውነታ እየሆነ መጥቷል።

ኤጀንሲው በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች የሚፈልጓቸውን ልጆች ቁጥር መውለድ እንደማይችሉ በማስጠንቀቅ ልጅ ለማሳደግ የሚጠይቀው ወጪ እና ተስማሚ አጋር አለማግኘትን በምክንያትነት ጠቅሷል።

የተባበሩት መንግሥታት የሥነ ሕዝብ ተቋም (ዩኤንኤፍፒኤ) በ14 አገራት ውስጥ የሚገኙ 14,000 ሰዎችን የመውለድ ፍላጎታቸውን ጠይቋል።

ከአምስቱ አንዱ የፈለጉትን የልጆች ቁጥር እንዳልወለዱ ወይም እወልዳለሁ ብለው እንደማይጠብቁ ተናግረዋል።

በጥናቱ የተካተቱ አገራት ደቡብ ኮሪያ፣ ታይላንድ፣ ጣልያን፣ ሃንጋሪ፣ ጀርመን፣ ስዊድን፣ ብራዚል፣ ሜክሲኮ፣ አሜሪካ፣ ሕንድ፣ ኢንዶኔዥያ፣ ሞሮኮ፣ ደቡብ አፍሪካ እና ናይጄሪያ ሲሆኑ፣ ከዓለም ሕዝብ አንድ ሦስተኛውን ይሸፍናሉ።

በምጣኔ ኃብት ረገድ አገራቱ ዝቅተኛ፣ መካከለኛ እና ከፍተኛ ገቢ ያላቸው ሲሆኑ፣ በውልደት መጠንም ዝቅተኛ እና ከፍተኛ የውልደት መጠን የሚታይባቸው ናቸው።

ዩኤንኤፍፒኤ ወጣት እና የመውለጃ ጊዜያቸው ያለፈ ግለሰቦችን በዚህ ጥናቱ አካትቷል።

የተቋሙ ኃላፊ የሆኑት ዶ/ር ናታሊያ ካነም “በዓለም ከዚህ በፊት ታይቶ በማይታወቅ መልኩ የወሊድ መጠኑ ማሽቆልቆል ጀምሯል” ብለዋል።

“ጥናቱ ላይ የተሳተፉ አብዛኞቹ ሰዎች ሁለት ወይም ከዚያ በላይ ልጆች ይፈልጋሉ። የወሊድ መጠን በከፍተኛ ደረጃ እየቀነሰ የመጣበት ምክንያት ብዙዎች የሚፈልጉትን ቤተሰብ መፍጠር እንደማይችሉ ስለሚሰማቸው ነው። ይህ ደግሞ ትክክለኛው ቀውስ ነው” ብለዋል።

በአውሮፓ የመውለድ ፍላጎትን ያጠኑት እና የፊንላንድ መንግሥት በሥነ ሕዝብ ፖሊሲ ላይ የሚያማክሩት አና ሮትኪርች “ይህን ቀውስ ብሎ መጥራት ተገቢ ነው ብዬ አስባለሁ” ይላሉ።

“በአጠቃላይ፣ የመውለድ ፍላጎት ከመጨመር ይልቅ እየቀነሱ ናቸው” ትላለች።

ይህንን በአውሮፓ ለረዥም ጊዜ ማጥናቷን ገልጻ፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ የማየት ፍላጎት አላት።

ከ50 በላይ ሰዎች (31 በመቶ) ከሚፈልጉት የልጅ ብዛት ያነሰ መውለዳቸው መናገራቸውም አስገርሟታል።

በሁሉም አገሮች 39 በመቶ የሚሆኑ ሰዎች የገንዘብ ውሱንነት ልጅ እንዳይወልዱ እንዳደረጋቸው ተናግረዋል።

ከፍተኛው ምላሽ በኮሪያ (58 በመቶ) ሲሆን፣ ዝቅተኛው ደግሞ በስዊድን (19 በመቶ) ነው።

በድምሩ 12 በመቶ ሰዎች በመሃንነት ወይም ለመፀነስ በመቸገር ምክንያት የሚፈልጓቸውን ልጆች ቁጥር አለመውለዳቸውን ተናግረዋል።

ነገር ግን ይህ ቁጥር በታይላንድ (19 በመቶ)፣ በአሜሪካ (16 በመቶ)፣ ደቡብ አፍሪካ (15 በመቶ)፣ ናይጄሪያ (14 በመቶ) እና ሕንድ (13 በመቶ) ሲሆን ከፍ ያለም ነበር።

በሆንግ ኮንግ የሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የሥነ ሕዝብ አወቃቀር ተመራማሪ ፕሮፌሰር ስቱዋርት ጊቴል ባስተን “[የተባበሩት መንግሥታት] በዝቅተኛ የወሊድ ምጣኔ ጉዳይ ላይ የተሟላ ምርምር ሲያደርግ ይህ የመጀመሪያው ነው።”

እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ኤጀንሲው ጥናት ያደርግ የነበረው ከሚፈልጉት በላይ ልጆች ባሏቸው ሴቶች እና “ያልተሟላ የእርግዝና መከላከያ ፍላጎት” ላይ ነበር።

አሁንም ዩኤንኤፍፒኤ ለዝቅተኛ የወሊድ ምጣኔ ምላሽ ጥንቃቄ እንዲደረግ አሳስቧል።

ከ40 ዓመታት በፊት ቻይና፣ ኮሪያ፣ ጃፓን፣ ታይላንድ እና ቱርክ የሕዝብ ብዛታችን በጣም ከፍተኛ ነው ብለው ይጨነቁ ነበር።

እንደ አውሮፓውያኑ በ2015 የወሊድ መጠንን መጨመር ፈለጉ።

ፕሮፌሰር ጊቴል ባስተን “እነዚያ አገራት ማንኛውንም ዓይነት ያልተጠና ፖሊሲ እንዳያወጡ በተቻለ መጠን መምከር እንፈልጋለን” ብለዋል።

“ዝቅተኛ የወሊድ መጠን፣ ከፍተኛ በዕድሜ የገፉ ሰዎች ቁጥር፣ የሕዝብ ቁጥር መቀነስ ብሔርተኝነትን ለመተግበሪያነት ሰበብ ሲሆን፣ ፀረ ስደተኛ ፖሊሲዎችን እና የሥርዓተ-ፆታ ወግ አጥባቂ ፖሊሲዎችን ለመተግበር እንደ ሰበብ ሲጠቀሙ እያየን ነው” ብለዋል።

የመንግሥታቱ ድርጅት ተቋ፥እ ከገንዘብ እጥረት ይልቅ ለልጆች ቁጥር መቀነስ የበለጠ ትልቅ እንቅፋት ሆኖ ያገኘው የጊዜ አለመኖር ነው።

በሙምባይ ለምትኖረው ናምራታ ያ እውነትነት አለው።

በቀን ቢያንስ ለሦስት ሰዓታት ወደ ቢሮዋ በመጓዝ ታሳልፋለች። ቤት ስትደርስ በድካም ዝላለች።

ነገር ግን ከልጇ ጋር ጊዜ ማሳለፍ ትፈልጋለች። ቤተሰቧ ብዙ እንቅልፍ አይተኛም።

“ከሥራ ቀናት በኋላ፣ እናት በመሆኔ ከልጄ ጋር በቂ ጊዜ ስለማሳልፍ የጥፋተኝነት ስሜት ይሰማኛል” ትላለች።

“ስለዚህ አንድ ልጅ ብቻ በቂ ነው የሚለው ላይ እናተኩራለን።”