
11 ሰኔ 2025, 08:21 EAT
ስዊዲናዊቷ ተሟጋች ግሬታ ቱንበርግ እና 11 ሰዎች ለጋዛ እርዳታ ጭነው በመርከብ ሲሄዱ በአለም አቀፍ ውሃ ላይ በእስራኤል ከተያዙ ከአንድ ቀን በኋላ ከአገር እንድትባረር መደረጉን እስራኤል አስታወቀች።
ግሬታ ከአገር ለመውጣት መስማማቷን ተከትሎ ማክሰኞ ዕለት ከቴላቪቭ ወደ ፈረንሳይ መብረሯን የእስራኤል ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገልጿል።
ፓሪስ አየር ማረፊያ ስትደርስ ግሬታ እስራኤል በዓለም አቀፍ ባሕር ሕገ ወጥ እገታ እንደፈፀመችባቸው ተናግራለች።
ፈረንሳይ ከግሬታ ጋር ተይዘው ከነበሩ ከስድስቱ ዜጎቹ ውስጥ አምስቱ ከአገር የሚያባርራቸውን ትዕዛዝ አልፈርምም ማለታቸውን ያስታወቀች ሲሆን፤ ተሟጋቾቹ በሕግ ይጠየቃሉ ብላለች።
የመርከቧ ባለቤት ‘የነፃነት ጀልባ ጥምረት’ በሚል የሚጠራው ተሟጋቾች ቡድን ሁሉም የተያዙት ሰዎች በአፋጣኝ እንዲለቀቁ ጠይቋል።
ቡድኑ መርከቧ በእስራኤል ጦር ዓለም አቀፍ ባሕር ላይ ከጋዛ 185 ኪ/ሜ ርቀት ላይ መያዟን አስታውቋል።
ተሟጋቾቹ ሰኞ ጠዋት የእስራኤልን የባሕር እግድ አሻፈረኝ በማለት በጋዛ የሰብዓዊ ቀውሱን ለማንፀባረቅ “ተምሳሌታዊ” እርዳታ ለማድረስ እየተጓዙ እያለ መርከቧ ተጠልፋለች።
የእስራኤል ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ‘የተናጠል እንቅስቃሴ’ በሚል ሁኔታውን ያጣጣለ ሲሆን፤ ሁሉም መንገደኞች ሰኞ ምሽት ወደ ቴል አቪቭ አየር ማረፊያ መወሰዳቸውን ገልጿል።
“ከአገር የሚያስወጣውን ሰነድ ለመፈረም እና እስራኤልን ለቀው ለመውጣት ፈቃደኛ ያልሆኑት በእስራኤል ሕግ መሰረት ከአገር እንዲወጡ ለፍርድ ይቀርባሉ” ብሏል።
ግሬታ ቱንበርግ በነፃ ለምን እንደተለቀቀች ስትጠየቅ “ትንሽ ግልፅ አይደለም” ያለች ሲሆን፤ እርሷ እና አንዳንዶች በተቻለ ፍጥነት ከእስራኤል ለመውጣት ሰነድ መፈረማቸውን፤ ነገር ግን በሕገ ወጥ መንገድ ወደ እስራኤል መግባታቸውን አልተቀበልንም ብላለች።
ሚኒስቴሩ ማክሰኞ ጠዋት ግሬታ ቱንበርግ ከእስራኤል በፈረንሳይ በኩል ወደ ስዊድን እንደምትበር ከገለፀ በኋላ፤ አውሮፕላን ውስጥ ተቀምጣ የሚያሳይ ምስል በማኅበራዊ የትስስር ገፆች ላይ አጋርቷል።
ግሬታ ፓሪስ ቻርለስ ደ ፏል አየር ማረፊያ ስትደርስ ለጋዜጠኞች እስራኤል “በዓለም አቀፍ ባሕር በሕገ ወጥ መንገድ ያለ ፍላጎታችን አግታ ወደ እስራኤል ወስዳናላች። እንዳንወጣ በጀልባው የታችኛው ክፍል እንድንቆይ አድርጋለች” ብላለች።
“ይህ እውነተኛው ታሪክ አይደለም። እውነታው በጋዛ የዘር ጭፍጨፋ እየተካሄደ ነው፤ በእግድ እና ከበባ ስልታዊ ረሃብ አለ። ለጋዛ በእጅጉ የሚያስፈልገው ምግብ፣ መድኃኒት፣ ውሃ እንዳይገባ እየተከለከለ ነው” ስትል እስራኤልን ወቅሳለች።
የእስራኤል ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እግዱ “ዓለም አቀፍ ሕግን የተከተለ” ነው በሚል እየወተወተ ሲሆን፤ ይህን እግድ ለመጣስ የሚደረግ ሙከራ “አደገኛ፣ ሕገ ወጥ እና እየተካሄደ ያለውን የሰብዓዊ ጥረት የሚያዳክም ነው” ብሏል።
እስከ ጀልባቸው በቁጥጥር ስር የዋሉት ተሟጋቾቹ ከስዊድን እና ፈረንሳይ ዜጎች በተጨማሪ የብራዚል፣ ጀርመን፣ ኔዘርላንድ፣ ስፔን እና ቱርክ ዜጎች ናቸው።
እስራኤል እና ግብፅ ሐማስ ተቀናቃኙን አሸንፎ ጋዛን እ.አ.አ በ2007 ሲቆጣጠር የአየር እና ባሕር እግድ ጥለዋል።