ዳታን በመቆጠብ ጽሑፍ ብቻ ለማንበብ

አንዲት ሴት

11 ሰኔ 2025, 06:38 EAT

በዓለም ዙሪያ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎችን የሚያሰቃይ ህመም ነው። የሰዎችን ወደፊት፣ የሥራ ሁኔታ ይለውጣል፤ ዓለማቸውንም ያጠብባል። ለዚህም ነው “የሚፈውስ” መፍትሔ ተገኘ ወይም በትንሹ እንኳ ማይግሬን ህመምን ያስታግሳል ነው ሲባል ሰዎች የሚሞክሩት።

ለማይግሬን ህክምናዎች ቢኖሩም በሽታውን ጨርሶ የሚያጠፋ መፍትሔ የለውም። በትዕዛዝ የሚሰጡ መድኃኒቶች በጣም ውጤታማ ሊሆኑ ይችላሉ፤ ነገር ግን ሁሌም አይሠሩም። ለብዙ ሰዎች ቀላል የሚባል መፍትሔ የለም።

አንዳንዶች ይህንን ህመም የሚያስታግሱበት የራሳቸውን ዘዴዎች ይፈጥራሉ። ለአንዳዶች መፍትሔው በበረዶ የተሞላ ከረጢት ይዘው፣ የፍራ ፍሬ ጭማቂ እና ወተት ድብልቅ እየጠጡ የሞቀ ውሃ ገንዳ ውስጥ መቀመጥ ሊሆን ይችላል። ሌሎች ደግሞ ግማሽ ፊታቸውን በፀጉር ማድረቂያ እንዲነፍስበት ማድረግ ይሠራላቸዋል።

አሁን ደግሞ አንድ መፍትሔ ዝነኝነት አግኝቷል። “ማክማይግሬን ሚል” ስያሜ ተሰጥቶታል። ቲክቶክ ላይ አዲሱን መፍትሔ እያወደሱ ያሉ በመቶዎች ሚቆጠሩ ሰዎች ኮካ ኮላ እና ጨው ያለው የድንች ጥብስ (ችፕስ) ለማይግሬን ህመም ማስታገሻ የሆነላቸው ይመስላል።

ከዚህ መፍትሔ ጀርባ አንዳች ሳይንስ ካለ፤ መነሳት ያለበት ጥያቄ “ይህ ጉዳይ ሰውነትን ምን ያደርጋል?” የሚል መሆን አለበት።

በኦክስፎርድሻየር ነዋሪ የሆነው ኒክ ኩክ፤ ድንገት ማይግሬን የሚያጋጥመኝ ከሆነ በሚል ሁልጊዜም “ዋሌት ሙሉ መድኃኒት” ይይዛል። ህመሙን ለማስቆም “ማንኛውንም ነገር እንደሚሞክር” ይናገራል።

“በዚህ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ሲኮን፣ በሳምንት አምስት ቀን ሲሠራ እና መቀጠል ግዴታ ሲሆን ምንም ነገር ይሞከራል” ይላል።

ህመሙ እጅግ ሲበረታ የኒከወ በዓይኑ ዙሪያ የሚኖረው ስሜት የዓይን ኳሶቹ እየተጨፈለቁ ያሉ ያህል ህመም ነው። ይህንን ህመም መለስ የሚያደርግለት ካፊን እና ኮካ ኮላ ውስጥ ያለው ስኳር እንደሆነ ይናገራል።

“አንዳንድ ጊዜ ህመሙን በቶሎ ከደረስኩበት ይሠራልኛል። ዕይታዬ ድክምክም ሲል ህመሙ እየመጣ እንደሆነ ይሰማኛል” ሲል ይገልጻል።

ኮካ ኮላ መጠጣት የማይክሬን ህመሙን ለመከላከል የሚወስደውን አመትሪፕተሊን መድኃኒት አጽንኦት ይሰጣል። አንዳንዴ ግን “እስከ ቀኑ መጨረሻ ለሚቆይ ጊዜ” እንደሚረዳው ይናገራል።

የድንች ጥብስ ምሥል

ሕይወቷን በሙሉ ከፍተኛ የሆነ ማይግሬን ለሚያሰቃያት ለ27 ዓመቷ ኬይሊ ዌብስተር ደግሞ የህመሙን መጠን የሚቀንሰው ድንች ጥብስ ላይ ጨው አድርጎ መመገብ ነው።

ህመሙን ለማስታገስ እንደሚረዳት የምትናገረው ኬይሊ፤ “ፈዋሽ አለመሆኑ ግን እርግጥ ነው” ትላለች።

“ማይግሬን ውስብስብ ኒውሮሎጂካል ህመም ነው። በትንሽ ካፌን፣ ፈጣን ምግቦች ላይ በሚደረግ ጨው እና በስኳር አይፈወስም” ስትል ትናገራለች።

ኬይሊ መፍትሔ ናቸው የተባሉ የተለያዩ መድኃኒቶችን ሞክራለች። እግሯን የሞቀ ውሃ ውስጥ መዘፍዘፍ፣ ጭንቅላቷ ጀርባ ላይ እርጥብ ጨርቅ ማድረግ፣ አኩፓነቸር፣ የሞቀ የጠርሙስ ብርጭቆ ቆዳ ላይ ማድረግ የመሳሰሉትን ብትሞክርም ውጤታቸው እዚህ ግባ የሚባል አልነበረም።

እረፍት ከሰጧት የተወሰኑ ዘዴዎች መካከል አንዱ፤ ጭንቅላት፣ ፊት እና አንገት ላይ በርካታ መርፌዎችን መወጋት ወይም ሜዲካል ቦቶክስ ነው። ቦቶክስ እንዴት ለማይግሬን መፍትሄ እንደሚሆን እስከአሁን ባይታወቅም፤ ከነርቮች የሚለቀቁ ኃይለኛ የህመም ስሜቶችን እንደሚገድብ ይታመናል።

ለቀናት ሊቆይ የሚችለው የማይግሬን ህመም፤ አጭር እና እንደ ፓራሴታሞል ባሉ የማስታገሻ መድኃኒቶች መፍትሔ ከሚያገኘው የራስ ምታት ህመም እጅግ የተለየ ነው።

ማይግሬን የጭንቅላት ህመም፣ አንገት ህመም፣ መደንዘዝ፣ የዕይታ መደብዘዝ እንዲሁም ንግግር እና እንቅስቃሴ ላይ የሚፈጠር ተጽዕኖን ሊያስከትል ይችላል።

ከክርስቶስ መወደል ሦስት ሺህ ዓመታት በፊት በነበሩ የራስ ቅል አጽሞች፤ የጥንት ግብፃውያን ጭምር በማይግሬን ይቸገሩ እንደነበር አሳይተዋል። ማይግሬን ይህንን ያህል ረጅም ታሪክ ቢኖረውን የሚከሰትበት ትክክለኛ ምክንያት እስካሁን አልታወቀም።

በደም ሥሮች ውስጥ ያሉ የህመም ተቀባይዎች እና በአንጎል ዙሪያ ያሉ የነርቭ ሕብረ ህዋሳት (ቲሹ) በተሳሳተ መልኩ የሆነ ችግር እንዳለ የሚያጠቁሙ ምልክት ሲልኩ የሚፈጠር ህመም እንደሆነ ይታሰባል።

ይሁን እንጂ የተወሰኑ ሰዎች የነርቭ ሥርዓት ለምን ከልክ ያለፈ ስሜት እንደሚሰጥ እንዲሁም የነርቭ ሥርዓቱ ለምን ለአንዳንዶች ይህንን ዓይነት ምላሽ እየሰጠ ለሌሎች እንደዚህ እንደማይሆን አልታወቀም።

ኮካ ኮላ
የምስሉ መግለጫ,እንደ ኮካ ያሉ መጠጦች ካፌን ስለሚይዙ ለአንዳንዶች መፍትሔ ቢሆኑም ካፌን በራሱ የማይግሬን ህመምን ይቀሰቅሳል

ባለሙያዎች፤ ከሰባት ሰዎች አንዱ ለምን በዚህ ህመም እንደሚጠቃ ለማወቅ ወይም እነሱን ለመርዳት የሚያስችል መፍትሄ ለማምጣት የሚያስችል በቂ ምርምር አልተደረገም ሲሉ ይሟገታሉ።

በማይግሬን ላይ ስፔሻላይዝ ያደረጉት ጠቅላላ ሐኪም ዶ/ር ኬይ ኬኒስ፤ ህመሙን ለመግታት የሚያስችሉ ንጥረ ነገሮች በማክማይግሬን ምግቦች ውስጥ ቢኖሩም “የማክዶናልድ” አካል አይደሉም ይላሉ።

“በኮካ ኮላ ውስጥ የሚገኘው ካፌን ነርቭን የሚያውክ ነው። ነርቭን እንቅስቃሴ ላይ ተጽእኖ የሚያደርግ ንጥረ ነገር ነው። ይህ የማወክ ተግባር ለአንዳንዶች በአዎንታዊ መንገድ ሊሠራ ይችላል” በማለት ይናገራሉ።

“ሰዎች ለማይግሬን ህመም የሚወስዷቸው እና ካፌን ያላቸው እዳንድ ማስታገሻ መድኃኒቶች አሉ። አንዳንዶች በዚያ መፍትሄ ያገኛሉ። ለምን እንደሆነ ግን ሙሉ በሙሉ አልታወቀም” ሲሉ ያክላሉ።

የሕክምና ባለሙያዋ እንደ ኮካ ያሉ ካፌን የበዛባቸውን መጠጦችን ለማይግሬን በመደበኛነት መጠቀምን በተመለከተ ያስጠነቅቃሉ።

“ብዙ ካፌን በራሱ ህመሙን ሊቀሰቅስ ይችላል፤ እናም በረጅም ጊዜ ውስጥ ከዚህ በባሰ ሁኔታ ውስጥ ሊወድቁ ይችላሉ” ይላሉ።

በፈጣን ምግቦች ውስጥ ከሚካተተው ጨው ያለው ድንች ጥብስም ቢሆን የነርቭ እንቅስቃሴ ላይ ተጽእኖ እንደሚያደርግ ዶ/ር ኬይ ያስረዳሉ። ነገር ግን ሶዲየም ማይግሬን ላይ ያለው ተጽእኖ ምን እንደሆነ አለመሞከሩን አክለዋል።

ፈጣን ምግቦች ብቻ ሳይሆኑ በፋብሪካ ውስጥ ያለፉ እና ጤናማ የአጋገብ ሥርዓትን የማይከተሉ ምግቦችንም በተመለከተ የጤና ባለሙያዋ አስጠንቅቀዋል።

እንደዚህ ዓይነት ምግቦች በብዙ ምግቦች ውስጥ የሚገኘውን እና የከፋ ማይግሬን የሚያስከትለውን ታይራማይን የተሰኘ የተፈጥሮ ውህድ በከፍተኛ መጠን እንደሚይዙ ይናገራሉ።

ለኤሎሲ አንደርውድ ደግሞ የትኛውም የማይግሬን ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ያሉ ፈጣን መፍትሔዎች አይሰሩላትም።

ኤሎሲ አንደርውድ
የምስሉ መግለጫ,ኤሎሲ አንደርውድ በዚህ ህመም ምክንያት ከተለያዩ ስራዎች ለቅቃለች

ከፍተኛ በሆነ የማይግሬን ህመም የምትሰቃየው ኤሎሲ፤ መፍትሔ የሚሆናትን “ተአምራዊ ምግብ” ለሰባት ዓመታት ፈልጋለች።

ሰዎች፤ ሐኪሞች አደገኛ እንደሆነ የሚገልጹትን እግርን በፈላ ውሃ ውስጥ መዘፍዘፍ፣ ቡና መጠጣት ወይም ንዝረት የሚፈጥሩ (ቫይብሬት) መሳሪያዎችን መጠቀምን ሲመክሩ ተመልክታለች። እነዚህም ግን ውጤታቸው እምብዛም ነበር።

ኤሎሲ፤ “እኛ የሚሰማንን የተስፋ መቁረጥ ስሜት ለራሳቸው የሚጠቀሙ ብዙ ቪድዮዎች ኦንላይን ላይ አሉ” ትላለች።

በዚህ ህመም ምክንያት ብዙ ሥራዎቿን አቋርጣለች፤ ብዙዎቹን የተወችው ቢሮው ውስጥ በሚኖሩት እና ማይግሬንን በሚቀሰቅሱት ብርሃን እና ጫጫታ ምክንያት ነው።

በቅርቡም ከነበራት ቤት እና ቢሮን ማስዋብ (interior designer) ሥራ ለቅቃ፤ የሰርግ አበባዎችን አዘጋጅታ የምትሸጥበትን የራሷን የንግድ ሥራ ከቤቷ ጀምራለች።

በዙሪያዋ የሚሰሙ ድምጾችን ኃይለኝነት ለመቀነስ እንዲያግዛት የጆሮ መሸፈኛዎችን የምታደርግ ሲሆን፣ ይህም ማኅበራዊ ሕይወቷን ገድቦታል።

“ሰዎች ማይግሬን የራስ ምታት ህመም እንደሆነ ያስባሉ፤ እርሱ አንድ ምልክቱ ነው” የምትለው ኤሎሲ፤ “ማይግሬን ለእኔ ሙሉ ሰውነትን የሚነካ ነገር ነው” ስትል ስሜቱን ታስረዳለች።

“ማይግሬን ሕይወቴን አሳንሶብኛል” ትላለች።

መድሃኒቶች

በኪንግስ ክሊኒካል ሪሰርች ፋሲሊቲ፤ ኒውሮሎጂስት የሆኑት ፕሮፌሰር ፒተር ጋድስቢ፤ ማይግሬንን በተመለከተ የሚደረጉ ምርምሮች ለዓመታት በቂ ገንዘብ የማይመደብላቸው ሆነው ቢቆዩም በአሁኑ ወቅት አዎንታዊ ውጤቶችን ማስገኘት መጀመራቸውን ይናገራሉ።

ፕሮፌሰሩ በቅርቡ ያሳተሙ አንድ ጥናት ጌፓንትስ በመባል ሚያወቁት ዓይነት መድኃኒቶች የማይግሬን ህመምን የሚያስከትሉ ህመም ተቀባዮችን በመገደብ ህመሙ ከመጀመሩ በፊት ማቆም እንደሚችሉ አሳይቷል።

“ማንኛውም አዲስ ህክምና የተስፋ ጭላንጭልን ይፈነጥቃል” የምትለው ኤሎሲ፤ “ለሁሉም ሰው የሚሠራ ነገር እንደሌለ ይናገራሉ፤ ነገር ግን የሆነ ነገር ለሆነ ሰው ይሠራል” በማለት ተስፋዋን አስረድታለች።

ፕሮፌሰር ፒተር ጋድስቢ እንደሚናገሩት የሕይወት ዘይቤን መቀየር ለውጥ ሊያመጣ እንደሚችል ይጠቅሳሉ። ደባሪ ሊሆን ይችላል ነገር ግን ዋናው ነገር “ለአእምሮ ጥንቃቄ ማድረግ ነው” ይላሉ።

“[ሕይወታችሁ] ወጥነት ሊኖረው ይገባል። ከፍታ እና ዝቅታዎችን አስወግዱ። እንደ ማዛጋት፣ እንቅልፍ ማዳፋት፣ የስሜት ለውጥ፣ ብዙ መጸዳዳት እንዲሁም ጨው እና ስኳር መፈለግ ያሉ የማስጠንቀቂያ ምልክቶቹ የሚሰሟችሁ ከሆነ ሰውነታችሁን አድምጡት።”

“የእኔ ምክር ቲክቶክን ትታችሁ ሰውነታችሁን አዳምጡት የሚል ነው” ይላሉ ፕሮፌሰሩ።

ኒክ ኩክ እና አጋሩ ኬቲ
የምስሉ መግለጫ,ኒክ እና አጋሩ ኬቲ የማይግሬን ህመም ተጠቂ ናቸው። ኒክ ህመሙን ለመቀነስ መነጽር ያደርጋል

ኒክም ሲያደርግ የነበረው ይህንኑ ነው። ያልተለመደውን ኮካ ኮላ እና ጨው ያለው የድንች ጥብስ ሊጠቀም ቢችልም፤ ሕይወቱን በሙሉ የቀየረውን የማይግሬን ህመሙን ማስታገስ እንዲያስችለው በማድረግ ነው።

“መጠጥ አልጠጣም፣ ደመናም ቢሆን መነጽር አደርጋለሁ” በማለት ይናገራል። “ከመስመር አልወጣም። እኔ እና አጋሬ በምንጓዝ ጊዜ ከምንይዘው ጓዝ ውስጥ ግማሹ የማይግሬን ህመሜን ለማስታገስ የሚያችሉኝ ነገሮች ናቸው”

በቅርቡ በተደረገ የቅድመ ጋብቻ ድግስ ላይ ኒክ በራሱ እና በጓደኞቹ ሕይወት መካከል ያለውን ልዩነት ማስተዋሉን ይናገራል።

“እስከሚነጋ ድረስ ሌሊቱን ሲጠጡ ነበር” የሚለው ኒክ፤”የረሃብ ስሜት ህመሙን ስለሚቀሰቅስ የራሴን ትራስ፣ አፕል፣ ሙዝ እና ሌሎች ምግቦች ይዤ ነበር።”

“እኩለ ሌሊት ላይ ተኝቻለሁ። ጓደኞቼ ይህንን ስለሚያውቁ ምንም አልመሰላቸውም። ምክንያቱም ሕይወቴን መኖር ያለብኝ እንደዚህ ነው” ሲል በሽታው ሕይወቱን እንዴት እንደለወጠው ማሳያ ይጠቅሳል።