
11 ሰኔ 2025, 09:25 EAT
ዩናይትድ ኪንግደም ሁለት የእስራኤል ቀኝ ዘመም ሚኒስትሮች እስራኤል በኃይል በያዘችው ዌስት ባንክ “በፍልስጤም ማኅበረሰቦች ላይ በተደጋጋሚ ጥቃት በማነሳሳት” ማዕቀብ ጥላለች።
ኢትማር ቤን ጋቪር እና በዛለል ስሞትሪች የተባሉት ሚኒስትሮቹ ወደ ዩናይትድ ኪንግደም እንዳይገቡ እና በዩኬ ያላቸውን ንብረትም እንዳያንቀሳቀስ እግድ እንደተጣለባቸው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።
ማክሰኞ ዕለት ይፋ የሆነው እርምጃው ከአውስትራሊያ፣ ኖርዌይ፣ ካናዳ እና ኒው ዝላንድ ጋር በጋራ የተወሰደ እንቅስቃሴ አካል ነው።
ለእርምጃው ምላሽ የሰጠችው እስራኤል “የተመረጡ ተወካዮች እና የመንግሥት አባላት ለእንደዚህ አይነት እርምጃ መዳረጋቸው አሳዛኝ ነው” ብላለች።
የዩናይትድ ኪንግደም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴቪድ ላሜይ የእስራኤል የፋይናንስ ሚኒስትር ስሞትሪች እና የደኅንነት ሚኒስትር ቤን ጋቪ “በፍልስጤም ሰብዓዊ መብቶች ላይ ከባድ ጥቃት እና የአክራሪ ግጭቶችን አነሳስተዋል” ብለዋል።
የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ እርምጃውን የተቃወሙ ሲሆን፤ “እንደዚህ አይነት ማዕቀቦች አሜሪካ መር የሆነውን የተኩስ ማቆም ጥረት አይደግፉም፤ ታጋቾችን ወደ ቤታቸው አይመልስም፤ ጦርነቱንም አያስቆምም” በማለት በኤክስ ገፃቸው አስታውቀዋል።
አገራቱ ማዕቀቡን እንዲያነሱ የጠየቁት ሩቢዮ፤ አሜሪካ ከእስራኤል ጋር በአጋርነት እንደምትቆም ገልፀዋል።
በእስራኤል የአሜሪካ አምባሳደር ማይክ ሀክቢ የሩቢዮን ውግዘት የተጋሩ ሲሆን፤ ከቢቢሲ ጋር በነበራቸው ቃለ ምልልስ እርምጃውን “አስደንጋጭ ውሳኔ” ብለውታል።
ሁለቱ የእስራኤል ሚኒስትሮች በጋዛ ጦርነት ላይ ባላቸው አቋም ትችት ይሰነዘርባቸዋል።
ሚኒስትሮቹ በጋዛ ሰርጥ እርዳታ እንዲገባ የተደረጉ ጥረቶችን የተቃወሙ እንዲሁም በጋዛ ያሉ ፍልስጤማዊያን ወደ ሌላ አካባቢ እንዲፈናቀሉ ጥሪ አቅርበዋል።
የዩኬ ውጭ ጉዳይ ቢሮ “በዌስት ባንክ የፍልስጤም ማኅበረሰብ በእስራኤል ፅንፈኛ ሰፋሪዎች ከባድ ጥቃት እየደረሰበት ሲሆን፤ ይህም የፍልስጤምን ወደፊት የሚጎዳ ነው። ዓለም አቀፍ ምላሽ ለማጠናከር ዩኬ አውስትራሊያን፣ ካናዳን፣ ኒው ዝላንድን እና ኖርዌይን ተቀላቅላለች” ብሏል።
ከመግለጫው በኋላ ዴቪድ ላሜይ “እነዚህ ድርጊቶች ተቀባይነት የላቸውም። ተጠያቂዎች ኃላፊነት እንዲወስዱ ለማድረግ ነው እርምጃ የወሰድነው” ብለዋል።
“በጋዛ አፋጣኝ የተኩስ አቁም፣ በጋዛ ወደፊት የመምራት ሚና በሌለው ሀማስ የተያዙ ታጋቾች በአፋጣኝ እንዲለቀቁ፣ እርዳታ እንዲጨምር እና የሁለት አገር መፍትሔን ለማሳካት አንጥራለን” ሲሉም አክለዋል።
የእስራኤል ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ሳር “ተቀባይነት የሌለው ውሳኔ” ሲሉ ለጠሩት እርምጃ ምላሽ ለመስጠት ካቢኔው በሚቀጥለው ሳምንት እንደሚገናኝ ተናግረዋል።
የዩኬ ውጭ ጉዳይ ቢሮ አምስቱ አገራት “በዌስት ባንክ የሚገኙ የፍልስጤም ማኅበረሰቦች ላይ እየጨመረ ያለው ጥቃት እና በእስራኤል ሰፋሪዎች የሚፈፀመው ማስፈራሪያ እንዲቆም ግልፅ” ናቸው ብሏል።
ቢሮው በመግለጫው በሚኒስትሮቹ ላይ የተጣለው ማዕቀብ “እስራኤል ዓለም አቀፍ የሰብዓዊነት ሕግን ማክበር ባለባት ጋዛ እየተፈፀሙ ካሉ ሁነቶች የተለየ ተደርጎ መታየት የለበትም” ሲልም አክሏል።
ሚኒስትሮቹ በእስራኤል ጥምር መንግሥት እጅግ አክራሪ የተባሉ ፓርቲዎችን የሚመሩ ናቸው።