ዳታን በመቆጠብ ጽሑፍ ብቻ ለማንበብ

በሎስ አንጀለስ የተሰማሩ ወታደሮች

11 ሰኔ 2025, 08:14 EAT

የፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር ስደተኞችን መክበብ እና በቁጥጥር ስር ማዋል ፖሊሲ ጋር ተያይዞ በተነሳው ተቃውሞ በሺዎች የሚቆጠሩ ወታደሮች መሰማራታቸውን “የአምባገነን ፕሬዚዳንት ቅዠት” ሲሉ የካሊፎርኒያ ግዛት አስተዳዳሪ ዘለፉ።

ተቃውሞ በሌሎች ከተሞች የተዛመተ ሲሆን ሎስ አንጀለስን የምትካተትበትን የካሊፎርኒያን ግዛት የሚያስተዳድሩት ጋቪን ኒውሶም “ሁኔታውን ያቀጣጠለው ትራምፕ” ነው ሲሉ ወቅሰዋቸዋል።

ቀናትን ባስቆጠረው በዚህ ተቃውሞ ትራምፕ በሺዎች የሚቆጠሩ ወታደሮችን እና የባህር ኃይል አባላት ማሰማራታቸውን አስተዳዳሪው ጋቪን እርምጃው “የአምባገነኑ ፕሬዚዳንት ቅጥ ያጣ ቅዠት” ሲሉ ዘልፈዋቸዋል።

በሎስ አንጀለስ እና አካባቢው 700 የአሜሪካ ባህር ኃይል አባላት እንዲሁም 4 ሺህ የብሔራዊ ዘብ አባላት ተሰማርተዋል።

ግዛቲቱ ያለ አስተዳዳሪው ፈቃድ ወታደር በመላክ ፕሬዚዳንቱን እየከሰሰች ነው።

የአሜሪካ መከላከያ በአገሪቱ ግዛቶች ውስጥ ህግ የማስከበር ሚና መኖሩ ያልተለመደ ነው።

ከፕሬዚዳንት ትራምፕ የስደት ፖሊሲ ጋር በተያያዘ የተነሳው ተቃውሞ በከፍተኛ ሁኔታ የተቀጣጠለባት ሎስ አንጀለስ የሰዓት እላፊ አዋጅ ተጥሎባታል።

ከአርብ ጀምሮ በሎስ አንጀለስ አራት የሜክሲኮ ዜጎች በቁጥጥር ስር ውለው ወደ ሜክሲኮ እንዲመለሱ መደረጋቸውን የሃገሪቱ የውጭ ጉዳይ ቢሮ አስታውቋል።

በሎስ አንጀለስ ትራምፕ ባሰማሯቸው ወታደሮችና በተቃዋሚዎች የተከሰተው ፍጥጫ ከ1965 ወዲህ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ያለ ግዛቷ አስተዳዳሪ ፈቃድ ብሔራዊ ዘብን ያሰማራበት የመጀመሪያ ክስተት ነው።

የአሜሪካ የባህር ኃይል አባላት ከዚህ ቀደም በደረሱ ከባድ የተፈጥሮ ቀውሶች በአውሮፓውያኑ 2005 የሃሪኬን ካትሪና አውሎ ንፋስ እንዲሁም የመስከረም 2001 ጥቃት መሰማራታቸው ይታወሳል።

የትራምፕ አስተዳደር እስካሁን ድረስ ወታደሮቹ ሰላማዊ ዜጎችን እንደ ፖሊስ እንዲቆጣጠሩ የሚፈቅደውን ‘ኢንዘሬክሽን አክት’ (የአመጽ ህግን) ተግባራዊ አላደረገም።

የሎስ አንጀለስ ከተማ አቃቤ ህግ ማክሰኞ እለት “ተጨማሪ ኃይል ማሰማራቱ አስፈላጊ አይደለም” ሲሉ የአስተዳደራቸውን አቋም አንጸባርቀዋል።

“የአካባቢው ህግ አስከባሪ አካላት ሁኔታውን ለመቋቋም ከአቅማቸው በላይ የሆነበት ደረጃ ላይ አልደረስንም” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የሎስ አንጀለስ ከንቲባ ካረን ባስ በከተማዋ የተነሳውን ሁከት ተከትሎ የሰዓት ዕላፊ አዋጅ ጥለዋል።

የሰዓት ዕላፊው ከምሽቱ 2 ሰዓት እስከ ጥዋቱ 12 ሰዓት እንደሚዘልቅ የተናገሩት ከንቲባዋ በከተማዋ ከፍተኛ ጉዳት ስለደረሰ አስፈላጊ ነው ሲሉ አጽንኦት ሰጥተዋል።

ከንቲባዋ ከተመረጡ አመራሮች እና ከህግ አስከሪ አካላት ጋር ምክክር እንደሚያደርጉ ተናግረው፤ ነገር ግን የሰዓት ዕላፊ አዋጁ ለበርካታ ቀናት እንደሚቆይ እንጠብቃለን ብለዋል።

በከተማዋ የሰዓት እላፊ ቢታወጅም ተቃዋሚዎች ከጸጥታ ኃይላት ጋር እንደተፋጠጡ ናቸው።

“ይህ ህገወጥ ተቃውሞ እንደሆነና አካባቢው ለቀው የማይሄዱ ከሆነ እንደሚታሰሩ” የሚነገሩ ማስጠንቀቂያዎች በከተማዋ እየተሰማ ይገኛል።

በአሜሪካ የኢሚግሬሽን እና ጉምሩክ ባለስልጣን (አይስ) የተነሳው ተቃውሞ በሌሎች ከተሞች እየተቀጣጠለ ሲሆን በኒውዮርክም በርካታ ሰዎች መታሰራቸውን የከተማዋ ፖሊስ አስታውቋል።