ዳታን በመቆጠብ ጽሑፍ ብቻ ለማንበብ

የአዲስ አበባ ከተማ ህንጻዎችን

11 ሰኔ 2025, 06:37 EAT

በቀጣይ ዓመት የፌደራል መንግሥት አጠቃላይ በጀት ውስጥ ባልተለመደ ሁኔታ ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሚደረግ የበጀት ድጋፍ ሳይካተት ቀረበ። በቀጣዩ ዓመት በጀት ውስጥ ለክልሎች እና ለድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር የተመደበው የፌደራል መንግሥት የበጀት ድጋፍ፤ ከዘንድሮው ጋር ሲነጻጸር በ92 ቢሊዮን ብር አድጓል።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማክሰኞ ሰኔ 3/2017 ዓ.ም. ባደረገው መደበኛ ስብሰባ የቀረበለትን የ2018 ዓ.ም. የፌደራል መንግሥት ረቂቅ በጀት ለተጨማሪ ዝርዝር ዕይታ ወደ የፕላን፣ በጀት እና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መርቷል።

ወደ ሁለት ትሪሊዮን ብር የተጠጋው የኢትዮጵያ መንግሥት የቀጣዩ ዓመት በጀት እየተጠናቀቀ ካለቀው ዓመት ጋር ሲነጻጻር በ24 በመቶ ክፍ ያለ ነው።

በቀጣዩ ዓመት በጀት ውስጥ ከግማሽ በላይ የሆነው 1.18 ትሪሊዮን ብር የተመደበው ለመደበኛ ወጪዎች ነው። ለመደበኛ ወጪ ከተመደበው ከዚህ ገንዘብ ውስጥ ደግሞ ዕዳ ክፍያ ከፍተኛውን ድርሻ ይይዛል።

ለካፒታል ወጪዎች የተመደበው በጀት 415.23 ቢሊዮን ብር ነው። ይህ ገንዘብ ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር የ62 ቢሊዮን ብር ጭማሪ ቢኖረውም፤ ለካፒታል ወጪዎች የሚመደበው ገንዘብ ከአጠቃላይ በጀት ውስጥ ያለው ድርሻ እንዳለፉት አምስት ዓመታት ሁሉ በቀጣዩ ዓመትም ቀንሷል።

በ2018 ዓ.ም. በጀት ውስጥ ሦስተኛውን ድርሻ የያዘው የፌደራል መንግሥት ለክልሎች የሚያደርገው የበጀት ድጋፍ ሲሆን ለክልሎች በበጀት ድጋፍነት እንዲተላለፍ የተመደበው 314.75 ቢሊዮን ብር ነው።

ይህ የገንዘብ መጠን በዘንድሮው ዓመት ለክልሎች ተመድቦ ከነበረው 222.69 ቢሊዮን ብር ጋር ሲጻጸር የ92 ቢሊዮን ብር ጭማሪ አሳይቷል።

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረቡት የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ በዘንድሮው ዓመት ለመንግሥት ሠራተኞች የደመወዝ ማሻሻያ ሲደረግ ክልሎች ያስፈልጋቸው የነበረውን ተጨማሪ ገንዘብ የሸፈነው የፌደራል መንግሥት መሆኑን ተናግረዋል።

ለክልሎች የሚሰጠው የበጀት ድጋፍ የተዘጋጀው ክልሎች በደመወዝ ማሻሻያ ምክንያት ያስፈለጋቸው ተጨማሪ ወጪ ተሰልቶ፣ ባለፈው ዓመት የተመደበላቸው በጀት ተደምሮ እንዲሁም “መነሻ ተወስዶ” መሆኑን አስረድተዋል።

በዚህ የድጋፍ በጀት ድልድል ውስጥ ከፍተኛውን የገንዘብ መጠን የሚያገኘው ኦሮሚያ ክልል፤ 108.46 ቢሊዮን ብር ተመድቦለታል። ክልሉ ለቀጣዩ ዓመት የተያዘለት ፌደራል መንግሥት ድጋፍ ዘንድሮ ካገኘው ገንዘብ በ33.61 ቢሊዮን ብር ያደገ ነው።

ኦሮሚያ ክልል ያገኘው ጭማሪ፤ በሦስተኛ ደረጃ የተቀመጠው የሶማሌ ክልል ለቀጣዩ ዓመት ከተመደበለት 31.41 ቢሊዮን ብር ይበልጣል።

በሁለተኛ ደረጃ የተቀመጠው አማራ ክልል ለቀጣዩ ዓመት የተመደበለት የድጋፍ በጀት ከዘንድሮው የ21 ቢሊዮን ብር ጭማሪ አለው። ክልሉ በ2018 ከፌደራል መንግሥት የሚያገኘው የበጀት ድጋፍ 67.98 ቢሊዮን ብር ነው።

በአራተኛ ደረጃ ከፍተኛ ድጋፍ የተመደበለት ደቡብ ኢትዮጵያ ክልል 22 ቢሊዮን ብር ያገኛል። ትግራይ ክልል ደግሞ 18.97 ቢሊዮን ብር ተመድቦለታል።

የፌደራል መንግሥት ለምክር ቤቱ ያቀረበው የ2018 በጀት ረቂቅ አዋጅ እና ሌሎች አስረጂ ሰነዶች የዘረዘሩት የሀገሪቱን 12 ክልሎች እና የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ብቻ የሚያገኙትን የበጀት ድጋፍ ነው።

የፌደራል መንግስት ለክልሎች የመደበውን ገንዘብ የሚያሳይ ሰንጠረዥ

በገንዘብ ሚኒስቴር የተዘጋጁት የበጀት ሰነዶች በፌደራል መንግሥት የበጀትም ሆነ የዘላቂ ልማት ግቦች ማስፈጸሚያ ድጋፎች ውስጥ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርን አላካተቱም።

እስካሁን በነበረው አሠራር የአዲስ አበባ ከተማ ከክልሎች እና ከድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ጋር በተመሳሳይ የበጀት ድጋፍ እና የዘላቂ ልማት ግቦች ማስፈጸሚያ ድጋፍ ድልድሎች ውስጥ ይካተት ነበር። በ2017 በጀት ላይ ለአዲስ አበባ ከተማ ተመድቦ የነበረው የበጀት ድጋፍ 5.4 ቢሊዮን ብር ነው።

ባለፉት ዓመታት ዓመታዊ በጀቱ በከፍተኛ መጠን እያደገ የመጣው አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፤ ባለፈው ሚያዝያ ያጸደቀውን ተጨማሪ ገንዘብ ጨምሮ ዘንድሮ አጠቃላይ በጀቱ 241.8 ቢሊዮን ብር ደርሷል።

የከተማ አስተዳደሩ ባለፉት ዓመታት የበጀት ዕቅዱን ሲያጸድቅ በሚዘረዝራቸው የገቢ ምንጮች ውስጥ ከሌሎች ክልሎች በተለየ ከፌደራል መንግሥት የሚመደብለትን የድጋፍ ገንዘብ አላካተተም።

የከተማ አስተዳደሩ በበጀት ዕቅዱ በገቢ ምንጭነት ታሳቢ የሚያደርጋቸው ዋነኛ ዘርፎች ታክስ፣ ታክስ ያልሆኑ ገቢዎች፣ ማዘጋጃ ቤታዊ ገቢዎች እና የመንገድ ፈንድ ናቸው። ከውጭ እርዳታ እና ብድር የሚገኝ ገንዘብም ሌላኛው የከተማ አስተዳደሩ የበጀት ምንጭ ነው።

ከሦስት ዓመት ገደማ በፊት የ2016 በጀት ለከተማ አስተዳደሩ ምክር ቤት በቀረበበት ወቅት አዲስ አበባ ከፌደራል መንግሥት “ሊያገኝ የሚገባው ድርሻ” በገቢ ምንጭነት አለመካተቱ ጥያቄ አስነስቶ ነበር።

በወቅቱ ለዚህ ጥያቄ ምላሽ የሰጡት ከንቲባ አዳነች አቤቤ፤ የፌደራል መንግሥት የድጎማ በጀት “ሊሰጥ የሚችል” ቢሆንም “በአንጻራዊነት” የከተማ አስተዳደሩ “የራሱን በጀት መሸፈን ያልቻለበት ትልቅ ችግር አለማጋጠሙን” ተናግረው ነበር።

የከተማ አስተዳደሩ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን ዕቅድ ለፌደራል መንግሥት በማቅረብ እርዳታ እና ብድር የሚገኝበትን መንገድ እንደሚያመቻች የጠቀሱት ከንቲባዋ፤ ከቀጥታ የበጀት ድጋፍ ውጪ ያሉ እና ፌደራል መንግሥት በአዲስ አበባ ከተማ የሚገነባቸው ፕሮጀክቶችም ከግምት ውስጥ መግባት እንዳለባቸው አሳስበዋል።

ጉዳዩን “ትንሽ ፖለቲሳይዝድ ማድረግ እንደተፈለገ” በማንሳት የተቹት ከንቲባ አዳነች፤ “የአዲስ አበበ ከተማ ሕዝብ ከፌደራል በጀት የሚነፈገው ወይም የተለየ ተጽዕኖ የሚደረግበት” እንዳልሆነ አስረድተው ነበር።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በዘንድሮው የፌደራል መንግሥት የበጀት ድጋፍ ውስጥ ስላለመካተቱ ጥያቄ ከቢቢሲ የቀረበላቸው የከተማዋ ፋይናንስ ቢሮ ኃላፊ አቶ አብዱልቃድር ሬድዋን፤ የበጀት “ዝርዝሩን ባለመመልከታቸው” አስተያየት ለመስጠት እንደማይችሉ ተናግረዋል።

ቢቢሲ በጉዳዩ ላይ ከገንዘብ ሚኒስቴር ማብራሪያ ለማግኘት ያደረጋቸው ጥረቶች አልተሳኩም።