
ከ 9 ሰአት በፊት
በእጮኛው ቀነኒ አዱኛ ሞት ተጠርጥሮ በእስር ላይ የነበረው ሙዚቀኛ አንዱአለም ጎሳ ላይ ዐቃቤ ሕግ ክስ ባለመመሥረቱ በዋስ መለቀቁን ጠበቃው ሊበን አብዲ ለቢቢሲ ተናገሩ።
ከእጮኛው ሞት በኋላ ለሶስት ወራት በእስር ላይ የቆየው አንዱዓለም ጎሳ በ50 ሺህ ብር ዋስ ማክሰኞ፣ ሰኔ 3/2017 ዓ.ም. መፈታቱን ጠበቃው ገልጸዋል።
የሕግ ባለሙያው ለቢቢሲ እንደገለጹት ላለፉት ሦስት ወራት ክሱ በፍርድ ቤት ሲታይ የነበረው አንዱዓለም ጎሳ ላይ ዐቃቤ ሕግ በተሰጠው ጊዜ ክስ ባለመሥረቱ በዋስ እንዲፈታ ፍርድ ቤቱ ብያኔ አስተላልፏል ብለዋል።
“ባለፉት ጥቂት ወራት ፖሊስ ምርመራዎችን ሲያደርግ ቆይቷል። ፖሊስ ግንቦት 15/2017 ዓ.ም. ምርመራውን አጠናቆ ጉዳዩን ለዐቃቤ ሕግ አስተላልፏል” ብለዋል።
ጠበቃው ዐቃቤ ሕግ የፖሊስ ምርመራ በደረሰው በ15 ቀናት ውስጥ ክስ መመሥረት አለበት ይላሉ።
ነገር ዐቃቤ ሕግ እስከ ግንቦት 30/2017 ዓ.ም. ድረስ ክስ እንዲመሠርት ወይም “ምርመራው በቂ አይደለም ብሎ መዝገቡን መዝጋት ቢኖርበትም” ይህንን አላደረገም ብለዋል።
ዐቃቤ ሕግ የፖሊስ ምርመራ በደረሰው በ15 ቀናት ውስጥ ክስ ካልመሠረተ “ከሕግ ውጪ ታስሯል” ተብሎ ስለሚታሰብ የደንበኛቸው አካልን ነጻ የማውጣት ጥያቄ እንዲከበርላቸው ጠበቃው ለፍርድ ቤቱ መጠየቃቸውን ገልጸዋል።
ፍርድ ቤቱ የተጠርጣሪውን ጥያቄ ተመልክቶ አንዱአለም ጎሳ በዋስ እንዲፈታ ብያኔ መስጠቱ ተነግሯል።
የሙዚቀኛው በዋስ የመፈታትን ውሳኔ በተመለከተ የሟች ቀነኑ አባት አቶ አዱኛ ዋቆ “ልጄን ለሁለተኛ ጊዜ ነው የገደሏት” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
“እስከዚች ሰዓት ድረስ ፖሊስም ሆነ ዐቃቤ ሕግ እዚህ ላይ ደርሰናል ብለው በግልጽ የነገሩን ነገር የለም። እንዲሁ በብላሽ ሦስት ወራት ነጉዷል። የልጃችንን ደምም፣ እውነታም አላገኘንም። ልጄን ለሁለተኛ ጊዜ ነው የገደሏት” ብለዋል።
ከዚህ በኋላ ምን እንደሚያደርጉ ቢቢሲ ላቀረበላቸው ጥያቄ “ሕግ ውስብስብ ነው፤ ዐቃቤ ሕግ የሚለውን አይተን ለአምላክ እንሰጣለን፤ እንደ ሰው የምንለው ነገር የለም። ቀነኒ ፍትህ እየተነፈገች ነው። ከጅምሩ አንስቶ የነበረ ነው። እኛን ለማድከም እስካሁን አቆዩን እንጂ ሊለቁት ከፈለጉ ቆይቷል” ብለዋል።
አክለውም በዚህ አካሄድ “እንሞክር ብለን እንጂ ፍትህ እናገኛለን ብለን አናስብም። ከእሷ ደም የልጁ ታዋቂነት ይበልጣል” ብለዋል።

ሞዴል እንዲሁም የማስታወቂያ ባለሙያ የነበረችው ቀነኒ አዱኛ መጋቢት 01/2017 ዓ.ም. ሌሊት 10 ሰዓት አካባቢ ከእጮኛዋ ጋር ከሚኖሩበት ውዳሴ ከተሰኘው ሕንጻ 5ኛ ፎቅ በረንዳ ላይ ለጊዜው ምክንያቱ ባልታወቀ ሁኔታ መውደቋ ለህልፈቷ ምክንያት መሆኑን ፖሊስ አመልክቷል።
ከቀነኒ ሞት ጋር ተያይዞ በግድያ ተጠርጥሮ የታሰረው እጮዋ አንዱአለም ጎሳ ከዚህ ቀደም በዋስትና እንዲወጣ የቀረበው ጥያቄ “በነፍስ ግድያ የተጠረጠረ በመሆኑ” እንዲሁም ማስረጃዎችን ያሸሻል በሚል ውድቅ መደረጉ ይታወሳል።
ቀጣዩ ሂደት ምን ይሆናል? በሚል ቢቢሲ የጠየቃቸው የሙዚቀኛው ጠበቃ “እስካሁን የፍርድ ቤት ቀጠሮ አልተሰጠውም። የዐቃቤ ሕግን ውሳኔ እየጠበቅን ነው፤ ክስ ለመመሥረትም ሆነ መዝገቡን ለመዝጋት የሚሰጠኑን ውሳኔ ግልባጭ የምንጠብቅ ይሆናል” ብለዋል።
የቀነኒ አባት አዱኛ ዋቆ ከዚህ ቀደም ከቢቢሲ ኦሮምኛ ጋር ባደረጉት ልዩ ቃለ ምልልስ ልጃቸው ከፎቅ ወድቃ ሞታለች ብለው እንደማያምኑ ተናግረዋል።
“ደውለው ልጅቷ ከፎቅ ወድቃለች ብለው ተናገሩ።… ልጅቱ ከፎቅ ላይ አትወድቅም። የተረጋጋች፣ ለለውጥ የምትሠራ፣ ራሷን የምትቀይር፣ ቤተሰቧን ለመለወጥ የምትሠራ ናት። ስለ ነገ ታስባለች፤ እንደዚህ ዓይነት ተልካሻ ነገር አታደርግም።”
“ራሷን ከፎቅ ወረወረች የሚለው ነገር አይዋጥልኝም. . . ሰው ጎድቷት፤ እንድታደርርግ ገፋፍቷት ካልሆነ በስተቀር” ብለዋል።
“እኛ የምንፈልገው ፍትህ ብቻ ነው። እኛ የምንፈልገው የልጃችንን ደም እንጂ ሌላ አይደለም” ሲሉም አክለው ተናግረው ነበር።
አስከትለውም ሆኖም አንዱአለም እና ቀነኒ “ጥሩ ግንኙነት እንዳላቸው አውቃለሁ” ብለዋል።
በምዕራብ ሐረርጌ ዞን ዳሮ ላቡ ወረዳ በሚጨታ ከተማ የተወለደችው ቀነኒ፣ ከልጅነቷ ጀምሮ በትምህርቷ ጠንካራ እንደነበረች የሕይወት ታሪኳ ያስረዳል።
በ25 ዓመቷ ሕይወቷ ያለፈው ቀነኒ በ2011 ዓ.ም. ከአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በሃይድሮሊክ እና ዋተር ኢንጅነሪንግ ተመርቃለች።
ከዚያ በኋላም በኦሮሚያ ውሃ እና ኢነርጂ ቢሮ ለተወሰነ ጊዜ ሰርታለች።
ቀነኒ በሞዴሊንግ፣ በማስታወቂያ እና በመዝናኛ ሥራዎቿ ትታወቃለች።