
10 ሰኔ 2025
የ’ኢትዮጵያ ኢንሳይደር’ የበይነ-መረብ ሚዲያ መሥራች እና ዋና አዘጋጅ ጋዜጠኛ ተስፋለም ወልደየስ በፀጥታ ኃይሎች ቁጥጥር ሥር ከዋለ በኋላ ፍርድ ቤት በዋስ እንዲለቀቅ ቢፈቅድም በእስር ላይ እንደሚገኝ ተገለጸ።
ባለፈው እሁድ አዲስ አበባ ግዮን ሆቴል ቅጥር ግቢ ውስጥ ሲቪል በለበሱ የፀጥታ ኃይሎች በቁጥጥር ሥር የዋለው ተስፋለም መጀመሪያ እስጢፋኖስ አካባቢ በሚገኝ የፖሊስ መምሪያ ቀጥሎም ቄራ አካባቢ ወደሚገኝ የፖሊስ መምሪያ ውስጥ በእስር ላይ ቆይቷል።
ዛሬ ማክሰኞ ሰኔ 3/2017 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከተማ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት፣ ቂርቆስ ምድብ ችሎት ቀርቦ በ15,000 ብር ዋስትና እንዲፈታ ተወስኖ ገንዘብ ከተከፈለ በኋላ እንዳልተፈታ ተገልጿል። ፖሊስ ይግባኝ እንደሚጠይቅ ቢገልጽም በተገቢው መንገድ ይግባኙ አልቀረበም ተብሏል።
ተስፋለም ፍርድ ቤት ቀርቦ በዋስ እንዲፈታ ትዕዛዝ በተሰጠበት ደብዳቤ ላይ “ሐሰተኛ መረጃ በማሠራጨት” ተጠርጥሮ መያዙ ተጠቅሷል።
ጠበቃው አቶ ቤተማሪያም አለማየሁ፣ጋዜጠኛው ሰኔ 1/2017 ዓ.ም. ግዮን ሆቴል በስልክ እያወራ ሳለ በደኅነንት አባላት በቁጥጥር ሥር መዋሉን ለቢቢሲ ገልጸዋል።
“በዕለቱ በወላይታ ዲቻ እና በሲዳማ ቡና መካከል ይደረግ የነበረ እግር ኳስ ውድድር ስለነበር፣ ደጋፊዎች ስታዲዮም ገብተው መከታተል እንደማይችሉና ጨዋታው በዝግ ይካሄድ እንደነበር ቀደም ሲል ተዘግቦ ስለነበር በዚህ ዙሪያ ከጓደኞቹ ጋር በስልክ እያወራ በነበረበት ጊዜ ነው የተያዘው” ብለዋል።
የደኅንነት አባላቱ ተስፋለምን “ምንድን ነው የምታወራው? ከማን ጋር ነው የምታወራው?” በማለት ስልኩን ወስደው፣ ከዚህ ቀደም የተሠሩ የኢትዮጵያ ኢንሳይደር ዘገባዎች ስልኩ ላይ ስለነበሩ እሱን ተመልክተው እስጢፋኖስ አካባቢ ወደሚገኝ የፖሊስ ማቆያ ወስደው እንዳሰሩት ገልጸዋል።
ፖሊስ በችሎት ላይ “ሐሰተኛ መረጃ ሲያሰራጭ ደርሰንበታል። ሰኔ 1/2017 ዓ.ም ከቀኑ 9፡00 ሰዓት ላይ የሲዳማ ቡና እና የወላይታ ዲቻ ደጋፊዎችን ሰብስቦ መንግሥት የሚፈራው የጃዋርን ንግግር ነው. . . በዚህ ጉዳይ ላይ የሆነ ነገር መደረግ አለበት እያለ ለእግር ኳስ ደጋፊዎች መልዕክት ሲያስተላልፍ ነበር” በማለት “ሐሰተኛ መረጃ ሲያስተላልፍ” እንደተያዘ መግለጹን ጠበቃው ተናግረዋል።
ሆኖም ጠበቃው ቤተማሪያም፣ “ጋዜጠኛ ተስፋለም በተባለው ቦታ ላይ ሳይሆን ግዮን ሆቴል መጽሐፍ እያነበበ እንደነበረ እና በወቅቱም በግል ከደወሉለት ሰዎች ጋር የስልክ ልውውጥ ከማድረግ ያለፈ ሰዎችን ሰብስቦ ያነጋገረው ነገር የለም። ለማንም ሰው ሐሰተኛ መረጃ አልሰጠም” ብለዋል።
ከሁለት ቀናት አስር በኋላ ዛሬ ፍርድ ቤት ቀርቦ የዋስትና መብት ቢፈቀድለትም በእስር ላይ ለሚገኝበት ፖሊስ መምሪያ የተጻፈው የማስፈቻ ደብዳቤ በሚመለከተው የፖሊስ መኮንን ሳይፈረምበት በመቅረቱ አሁንም በእስር ላይ እንደሚገኝ ተገልጿል።
በዚህም ምክንያት እስከ ማክሰኞ አመሻሽ ድረስ ጋዜጠኛ ተስፋለም ወልደየስ “በፍርድ ቤት የተረጋገጠለት የዋስትና መብት አልተከበረም” ሲል ‘ኢትዮጵያ ኢንሳይደር’ ባለቤት የሆነው ሐቅ ሚዲያና ኮሚኒኬሽን ባወጣው መግለጫ ላይ አመልክቷል።
ተስፋለም ወደልደየስ ዜናና ትንታኔ የሚቀርብበት ‘ኢትዮጵያ ኢንሳይደር’ የተባለው ድረገጽ መስራችና ዋና አዘጋጅ ሲሆን፤ ገጹ በተለይ ወቅታዊ የፖለቲካ ዜናዎችን በማቅረብ እየታወቀ ያለ ከመሆኑ በተጨማሪ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይም በርካታ ተከታዮችን በማፍራት ላይ ያለ ነው።
ተስፋለም ከጋዜጠኝነት ሥራው ጋር በተያያዘ በተደጋጋሚ በፀጥታ ኃይሎች ተይዞ የታሰረ ሲሆን ከሦስት ዓመት በፊት መስከረም 22/2014 ዓ.ም. በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውሎ ለሦስት ቀናት እስር በኋላ የተለቀቀ ሲሆን፣ ከዓመታት በፊትም ከዞን ዘጠኝ ጦማሪዎች ጋር ለረጅም ጊዜ በእስር ላይ ቆይቷል።
ተስፋዓለም ከእስር ከወጣ በኋላ በኬንያና በኡጋንዳ ውስጥ በስደት በቆባቸው ጊዜያት ኢትዮጵያንና የአካባቢው አገራትን የሚመለከቱ ዜናና የተለያዩ ፊቸሮች የሚቀርቡበት ጋዜጣ ያዘጋጅ ነበር።
ተስፋለም በአገር ውስጥ በአዲስ ፎርቹን እና በአዲስ ነገር ጋዜጦች ላይ የሠራ ሲሆን ወደ ጀመርን በመሄድ የጀርመን ድምጽ የአማርኛው ክፍል ውስጥ ሲሰራ ነበር።ከዚያም ወደ ኢትዮጵያ ተመልሶ ኢትዮጵያ ኢንሳይደርን በመመሥረት እየሠራ ይገኛል።