
ከ 4 ሰአት በፊት
ረቡዕ ዕለት በምሽት የሚደረግ እንቅስቃሴ ላይ ገደብ ተጥሎባት የነበረችው ሎስ አንጀለስ የሰዓት እላፊው ከተነሳ በኋላ መረጋጋት ማሳየቷ ተገለፀ።
በሌሎች የአሜሪካ ከተሞች የሚካሄዱ ተቃውሞዎች ግን እንደቀጠሉ መሆናቸው ተገልጿል።
በሎስ አንጀለስ እስካሁን ወደ 400 የሚጠጉ ሰዎች በቁጥጥር ስር የዋሉ ሲሆን ከእነዚህም መካከል 330 ሕጋዊ ሰነድ የሌላቸው ስደተኞች ናቸው።
157 ሰዎች በቁጥጥር ስር የዋሉት ጥቃት በማድረስ እና የጸጥታ ኃይሎችን ስራ በማደናቀፍ ሲሆን አንድ የፖሊስ መኮንን ላይ የግድያ ሙከራን በማድረግ በቁጥጥር ስር የዋለ መኖሩ ተገልጿል።
የፌደራል አቃቤ ሕጎች እስካሁን በሁለት ግለሰቦች ላይ ተቀጣጣይ ነገር በፖሊስ አባላት ላይ በመወርወር ክስ መስርተዋል።
ሁከቱን ለማረጋጋት በድምሩ 4,000 የብሔራዊ ዘብ ወታደሮች እና 700 የባሕር ኃይል ወታደሮች ተሰማርተዋል።
ከእነዚያ የብሔራዊ ዘብ ወታደሮች መካከል አንዳንዶቹ ፖሊስ በቁጥጥር ስር እስከሚያውላቸው ድረስ ሰዎችን ማሰር እንደሚችሉ ተገልጿል።
የሎስ አንጀለስ ከንቲባ ካረን ባስ ረቡዕ ዕለት ከ30 ሌሎች ከንቲባዎች ጋር በመሆን በሰጡት መግለጫ ተቃውሞው የአሜሪካ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ስደተኞች ላይ በፈጸሙት አፈሳ የተቀሰቀሰ ነው ሲሉ ወቅሰዋል።
ይህም በነዋሪዎች ዘንድ “ፍርሃት” እና “ድንጋጤ” መፍጠሩን እና አፈሳው “ተቃውሞ ቀስቅሷል” ብለዋል።
“ከሳምንት በፊት ሁሉም ነገር ሰላማዊ ነበር” ያሉት ከንቲባዋ፣ “አርብ ዕለት ወረራ ሲፈጸም ነገሮች አስቸጋሪ መሆን ጀመሩ።”
ባስ ሎስ አንጀለስ “የፌዴራል መንግሥት ከአካባቢው አስተዳደር፣ ስልጣንን ለመቆጣጠር ምን ያህል ርቀት መሄድ እንደሚችል ለመወሰን የብሔራዊ ሙከራ አካል” እንደሆነች ጠቁመዋል።
ከንቲባዋ ከዚህ ቀደም አፈሳው እንዲቆም አስተዳደሩን ጠይቀው ነበር።
ሰነድ አልባ ዜጎችን ከአገር ማስወጣትን በመቃወም አደባባይ የወጡ ሰዎች አምስተኛ ቀናቸውን በያዙበት ከማክሰኞ ለሊት እስከ ረቡዕ ድረስ የሎስ አንጀለስ ፖሊስ በርካቶችን “በጅምላ ማሰሩን” ገልፀዋል።
የከተማው ፖሊስ መምሪያ ባወጣው ተከታታይ መግለጫ እንዳስታወቀው በቁጥጥር ስር ከዋሉት መካከል 203 ሰዎች ተበተኑ ሲባሉ አሻፈረኝ በማለታቸው ነው ብሏል።
17 ሰዎች ደግሞ የሰዓት እላፊ በመጣስ፣ ሦስት ደግሞ የጦር መሳሪያ በመያዝ እና አንድ በፖሊስ መኮንን ላይ የግድያ ሙከራ በማደረግ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ተናግሯል።
በግጭቱ ሁለት ፖሊሶች መቁሰላቸውን ተገልጿል።
ማክሰኞ ዕለት ባስ በከተማው መሀል በምትገኝ አንዲት አካባቢ ብቻ የንግድ ቤቶች እየወደሙ እና እየተዘረፉ መሆናቸውን ተከትሎ ለአንድ ሌሊት የሰዓት እላፊ አውጀዋል።
የሎስ አንጀለስ የሰዓት እላፊ ስራ ላይ ከዋለ በኋላ ፖሊስ ሠልፈኞችን ለመበተን የጎማ ጥይቶችን በመተኮስ በመሀል ከተማ አካባቢዎች ተንቀሳቅሰዋል።
ማክሰኞ የተጣለውን የሰዓት እላፊ በሚመለከት ባስ ሲናገሩ “ውድመትን እና ዘረፋውን ለማስቆም” እንደሚፈልጉ አብራርተዋል።
የሰዓት እላፊ ትዕዛዙ በዩናይትድ ስቴትስ ሁለተኛ ትልቅ ከተማ ውስጥ የሚገኝ ስፍራ ላይ ተጽዕኖ አሳድሯል።
የፖሊስ አዛዡ ጂም ማክዶኔል እንዳሉት “አንዳንድ የተቃውሞ እና የብጥብጥ ምስሎች አለመረጋጋቱ ከተማ አቀፍ ቀውስ ይመስላል፤ ግን አይደለም” ብለዋል።
የዩናይትድ ስቴትስ ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ፓም ቦንዲ ረቡዕ በዋይት ሐውስ ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት የሰዓት እላፊ እገዳው “ትንሽም ቢሆን ረድቷል” ብለዋል።
በሌላ ስፍራ ከብሔራዊ ዘብ ወታደሮች ጋር በመሆን ሰነድ አልባ ስደተኞችን ማፈሱ ቀጥሏል።
ማክሰኞ ዕለት በሌሎች በርካታ የአሜሪካ ከተሞች ተቃውሞዎች ተቀስቅሰዋል።
በአትላንታ፣ ጆርጂያ፣ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በተሳተፉበት ሰላማዊ ሠልፍ ላይ ፖሊሶች አስለቃሽ ጭስ ተጠቅመዋል።
የኒውዮርክ ፖሊስ ለቢቢሲ እንደገለፀው በሺዎች የሚቆጠሩ ሠልፈኞች ወደ ማንሃታን በመሄድ የተሽከርካሪዎች እንቅስቃሴን በመዝጋታቸው በቁጥጥር ስር ውለዋል።
የቴክሳስ አስተዳዳሪ ግሬግ አቦት ስደተኞችን በሚመለከት ሠልፎች ለማካሄድ ወደታቀዱበት ወደ ሳን አንቶኒዮ ብሔራዊ ዘብ ወታደሮችን ልከዋል።