
ከ 2 ሰአት በፊት
የቀድሞ የሲአይኤ ባልደረባ እስራኤል ኢራን ላይ ለመፈፀም ስላቀደችው ጥቃት የሚገልጽ ሚስጥራዊ ሰነድ አሳልፎ በመስጠቱ የ37 ወራት ተፈረደበት።
የ34 ዓመቱ አሲፍ ዊሊያም ራህማን በጥር ወር በሁለት ክሶች ጥፋተኛ መሆኑ ተረጋግጧል።
ባለስልጣናት እንዳሉት ራህማን በደህንነቱ ተቋም ውስጥ ያለውን ዕድል ተጠቅሞ ከፍተኛ ምስጢራዊ የሆኑ ሰነዶችን አትሞ እና ፎቶ አንስቶ መላኩን ተናግረዋል።
እስራኤል ባለፈው ጥቅምት ወር ቴህራን በርካታ ሚሳዔሎችን ወደ እስራኤል ማስወንጨፏን ተከትሎ በኢራን የተለያዩ ግዛቶች የሚገኙ ወታደራዊ ዒላማዎች ላይ የአየር ድብደባ ፈጽማለች።
የብሔራዊ ደኅንነት ዋና አቃቤ ሕግ ረዳት ጆን አይዘንበርግ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫው ላይ “ይህ ተከሳሽ ለወራት የአሜሪካን ሕዝብ እና ሲቀጠር የገባውን ቃለ መሃላ ክዶ አገራችንን በቅርበት የያዘቻቸውን ሚስጥሮችን አሳልፎ ሰጥቷል” ብለዋል።
በጥቅምት 2024 ከመከላከያ ኤጀንሲ የወጡ የሚመስሉ ሰነዶች ከኢራን ጋር ግንኙነት ባለው የቴሌግራም ገጽ ላይ ታትመዋል።
ሰነዶቹ፣ ጥብቅ ሚስጥር የሚል ምልክት የሰፈረባቸው ሲሆን፣ በአሜሪካ፣ ብሪታንያ፣ ካናዳ፣ ኒውዚላንድ እና አውስትራሊያ የስለላ ቡድኖች ተመለከተዋቸዋል።
ሾልከው የወጡ ሰነዶች አሜሪካ በኢራን ላይ ከምትፈጽመው ጥቃት በፊት እና በወታደራዊ መሳርያዎች እንቅስቃሴ ላይ የእስራኤልን እቅድ በተመለከተ የወሰደችውን ግምገማ አካትቷል ተብሏል።
አንደኛው ሰነድ የእስራኤልን የኒውክሌር አቅምን የሚያመለክት ሲሆን ይህም በይፋ እስካሁን ድረስ እውቅና አግኝቶ አያውቅም።
የቀድሞው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ስለ ሾለከው ሰነድ ተጠይቀው “በጣም አሳስቦኛል” ማለታቸው ይታወሳል።
ከሳምንታት በፊት በቴህራን ለተተኮሱ ሚሳኤሎች ምላሽ ለመስጠት እስራኤል የአየር ጥቃቶች በጥቅምት ወር መገባደጃ ላይ በበርካታ የኢራን ግዛቶች በሚገኙ ወታደራዊ ሠፈሮችን ዒላማ አድርጋ ደብድባለች።
በውጭ አገር ይሰራ የነበረው ራህማን፣ በካምቦዲያ በ ኤፍቢአይ ተይዞ ክስ ለመመስረት ወደ አሜሪካ ግዛት ጉዋም ተወስዷል።