
ከ 5 ሰአት በፊት
የዓለማችን ታላላቅ ምጣኔ ኃብት ባለቤቶች ቻይና እና አሜሪካ በመካከላቸው ያለውን የንግድ ውጥረት ለማርገብ በመርኅ ደረጃ አንድ የስምምነት ማዕቀፍ ላይ መድረሳቸውን ተናግረዋል።
የአሜሪካ የንግድ መሥሪያ ቤት ኃላፊ ሐዋርድ ሉትኒክ የስምምነቱ ማዕቀፍ በብርቅዬ የምድር ማዕድናት እና ማግኔቶች ላይ የተጣለውን ገደብ እልባት ሊሰጠው እንደሚገባ ይናገራሉ።
የሁለቱም አገራት ልዑካን የስምምነቱ ዕቅድ ተፈጻሚ እንዲሆን ወደ የአገራቱ መሪዎች ዶናልድ ትራምፕ እና ፕሬዝዳንት ዢ ጂንፒንግ እንደሚወስዱት ገልጸዋል።
ከሁለቱ አገራት የተውጣጡ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ለሁለት ቀናት የዘለቀ ድርድር በለንደን ካካሄዱ በኋላ ነው ይህንን ያሉት።
ቻይና ለዘመናዊ ቴክኖሎጂ መሠረታዊ ግብዓት የሚባሉት ብርቅዬ የምድር ማዕድናትን በወጭ ንግድ መላኳ ከስብሰባዎቹ ዋነኛ አጀንዳዎች መካከል ነበር።
ባለፈው ወር አሜሪካ እና ቤይጂንግ በታሪፍ ላይ የገቡትን ጦርነት መፍትሄ ለማበጀት ጊዜያዊ እርቅ ላይ ቢደርሱም ስምምነቱን በመጣስ መወነጃጀላቸው አልቀረም።
ቻይና ከተንቀሳቃሽ ስልክ እስከ ኤሌክትሪክ መኪኖች ለማምረት አስፈላጊ የሆኑ ብርቅዬ የምድር ማዕድናትን እና ማግኔቶችን ወደ ውጭ ለመላክ ዳተኝነት አሳይታለች ስትል አሜሪካ ተችታታለች።
አሜሪካ በበኩሏ እንደ ሴሚኮንዳክተር ያሉ የኤሌክትሪክ ማስተላላፊያዎች እንዲሁም ከሰው ሰራሽ አስተውሎት (ኤአይ) ጋር የተገናኙ የቴክኖሎጂ ምርቶቿ ላይ የቻይናን ተደራሽነት ገድባለች ተብሏል።
በአሁኑ ወቅት ቻይና እና አሜሪካ የስምምነት ማዕቀፍ ላይ የደረሱ ሲሆን፣ ስምምነቱ ከሁለቱ አገራት መሪዎች ይሁንታ ከተገኘ በኋላ ይጸድቃል ተብሏል።
ይህ ድርድር ባለፈው ሳምንት ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ እና ፕሬዝዳንት ዢ ጂንፒንግ ያደረጉትን የስልክ ውይይት ተከትሎ ነው። ትራምፕ ከቻይና አቻቸው ጋር ያደረጉትን ውይይት “በጣም ጥሩ” ሲሉ ገልጸውታል።
“ሁለቱ ወገኖች በመርኅ ደረጃ መሪዎቹ ግንቦት 28/2017 ዓ.ም. ያደረጉትን ውይይት እንዲሁም ከዚያ በፊት በነበረው በጄኔቫ ስብሰባ ላይ ተመርኩዘው ተግባራዊ ሊሆን የሚችል የስምምነት ማዕቀፍ ላይ ደርሰዋል” ሲሉ የቻይና ምክትል የንግድ ሚኒስትር ሊ ቸንጋንግ ተናግረዋል።
ትራምፕ ወደ አሜሪካ በሚገቡ በበርካታ አገራት ምርቶች ላይ ታሪፍ ሲጥሉ በከፍተኛ ሁኔታ የተመታችው ቻይና ነበረች።
ቻይናም በአጸፋው በአሜሪካ ምርቶች ላይ ታሪፍ የጣለች ሲሆን፤ ይህም አገራቱ እርስ በርስ የጣሉትን ታሪፍ 145 በመቶ እንዲያሻቅብ አድርጎታል።
ግንቦት ወር ላይ በስዊትዘርላንድ በተካሄደ ውይይት ሁለቱ አገራት ጊዜያዊ እርቅ ላይ ደርሰው ነበር።
በዚህም ውይይት አሜሪካ በቻይና ላይ የጣለችው ታሪፍ ወደ 30 በመቶ ዝቅ እንዲል እንዲሁም ቻይና በአሜሪካ ላይ የጣለችው ወደ 10 በመቶ እንዲሆን ተስማምተዋል።
በተጨማሪም ወሳኝ የሆኑ ማዕድናት ላይ የተጣለው ገደብ እንዲነሳ ጊዜያዊ እርቅ ላይ ደርሰዋል። ሁለቱም አገራት በዚህ እርቅ መሠረት የንግድ ስምምነት ላይ እንዲደርሱ የ90 ቀናት ገደብ ተቀምጦ ነበር።
ነገር ግን ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ሁለቱም አገራት ከታሪፍ ውጪ የተገቡ ቃሎችን በመጣስ ተወነጃጅለዋል።
የአሜሪካ የንግድ ተወካይ ጄሚሶን ግሪር ቻይና በብርቅዬ የምድር ማዕድናት እና ማግኔቶች ላይ የጣለቻቸውን ገደቦች ማንሳት አልቻለችም ሲሉ ወቅሰዋል።
ቻይና በበኩሏ አሜሪካ የኮምፒውተር ቺፕ ዲዛይን ሶፍትዌሮችን ለቻይና ኩባንያዎች እንዳይሸጡ በማስቆም እንዲሁም በቻይናው ግዙፉ የቴክኖሎጂ ኩባንያ ሁዋዌ የተሠሩ ቺፖች ላይ ማስጠንቀቂያ በማውጣት ገደቦችን ጥላለች ስትል ተችታለች።
በተጨማሪም በአሜሪካ የቻይና ተማሪዎችን ቪዛ ሰርዛለች ስትል ቻይና ወቅሳለች።
የአሁኑ ንግግር ከመደረጉ በፊት የቻይና የንግድ ሚኒስቴር የብርቅዬ የምድር ማዕድናት የውጭ ንግድ ፈቃድ ውስን ለሆኑ ማመልከቻዎች መፍቀዷን አስታውቋል።
ነገር ግን ለየትኞቹ አገራት እንደተፈቀደ በዝርዝር አልተገለጸም።
ትራምፕ በበኩላቸው ፕሬዝዳንት ዢ በምድር ማዕድናት ላይ ያለው ንግድ እንዲጀመር ተስማምተዋል ሲሉ ባለፈው አርብ ተናግረው ነበር።