ዳታን በመቆጠብ ጽሑፍ ብቻ ለማንበብ

ዶ/ር ሰለሞን ጉርሙ ቤካ
የምስሉ መግለጫ,ዶ/ር ሰለሞን ጉርሙ ቤካ

ከ 5 ሰአት በፊት

ከአምስት ዓመታት በፊት የመላው ዓለምን እንቅስቃሴ የገታው የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ የበረራውን ዘርፍ አንኮታኩቷል።

ቫይረሱ በበረራ ወቅት ሥርጭቱ እንዳይስፋፋ በማድረግ ከፍተኛ ድርሻ የነበራቸው የኤሮስፔስ ሜድስን (Aerospace medicine) ባለሙያዎች ናቸው።

ኤሮስፔስ ሜድስን ወይም አቪዬሽን ሜድስን (Aviation medicine) የአውሮፕላን አብራሪዎች፣ የበረራ መስተንግዶ ባለሙያዎች እና የጠፈርተኞችን ጤና ይከታተላል።

ዶ/ር ሰለሞን ጉርሙ ቤካ የአቪዬሽን እና የጠፈር ሕክምና ባለሙያ ናቸው።

ኒው ዚላንድ ከሚገኘው ዩኒቨርስቲ ኦፍ ኦታጎ በቅርቡ ፒኤችዲያቸውን ይዘዋል። ከዩኒቨርስቲው በአቪዬሽን ሜድስን ፒኤችዲ በማግኘት የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ናቸው።

የዶ/ር ሰለሞን ጥናት ፓይለቶች እና ኮቪድ-19ኝን ይመለከታል።

ዶ/ር ሰለሞን ለአሥርታት በኢትዮጵያ አየር ኃይል በቀዶ ሕክምና ባለሙያነት ሠርተዋል። ወደ ኒው ዚላንድ ለትምህርት በሄዱበት ወቅት ነበር ወረርሽኙ የተከሰተው።

ወረርሽኙ በዋናነት ከጎዳቸው ዘርፎች አንዱ አቪዬሽን ሲሆን፤ ቫይረሱ የአጭር እና የረዥም ጊዜ የጤና ችግርን አስከትሏል።

ዶ/ር ሰለሞን እንደሚሉት በአጭር ጊዜ፤ በተለይም ከኦክስጅን እጥረት ጋር በተያያዘ ከተከሰቱ የጤና እክሎች በተጨማሪ ወረርሽኙ አሁንም ድረስ የዘለቁ ችግሮችን ይዞ መጥቷል።

በቫይረሱ በመያዝ ሳቢያ ለረዥም ጊዜ ከሚቆዩ ችግሮች ውስጥ ዘለግ ላለ ጊዜ የሚቆይ ድካም እና የአእምሮ ጤና መታወክን ባለሙያው ይጠቅሳሉ።

በኮሮናቫይረስ ምክንያት የፓይለቶች የማሰላሰለል እና የመከወን ብቃት መታወክ (Cognitive impairment) የዶ/ር ሰለሞን የጥናት ትኩረት ነው።

“ፓይለቶች አካላዊ እና አእምሯዊ ጤናቸው መጠበቅ አለበት። ለረዥም ጊዜ በሚቆይ የኮቪድ ተጽዕኖ ምክንያት ከሚገጥሙ ችግሮች አንዱ ኮግኒቲቭ ኢምፔርመንት ነው” ይላሉ ባለሙያው።

ፓይለቶችን የሚቆጣጠሩ ተቋማት ባስቀመጡት ፖሊሲ መሠረት፤ በኮቪድ-19 ከተያዙ በኋላ ተጨማሪ ምርመራ እንዲያገኙ የተደረጉት ፓይለቶች ሆስፒታል የገቡት ብቻ ነበሩ።

ሆኖም ግን በቫይረሱ ምክንያት ሆስፒታል ያልገቡት ሰዎች ቁጥር እንደሚበልጥ ዶ/ር ሰለሞን ይናገራሉ።

ስለዚህም የወጣው የምርመራ ፖሊሲ ብዙ ፓይለቶችን እንደማያካትት ይገልጻሉ።

ጥናታቸው፤ መደበኛ የፓይለቶች የጤና ፍተሻ እንዳለ ሆኖ ከኮቪድ-19 ጋር በተገናኘም ምርመራ መደረግ አለበት የሚል ድምዳሜ ያስቀምጣል።

ኤሮስፔስ ሜድስን

ፓይለቶች የማሰላሰለል እና የመከወን ብቃት መታወክ ገጥሟቸው ከሆነ ማወቅ የሚቻልበትን መንገድ በጥናታቸው አግኝተዋል።

“ያስቀመጥኩት ቱል [ዘዴ] በምርመራ ወቅት ፍተሻ ለማድረግ የሚረዳ ነው” ይላሉ።

በጤና ምርመራ ወቅት፤ ፓይለቶች የአእምሮ ጤና እክል ካለባቸው ራሳቸው እንዲናገሩ እንደሚደረግ እና ሆኖም ግን ጥናቶች እንደሚያሳዩት ፓይለቶች ችግሩን ሊደብቁ ወይም ላያውቁ እንደሚችሉ ይናገራሉ።

“መደበቅ አለ። ወይም ደግሞ በጣም ጉልህ ችግር ካልሆነና ብዙ ችግር የማያደርስ ከሆነ ስለማያውቁት አይገልጹትም። በረራ በጣም ቁልፍ ነገር ስለሆነ ችግሩን ባያውቁት ወይም ባይናገሩት የሚያሳድረው ጉዳት የከፋ ነው።”

በጥናታቸው ያገኙትን የማሰላሰለል እና የመከወን ብቃት ችግር መለያ ለመተግበር ሥራዎች ጀምረዋል።

የኦታጎ ዩኒቨርስቲ በድረ ገጹ ስለ ዶ/ር ሰለሞን ባወጣው ጽሑፍ ላይ እንደሚለው፤ ለፓይለቶች በሚደረግ የሕክምና ምርመራ ውስጥ የሚካተት ከአእምሮ ብቃት ጋር የተገናኘ የምርመራ ስልትን በጥናታቸው አግኝተዋል።

በኒው ዚላንድና በሌሎችም ዓለም አቀፍ ጉባዔዎች በፓይለቶች ሕክምና ላይ የሠሩትን ጥናትም አቅርበዋል።

በተጨማሪም እአአ በ2022 የኒው ዚላንድ ሮያል ሶሳይቲ ሽልማት እና በ2023 የስፔስ ሜድስን አውትስታንዲንግ ሽልማትን ጨምሮ ሌሎችም ዓለም አቀፍ ዕውቅናዎች አግኝተዋል።

ዶ/ር ሰለሞን ጉርሙ ቤካ
የምስሉ መግለጫ,ዶ/ር ሰለሞን ጉርሙ ቤካ

ኤሮስፔስ ሜድስን ምንድን ነው?

ኤሮስፔስ ሜድስን የበረራ ባለሙያዎች እና የጠፈር ተጓዦችን ጤና ያጠናል። እያደጉ ከመጡ አዲስ የሳይንስ ዘርፎች አንዱ ነው።

በቀጣይ ዓመታት ለሰው ልጆች ዕድገት አስፈላጊ ከሆኑ የሳይንስ ዘርፎች አንዱ መሆኑን ዶ/ር ሰለሞን ይገልጻሉ።

አንደኛው የኤሮስፔስ ሜድስን ክፍል የጠፈርተኞች ጤና ላይ ያተኩራል። ወደ ሕዋ ከመጓዛቸው በፊትና ከተመለሱ በኋላም የሕክምና ክትትል ይደረግላቸዋል።

ለዚህ ምሳሌ እንዲሆነን የጡንቻ መኮማተር ወይም የአጥንት መሳሳት ሕመምን እንውሰድ። ይሄ በዕድሜ የገፉ ሰዎች የሚገጥማቸው ችግር ነው።

ነገር ግን ሕዋ ደርሰው የሚመጡ ሰዎችም ይገጥማቸዋል።

እነዚህ ያለ ዕድሜያቸው ችግሩ የገጠማቸው ጠፈርተኞች ላይ የሚሠራው ጥናት በዕድሜ ምክንያት የሚመጣውን የአጥንት መሳሳት ለመቅረፍ እንደሚውል ዶ/ር ሰለሞን ያስረዳሉ።

ዘርፉ ጠፈር ላይ የሚሠሩ ባለሙያዎች እንዲሁም ፓይለቶች እና የበረራ መስተንግዶ ሠራተኞች ጤናቸው እና ደኅንነታቸው የተጠበቀ እንዲሆን፣ ሥራቸውን በአግባቡ መወጣት እንዲችሉ ይረዳል።

ለጠፈር ጉዞ የሚመረጡት ምን ዓይነት ሰዎች ናቸው? የሚለውንም ዘርፉ ይመለከታል። በሥራው ውስጥ ከገቡ በኋላም ብቃታቸውን አስጠብቀው እንዲጓዙ ተከታታይ ክትትል ይደረግላቸዋል።

“ፓይለቶች ምርመራ በየጊዜው ይደረግላቸዋል። ያሉበት ወቅታዊ የጤና ሁኔታም ይፈተሻል። ዓለም አቀፍ ወረርሽኞች ሲከሰቱ የሥርጭቱን መጠን ለመቀነስ እና ለመቆጣጠር ዘርፉ ሚና አለው” ይላሉ ዶ/ር ሰለሞን።

ኤሮስፔስ ሜድስን

የሕዋ ጉዞ እና ሕክምና

ለመሆኑ ጠፈርተኞች ላይ የሚሠሩ ጥናቶች ለምን በተለየ ሁኔታ አስፈላጊ ሆኑ?

ሕዋ ምድር ላይ ካለው ከባቢ አየር የተለየ ነው። የመሬት ስበት ሕዋ ላይ ዜሮ ስለሆነ፣ ከፍተኛ ጨረራ ስላለ እና በአጠቃላይ ከባቢ አየሩ ከባድ ከመሆኑ ጋር በተያያዘ ጉዞው ለሰዎች ፈታኝ ነው።

በሕዋ ጉዞ የሚገጥሙ ችግሮች ላይ ጥናት ሲደረግ፤ ምድር ላይ ለሚከሰቱ ተመሳሳይ ችግሮች መፍትሔ ማግኛ አቋራጭ መንገድ እንደሆነ ዶ/ር ሰለሞን ይገልጻሉ።

የሰውነት ፈሳሽ የሚንቀሳቀስበት መንገድ ሕዋ ላይ ይለወጣል። ሕዋ ላይ የሚኖረው የልብ የደም ዝውውርም ይለወጣል።

ጠፈርተኞች በ24 ሰዓት ውስጥ ምድርን ቢያንስ 16 ጊዜ ስለሚዞሩ መሬት ላይ እና ሕዋ ላይ የሚኖረው እንቅልፍም የተለያየ ነው።

ስለዚህ ጠፈርተኞች ሰውነት ላይ ለውጦች ይስተዋላሉ። እነዚህ ለውጦችም ለምርምር ግብዓት ይሆናሉ።

“ከሕዋ ጋር በተያያዘ የሚሠሩ ጥናቶችን ወደ ምድር በማምጣት ችግሮችን መቅረፍ ይቻላል” ሲሉ ዶ/ር ሰለሞን ያስረዳሉ።

ለምሳሌ ከጨረራ ጋር የተገናኙ ችግሮች፣ ከዕይታ እና ከመስማት ጋር የተገናኙ ችግሮችም በሕዋ ላይ ሲከሰቱ የሚሠራው ጥናት በምድር ላይም የሚተገበር ነው።

ወደ ሕዋ ጠፈርተኞች ከመሄዳቸው በፊት ውስብስብ የሆነ ምርመራ ይደረግላቸዋል። መሬት ላይ ሳሉ ምግባቸው፣ የሚሠሩት የአካል ብቃት እንቅስቃሴ እና ሌሎችም ዝግጅቶች ይደረጋሉ።

አብዛኛውን ጊዜ ስድስት ወር ቆይተው ከሕዋ ወደ ምድር ይመለሳሉ። ምድር ላይ ሳሉ የተደረጉላቸው ምርመራዎች ከሕዋ ሲመለሱም ይደረጉላቸዋል።

በሁለቱ መካከል የተፈጠሩ ልዩነቶች ላይ ምርምር ይደረጋል ማለት ነው።

“መጀመሪያ የነበራቸው ቤዝላይን ተመልሰው ሲመጡ ካለው ጋር ያለው ልዩነት ለጥናት በጣም ጠቃሚ ነው” ይላሉ ዶ/ር ሰለሞን።

ጠፈርተኞች ቀድሞ የነበራቸውን አቋም እንዲይዙ የማገገሚያ ሕክምናዎች ይደረጉላቸዋል።

ኤሮስፔስ ሜድስን ገና ጅምር ላይ ያለ ሳይንስ እንደመሆኑ፤ ሳይንሱ አሁን ካለው በበለጠ ውጤቱ እየታየ የሚመጣውም በቀጣይ ዓመታት እንደሆነ ባለሙያው ያስረዳሉ።

ኤሮስፔስ ሜድስን

በረራ እና ሕክምና

ኤሮስፔስ ሜድስን ከበረራ እና ጤና ጋር የተገናኘም ዘርፍ ነው። ከበረራ ጋር በተያያዘ ሊከሰቱ የሚችሉ የጤና እክሎችን ለመከላከል ባለሙያዎች ይሠራሉ።

በየአውሮፕላን ማረፊያው የኤሮስፔስ ክሊኒኮች አሉ።

ከበረራ በፊት ተላላፊ በሽታ ያለባቸውን ሰዎች ወደ ለይቶ ማቆያ ማስገባት የሙያተኞቹ ድርሻ ይሆናል።

አውሮፕላን አብራሪዎች፣ የበረራ መስተንግዶ ሠራተኞች እና ተሳፋሪዎችንም ይጨምራል።

ለበረራ መስተንግዶ ሠራተኞች የመጀመሪያ ሕክምና እርዳታ ሥልጠና መስጠትን ጨምሮ ተላላፊ በሽታዎች ወደ ማኅበረሰቡ እንዳይሻገሩ ያደርጋሉ።

ተጓዦች በሚሄዱበት አገር ተላላፊ በሽታዎች ካሉ ክትባት መስጠት ከቅድመ ጥንቃቄዎች አንዱ እንደሆነ ዶ/ር ሰለሞን ይናገራሉ።

አቪዬሽን እና አፍሪካ

ዶ/ር ሰለሞን በአየር ኃይል የቀዶ ሕክምና ባለሙያ ሆነው እየሠሩ ሳለ ነበር የአሜሪካ አየር ኃይል ባለሙያዎች የአቪዬሽን ሜድስን እና ኤሮስፔስ ፊዚዮሎጂ ሥልጠና ለመስጠት ወደ አየር ኃይል የሄዱት።

“ያኔ ሳይንሱ አዲስ ነው። ሥልጠናው ሲሰጠን ለወደፊት አስፈላጊ የሆነና ለውጥ የሚያመጣ መሆኑን በማሰብ ወደ ዘርፉ ገባሁ።”

ከቀዶ ሕክምና ባለሙያነት ወደ ጥናትና ምርምር መሄድ “ቀላል እንዳልሆነ” ይናገራሉ።

“የመጀመሪያው በኤሮስፔስ ሜድስን ፒኤችዲ የሠራ ባለሙያ በመሆኔ ደስተኛ ነኝ። ይህ ስኬት እንደሆነ ሁሉ ኃላፊነትም አለው። ያለኝን [ዕውቀት] ወደ መሬት ማውረድ እና አገርንም ሕዝብንም የመጥቀም ኃላፊነት አብሮ ይመጣል” ይላሉ።

ዶ/ር ሰለሞን ከአርሶ አደር ቤተሰብ ተነስተው እስከአሁን የተጓዙት የሕይወት መንገድ ከባድ መሆኑን ሳይጠቅሱ አያልፉም።

“ከባድ ሕይወት ብዙ ያስተምራል። ቀላል ቢሆን የደረሱበትን ለመረዳትም ያዳግታል። በፈተና ሲታጀብ ስኬትን የበለጠ ማጣጣም ይቻላል” በማለት ነው ሕይወታቸውን የሚገልጹት።

ኤሮስፔስ ሜድስን

በተለይም ደግሞ አፍሪካዊ የኤሮስፔስ ሜድስን ባለሙያ መኖር በዘርፉ ያሉ ክፍተቶችን የሚሞላ ይሆናል።

የአፍሪካ አቪዬሽን ከሌሎች አህጉራት ጋር ሲነጻጸር በእኩል ደረጃ እየሄደ እንዳልሆነ ዶ/ር ሰለሞን ይናገራሉ።

ከኦታጎ ዩኒቨርስቲ ወደ አየር ኃይል ከተመለሱ በኋላ ከባድ ኃላፊነት እንደሚጠብቃቸውም ያክላሉ።

“ብዙ ፈተናዎች እንደሚያጋጥሙኝ አውቃለሁ። ግን ቢያንስ በአቪዬሽን ሜድስን ዘርፍ መሠረታዊ ነገሮች ስታንዳርድ [ደረጃ] እንዲኖራቸው ማድረግ እፈልጋለሁ” ይላሉ።

በእርግጥ አየር መንገዱ እና አየር ኃይልም የኤሮስፔስ ማዕከሎች እና የሕክምና ተቋማትም አሏቸው።

“እንደ ሌላው ዓለም ባይሆንም መሠረታዊ ደረጃ ለማስያዝ የሕክምና ቁሳቁስ እና የሰው ኃይል ከማሟላትን ጀምሮ ሙሉ ወደሆነው አገልግሎት መግባት ይቻላል።”

አሜሪካ በዘርፉ የላቀ ደረጃ ላይ ካሉ አገራት ቀዳሚውን ሥፍራ ትይዛለች።

ዓለም አቀፍ ሲቪል አቪዬሽን የተባበሩት መንግሥታት አንድ አካል ቢሆንም በአፍሪካ ውክልና የለውም። ዶ/ር ሰለሞን እነዚህን ችግሮች የመቅረፍ ሕልም ሰንቀዋል።

ዶ/ር ሰለሞን ጉርሙ ቤካ
የምስሉ መግለጫ,ዶ/ር ሰለሞን ጉርሙ ቤካ

የባሕር በር እና የአየር ክልል

ዶ/ር ሰለሞን ትኩረት ከሚሰጧቸው ጉዳዮች መካከል ኢትዮጵያ ባሕር በር አልባ አገር መሆኗ ከበረራ ጋር በተያያዘ የሚያሳድረው የምጣኔ ሃብት፣ የደኅንነት እና ዲፕሎማሲ ተጽዕኖን ነው።

“እምብዛም ትኩረት ያልተሰጠው ነገር ላንድሎክድ (የባሕር በር አልባ) መሆን ኤሮስፔስ ሎክድ [በአየር ላይም ዝግ] መሆንም ነው” ይላሉ።

ለበረራ ወይም ወደ ሕዋ ለመጓዝ በሌላ አገር በኩል ማለፍ እንደሚያስፈልግ እና ለዚህም ዓለም አቀፍ ስምምነቶችን ተከትሎ ከሌሎች አገራት ፈቃድ ማግኘት የግድ እንደሚሆን ይገልጻሉ።

“ኢትዮጵያ የአየር ክልል አቋርጣ ለመብረር የግድ የአገራት ፈቃደኛነት ያስፈልጋታል። ብዙ ሰዎች ያዩት ባሕር በር አልባ መሆንን ብቻ ነው እንጂ በአየር ክልል ያለውን ተጽዕኖም አላዩትም” ሲሉ ያስረዳሉ።

ይህ ከሚያሳድረው የምጣኔ ሃብት ጫና በተጨማሪ የብሔራዊ ደኅንነት ስጋትንም እንደሚፈጥር ይናገራሉ።

“አየር ኃይል መከላከል በሚያስፈልገው ወቅት ከሌላ አገር ፈቃድ እስኪሰጠው መጠበቅ ይኖርበታል ማለት ነው።”

በአፍሪካ ቀንድ ካለው የፖለቲካ አለመረጋጋት አንጻር፤ በጎረቤት አገራት ያሉ ግጭቶች የበረራ ክልሉን ደኅንነት ማወካቸውም ጫና እንደሚያሳድር ያክላሉ።