
ከ 4 ሰአት በፊት
ከአንድ ወር በፊት ወደ ኢትዮጵያ የገባው የኤምፖክስ (የዝንጀሮ ፈንጣጣ) ቫይረስ ዝርያ “ከፍተኛ የሞት መጠን” የሚያስከትል እና በከፍተኛ መጠን የሚሠራጭ እንደሆነ ጤና ሚኒስቴር እና የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አስታወቁ።
ከሁለት ሳምንት በፊት በበሽታው ሕይወቱ ያለፈው አንድ ወር እድሜ ያለው ሕጻን እንደሆነም ተቋማቱ ገልጸዋል።
የጤና ሚኒስቴር እና ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ይህንን ያስታወቁት ትናንት ረቡዕ ሰኔ 4/2017 ዓ.ም. ምሽት ባወጡት ‘ወቅታዊ ማብራሪያ’ ነው።
ግንቦት 16 ቀን ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ መግባቱ የተረጋገጠው ኤምፖክስ ከሁለት ሳምንት ባነሰ ጊዜ ውስጥ 18 ሰዎችን መያዙን የተቋማቱ መረጃ ያመለክታል።
በበሽታው ከተያዙት ሰዎች መካከል አምስቱ “ሙሉ ለሙሉ” ማገገማቸውን መግለጫው ያስረዳል።
የትናንቱ መግለጫ ከሁለት ሳምንት ገደማ በፊት በተመዘገበው የመጀመሪያ ሞት ሕይወቱ ያለፈውን ሰው ማንነት ይፋ አድርጓል።
መግለጫው፤ “በበሽታው ከተያዙት ታማሚዎች መካከል የአንድ ወር ሕጻን ሕይወት አልፏል” ብሏል። ሕይወቱ ያለፈው ህጻን፤ በኦሮሚያ ክልል ሞያሌ ከተማ ከተገኙት የመጀመሪዎቹ ሁለት ታማሚዎች አንዱ ነበር። ኤምፖክስ ወደ ኢትዮጵያ መግባቱ ይፋ በተደረገበት ወቅት በበሽታው የተያዙት የ21 ቀን ዕድሜ ያለው ሕጻን እና እናቱ እንደሆኑ ተገልጾ ነበር።
በሽታው ወደ ኢትዮጵያ ከገባበት ጊዜ አንስቶ እስከ ትናንት ድረስ የተደረጉ የላቦራቶሪ ምርመራዎች ብዛት 102 እንደሆነ የጤና ሚኒስቴር እና ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በመግለጫቸው ጠቅሰዋል።
እንደ ተቋማቱ ገለጻ ወደ አገሪቱ የገባውን የኤምፖክስ ቫይረስ ዝርያ ለመለየት በሕክምና ላይ ካሉ ታማሚዎች ናሙና ተወስዶ የዘረመል ምርመራ ተደርጓል።
የምርመራው ውጤት ወደ አገር የገባው “ክሌድ 1ቢ” (Clade 1b) የተባለው ዝርያ እንደሆነ እንዳሳየ ተገልጿል።
ይህ የቫይረስ ዝርያ “በአንጻሩ ከፍተኛ የሚባል የስርጭት መጠን” እንዲሁም የሚያስከትለው “የሞት መጠን በአንጻሩ ከፍተኛ” እንደሆነ የጤና ሚኒስቴር እና ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አስታውቀዋል።
“ይህ የቫይረስ ዝርያ በአንጻሩ ከፍተኛ የሚባል የስርጭት መጠን ያለውና በዚህ የቫይረስ ዝርያ ከበሽታው ጋር በተያያዘ የሚከሰት የሞት መጠን በአንጻሩ ከፍተኛ እንደሆነ በሌሎች አገራት በተገኘ ልምድ ማወቅ ተችሏል” ሲል የተቋማቱ መግለጫ ያስረዳል።

ክሌድ 1ቢ ምንድን ነው?
የዓለም የጤና ድርጀት ባለፈው ዓመት ነሐሴ ወር ኤምፖክስን ዓለም አቀፍ የሕብረተሰብ ጤና ስጋት በማለት ካወጀባቸው ዋነኛ ምክንያቶች አንዱ ይህ “ክሌድ 1ቢ” የተሰኘው የቫይረስ ዝርያ ነው።
ከዚህ ቀደም “ክሌድ” የሚባል ስያሜ በተሰጠው የኤምፖክስ ቫይረስ ቤተሰብ ግንድ ውስጥ “ክሌድ 1ኤ” እና “ክሌድ 2” የተባሉት ዝርያዎች ተሰራጭተው ነበር።
ከሌሎቹ ዝርያዎች አንጻር አዲስ የሚባለው “ክሌድ 1ቢ” በስፋት መሰራጨት የጀመረው ባለፈው ዓመት ነው።
ዝርያው፤ በዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኦፍ ኮንጎ እና በአጎራባች አገራት ወረርሽኝ አስከትሏል።
ዝርያው ከዚህ ቀደም ኤምፖክስ ባልገባባቸው ብሩንዲ፣ ኬንያ፣ ኡጋንዳ ተሰራጭቷል።
ወደ ኢትዮጵያ የገባውም ይህ የቫይረስ ዝርያ እንደሆነ ተገልጿል።
የቫይረስ ዝርያው ለመጀመሪያ ጊዜ ሪፖርት የተደረገው ባለፈው ዓመት ቢሆንም መነሻው የሚመዘዘው እ.አ.አ ከመስከረም 2023 ነው።
በወቅቱ ዝርያው የታየው የዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኦፍ ኮንጎ አንድ አውራጃ በሆነችው ሳውዝ ኪቩ በምትገኘው ካሚቱጋ ከተማ ነው።
የወርቅ ማውጫ ከተማ የሆነችው ካሚቱጋ ከፍተኛ የሰዎች እንቅስቃሴ ያለባት እና የወሲብ ንግድ በስፋት የሚካሄድባት እንደሆነች የአገሪቱ ባለስልጣናት ይናገራሉ።
ባለስልጣናቱ፤ በክፍያ የሚፈጸም ወሲብ ለቫይረሱ ሰፊ ስርጭት ዋነኛ ምክንያት መሆኑን ያነሳሉ።
ይሁን እንጂ ቫይረሱ ከእናት ወደ ልጅ፣ ከልጆች ወደ ልጆች ተላልፎ የተገኘ ሲሆን ከጽንስ መጨናገፍ ጋርም የተያያዘባቸው ጊዜያት አሉ።
“ክሌድ 1ቢ” ከሌሎች የኤምፖክስ ቫይረስ ዝርያዎች በበለጠ መልኩ እንደ መሳሳም እና ወሲብን ባሉ አካላዊ ንክኪዎች በፍጥነት ይታላለፋል።
የኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲው ፕሮፌሰር ትሩዲ ላንግ፤ “[ዝርያው] በጣም የተለየ ነው። ምክንያቱም [የሚያስከትለው] የሰውነት ሽፍታ የበለጠ ከባድ ነው፣ በሽታው ረዘም ላለ ጊዜ የሚቆይ ይመስላል፣ ከሁሉም በላይ እየተላለፈ ያለው በወሲባዊ ግንኙት እና የሰው ለሰው ንክኪ ነው። ደግሞም ከዱር እንስሳ ስጋ ጋር ግንኙነት ምንም ዓይነት አላየንም” ሲሉ ዝርያውን ገልጸዋል።
ጤና ሚኒስቴር እና የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ትናንት ባወጡት መግለጫ ወረርሽኙን “በአጭር ጊዜ” ውስጥ ለመቆጣጠር ሲባል፤ “የተቀናጀ የቅኝት፣ የመከላከል እና የምላሽ ስራዎችን” እየተከናወኑ እንደሚገኙ አስረድቷል።
በሽታው በተገኘባቸው ክልሎች “የተደራጁ የለይቶ ማከሚያ ማዕከላት” መቋቋማቸውን የገለጸው መግለጫው፤ “በሽታው ባልተገኘባቸው ክልሎች ደግሞ በሽታው ቢከሰት ለማከም የሚያስችሉ የለይቶ ማከሚያ ማዕከላትን” መዘጋጀታቸውን ጠቅሷል።
ሞንኪፖክስ በተባለ ቫይረስ አማካኝነት የሚከሰተው የዝንጀሮ ፈንጣጣ (Mpox)፤ በበሽታው የተያዙ ሰዎች ትኩሳት፣ ራስ ምታት፣ እብጠት፣ ሽፍታ፣ ሳል፣ የጀርባ እና የጡንቻ ሕመምን እንዲሁም የቆዳ ቁስለት እና ድካም ይታይባቸዋል።
በበሽታው የተያዙ ሰዎች ትኩሳት ከተከሰተ በኋላ ከፊት ጀምሮ ቀሪውን የሰውነት ክፍልን የሚያዳርስ እንዲሁም በአብዛኛው በእጅ መዳፍ እና በእግር መረገጫን የሚሸፍን ሽፍታ ያጋጥማቸዋል።
በሰውነት ላይ የሚያጋጥመው ሽፍታ በጣም የሚያሳክክ እና የሚቆጠቁጥ ሲሆን፣ በተለያዩ የለውጥ ደረጃዎች ውስጥ አልፎ በመጨረሻም እብጠት በመፍጠር ኋላ ላይም ይከስማል። ቁስለቱም ጠባሳን ትቶ ሊያልፍ ይችላል።
ባለፈው ዓመት ነሐሴ ወር ላይ የአፍሪካ በሽታዎች መቆጣጠሪያ እና መከላከያ ማዕከል (ሲዲሲ) የአፍሪካ የሕብረተሰብ ጤና አደጋ ሆኖ የታወጀው ኤምፖክስ፤ እስከ ባለፈው ሚያዝያ ወር ድረስ ጎረቤት አገራት ኬንያ እና ደቡብ ሱዳንን ጭምሮ በዘጠኝ የአፍሪካ አገራት ተከስቷል።