ዳታን በመቆጠብ ጽሑፍ ብቻ ለማንበብ

ሁለት ሄሊኮፕተሮች በበረራ ላይ

ከ 3 ሰአት በፊት

ኢራቅ በሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ የሚሠሩ እና እጅግ አስፈላጊ ሥራ የሌላቸው ሠራተኞች እና ቤተሰቦቻቸው በከፍተኛ የደህንነት ስጋት ምክንያት ሊወጡ እንደሆነ የአሜሪካ መንግሥት ምንጭ ተናግሯል።

የደህንነት ስጋት የተባለውን ጉዳይ ምንነት በአሜሪካ ባለስልጣናት በኩል በግልጽ ባይነገርም ትናንት ረቡዕ እስራኤል በኢራን ውስጥ ‘ጥቃት’ ልታካሂድ እንደሆነ ለአሜሪካ መነገሩን በአሜሪካ የቢቢሲ አጋር ሲቢኤስ ባለስልጣናትን ጥቅሶ ዘግቧል።

ይህም አሜሪካ ከቀጠናው የኤምባሲ ሠራተኞችን የምታስወጣበት አንደኛው ምክንያት ሊሆን እንደሚችል ባለስልጣኑ ገልጿል።

ይህ የሚሆነው በእስራኤል ‘ጥቃት’ ምክንያት ኢራን በኢራቅ በሚገኙ የአሜሪካ ይዞታዎች ላይ የአጸፋ እርምጃ ትወስዳለች በሚል ስጋት ነው።

ይህ ዜና የተሰማው አሜሪካ ከኢራን ጋር በቴህራን የኒውክለር ፕሮግራም ዙሪያ የሚያደርጉት ንግግር መቋረጡ በተሰማ በጥቂት ጊዜ ውስጥ ነው።

ይህ ቢሆንም በመካከለኛው ምሥራቅ የአሜሪካ ልዩ መልዕክተኛ የሆኑት ስቲቭ ዊትኮፍ በመጪው ቅዳሜ ከኢራን ባለስልጣናት ጋር ለመነጋገር ቀጠሮ እንደያዙ ተሰምቷል።

የአሜሪካ ውጪ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ባለስልጣን አገራቸው በሁሉም የአሜሪካ ኤምባሲዎች ያለውን ሁኔታ እየፈተሸች እንደምትገኝ ተናግረዋል።

“አሁን ባለን አዲስ ግምገማ በኢራቅ ያለንን ዲፕሎማቲክ ሥራዎች ለመቀነስ ወስነናል” ሲሉም አክለዋል።

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ይህንኑ ጉዳይ በተመለከተ ሲናገሩ የኤምባሲ ሠራተኞች በዚያ መቆየታቸው “አደገኛ ሊሆን የችላል። ምን እንደሚፈጠር አብረን እናያለን” ብለዋል።

ትራምፕ ኢራን የኒውክለር መሳሪያን እንድታበለጽግ እንደማይፈለጉም “ያንን አንፈቅድም” ሲሉ ተናግረዋል።

ትራምፕ ቴህራን ኒውክለር እንዳታበለጽግ የሚያስችል ስምምነት ላይ ይደረሳል ብለው ተስፋ አድርገዋል።

በዚህ ሳምንት መግቢያ ላይ ትራምፕ ከእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታኒያሁ ጋር ለ40 ደቂቃ የዘለቀ በውጥረት የተሞላ የስልክ ቆይታ አደርገው ነበር።

በዚህ የስልክ ቆይታ ኔታኒያሁ ከዲፕሎማሲያዊ አማራጭ ይልቅ ወታደራዊ እርምጃ አስፈላጊ እንደሆነ አጥበቀው ተከራክረዋል ተብሏል።

በዋሽንግተን እና በቴህራን መካካል ያለው የኒውክለር ውይይት ወሳኝ ቦታ ላይ በቆመበት በዚህ ሰዓት አሜሪካ በኢራቅ የምታወስደው ሠራተኞችን የማስወጣት እርምጃ ያለውን እውነተኛ ስጋት ምን ያህል ያሳያል የሚለው ግለጽ አይደለም።

ነገር ግን የኢራን መከላከያ ሚኒስትር አዚዝ ናስርዛዳህ የኒውክለር ስምምነቱ ቢከሽፍ እና ትራምፕ ወታደራዊ እርምጃ ኢራን ላይ የሚያዙ ከሆነ አገራቸው በቀጠናው በሚገኙ የአሜሪካ ወታደራዊ ሠፈሮች ላይ የአጸፋ እርምጃ እንደምትወስድ ተናግረዋል።

የአሜሪካ መከላከያ ሚነስትርም በኩዌት እና ባህሬን የሚገኙትን ጨምሮ በቀጠናው ባሉ አገራት የሚገኙ የአሜሪካ ወታደሮች ቤተሰቦች በፍቃዳቸው ለቅቀው እንዲወጡ ፈቅደዋል።

ኢራን ዩራኒየምን የምታበለጽገው ለኃይል ምንጭ አገልግሎት እንጂ አቶሚክ ቦምብን ለመስራት እንዳልሆነ ትናገራለች።