
ከ 4 ሰአት በፊት
የትራምፕ አስተዳደር ዘጠኝ ሺህ ሰነድ አልባ ስደተኞችን በዚህ ሳምንት ወደ ጓንታናሞ ለመላክ ማቀዱን የአሜሪካ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።
በመቶዎች የሚቆጠሩ አውሮፓውያን ስደተኞችን ያካትታል ተብሎ የታመነው ይህ ውሳኔ ወደ አገራቸው እስኪላኩ ድረስ በኩባ በሚገኘው የአሜሪካ የባሕር ኃይል ጦር ሠፈር ለአጭር ጊዜ እንዲቆዩ ይደረጋል።
በጥር ወር ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ 500 ሰው የመያዝ አቅም ያለውን የጓንታናሞ ቤይ የስደተኞች ማቆያ ማዕከል፣ 30,000 መያዝ እንዲችል ማስፋፍያ እንዲደረግለት አዝዘው ነበር።
አሜሪካ በኩባ ግዛት ውስጥ እንዲህ ዓይነት ተቋም የኖራት ለምንድን ነው? ስለ ጓንታናሞ ቤይ ምን እናውቃለን?
በጓንታናሞ ቤይ የአሜሪካ ባሕር ኃይል
ጓንታናሞ ቤይ በአሜሪካ ከሚተዳደሩ በጣም ውድ ወታደራዊ ጦር ሠፈሮች መካከል አንዱ ሲሆን፣ ምናልባትም በጣም አወዛጋቢው ነው።
እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በመስከረም 11/2001 ከተፈጸመው ጥቃት በኋላ በሽብርተኝነት ተጠርጥረው የተያዙ ሰዎች እስር ቤት በመሆን ታዋቂነትን አትርፏል።
እነዚህ እስረኞች በይፋ ክስ ሳይመሰረትባቸው እና ፍርድ ሳያገኙ ዓመታት አሳልፈዋል።
በእርግጥ ጓንታናሞ ቤይ እስር ቤት እንዲሆን የተመረጠው የአሜሪካ ግዛት ስላልሆነ እንዲሁም የአሜሪካ መንግሥት የአገር ውስጥ የሕግ ከለላዎችን መተላለፍ እንዲያስችለው ነው።
ከዚህ ቀደም በእስር ቤቱ 800 የሚጠጉ እስረኞችን የነበሩ ቢሆንም በአሁኑ ወቅት በመስከረም 11 ጥቃት አስተባባሪነት የተከሰሰውን ኻሊድ ሼክ መሐመድን ጨምሮ በሽብርተኝነት የተጠረጠሩ 15 የውጭ ዜጎች ብቻ ይገኛሉ።
ባራክ ኦባማን ጨምሮ በርካታ የዴሞክራቲክ ፓርቲ ፕሬዝዳንቶች እስር ቤቱን ለመዝጋት ቃል ገብተው የነበረ ቢሆንም ይህን ማድረግ ግን አልቻሉም።
ጓንታናሞ ከወታደራዊ እስር ቤት ርቆ በሚገኝ የተለየ ቦታ ስደተኞቹን በማቆየት ለረጅም ጊዜ ሲያገለግል ቆይቷል።
በአውሮፓውያኑ 1970ዎቹ መጀመሪያ ላይ የአሜሪካ መንግሥት በባሕር ወደ አገሪቱ ለመግባት የሚሞክሩ በተለይም ኩባውያንን፣ ሄይቲያውያን እና ዶሚኒካውያንን በቁጥጥር ሥር ሲያውል ወደ ጓንታናሞ ይወሰድ ነበር።
በ1990ዎቹ በሄይቲ በተካሄደ መፈንቅለ መንግሥት በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የአገሪቱን ወታደሮች ሸሽተው በጀልባ ወደ አሜሪካ ለመግባት የሞከሩ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ስደተኞች በደሴቲቱ ታስረው ነበር።
ከዚያም በ1994 የኩባው መሪ ፊደል ካስትሮ ደሴቲቱን ለቅቆ መውጣት የሚፈልግ ሰው ያለ ምንም ችግር መሄድ እንደሚችል ማስታወቃቸውን ተከትሎ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩት ስደተኞች በጀልባ ለመሻገር ሞክረው ነበር።
በአሁኑ ጊዜ ማዕከሉ የጓንታናሞ የስደተኞች ማቆያ ማዕከል በመባል የሚታወቅ ሲሆን፣ በቀድሞው ማዕከል ውስጥ ትንሽ ክፍል ብቻ ይገኛል።
ስለዚህ በትራምፕ አስተዳደር የታቀደውን 30 ሺህ ስደተኞች ለመያዝ እንዲችል በከፍተኛ ሁኔታ ማስፋፊያ ይሰራለታል።
በሚያዝያ ወር የወጡ የሳተላይት ምሥሎች የማቆያው ትላልቅ ክፍሎች መፍረሳቸውን ያሳያሉ።

በጓንታናሞ ማን ይታሰራል? ምን ያህልስ ያስወጣል?
ባለፈው ጥር ትራምፕ ወደ ሥልጣን መምጣታቸውን ተከትሎ በስርቆት ወይም በአመጽ ወንጀሎች ላይ ሲሳተፉ የተያዙ ሰነድ አልባ ስደተኞች በእስር ቤት እንዲቆዩ የሚፈቅደውን ሕግ ፈርመዋል።
ይህ ሕግ መጠሪያ ስሙን ያገኘው ባለፈው ዓመት በቬንዙዌላዊ ስደተኛ በተገደለችው የጆርጂያ የነርሲንግ ተማሪ ነው።
በምረጡኝ ዘመቻ ወቅት የድንበር ቁጥጥርን ለማጠናከር ቃል ለገቡት ትራምፕ የዚህ ሕግ መፈረም ትልቅ ድል ነበር።
ትራምፕ ከዚህ ቀደም በአሜሪካ የባሕር ጠረፍ ጠባቂዎች የሚያዙ ስደተኞች በቀጥታ ወደዚያ እንዲሄዱ እንደሚደረግ እና “ከፍተኛ” የማቆያ እርምጃዎች እንደሚተገበሩ ጠቁመዋል።
አክለውም ማቆያው አገሪቱ ሰነድ የሌላቸውን ስደተኞች ለመያዝ የሚኖራትን አቅም በእጥፍ ያሳድጋል ብለዋል።

በጓንታናሞ የሚገኘው የስደተኞች ማቆያ “ከክፉዎችም ክፉ ለሆኑት” ጥቅም ላይ ይውላሉ ሲሉ የአስተዳደሩ ባለሥልጣናት ተናግረዋል።
ይህም የአገር ውስጥ ደኅንነት ኃላፊ ክሪስቲ ኖም እና የሰነድ አልባ ስደተኞችን መባረር በበላይነት የሚያጋፍሩት ቶም ሆማን የሚጠቀሙበት ሐረግ ነው።
ዋይት ሐውስ በመግለጫው ተቋሙ “በአሜሪካ በሕገ ወጥ መንገድ ለሚኖሩ ከፍተኛ ወንጀለኞች ተጨማሪ የማቆያ ስፍራ በመሆን ያገለግላል፤ እንዲሁም የኢሚግሬሽን ቁጥጥር መሥሪያቤት ባልደረቦች ጥያቄዎችን ለመመለስ ይረዳል” ከማለት በዘለለ ተጨማሪ ማብራርያ አልሰጠም።
ማቆያው ምን ያህል እንደሚያስወጣ እና መቼ እንደሚጠናቀቅም ግልፅ አይደለም።
ፔንታጎን በዚህ ዓመት የመጀመሪያ ወር ብቻ በጓንታናሞ ቤይ ስደተኞችን ለማቆየት እና ለማሰር ብቻ ወደ 38 ሚሊዮን ዶላር ወጪ አውጥቷል ሲል የመከላከያ ሚኒስቴር ባለሥልጣን ተናግረዋል።

ለትራምፕ ዕቅድ ምን ምላሽ ተሰጠ?
የኩባው ፕሬዝዳንት ሚጌል ዲያዝ ካኔል የትራምፕን ዕቅድ “የጭካኔ ድርጊት” ሲሉ ኮንነውታል።
“አዲሱ የአሜሪካ መንግሥት በሕገ-ወጥ መንገድ በተያዘው የኩባ ግዛት በሚገኘው የጓንታናሞ የባሕር ኃይል ጦር ሠፈር፣ ከታዋቂው የማሰቃያ እና ሕገወጥ እስር ቤት ጎን በሺዎች የሚቆጠሩ በኃይል የተባረሩ ስደተኞች ማቆያ እንደሚሆን አስታውቋል” ሲሉ በኤክስ ገጻቸው ላይ ለጥፈዋል።
በኦሪገን ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ ፕሮፌሰር የሆኑት ዳን ቲቼኖር ለቢቢሲ ሙንዶ “ለሰብዓዊ መብት የሚጨነቅ ማንኛውም ሰው የሚያሳስበው ነገር በጓንታናሞ የሚታሰሩ ስደተኞች በቀላሉ ማምልከቻቸው ውድቅ ሊደረግ እና ላልተወሰነ ጊዜ ሊታሰሩ መቻላቸው ነው።”
በዓለም አቀፍ የስደተኞች እርዳታ ፕሮጀክት ጠበቃ የሆኑት ዲፓ አላጌሳን በበኩላቸው ትራምፕ በጓንታናሞ የታሰሩትን ስደተኞች ቁጥር ለመጨመር ያቀረቡት ዕቅድ “አስፈሪ” ብለውታል።
ድርጅታቸው በ2024 ባወጣው ሪፖርት የአሜሪካ መንግሥት በባሕር ወደ ግዛቱ ለመግባት ሲሞክሩ የያዛቸውን ስደተኞች “ኢ ሰብአዊ በሆነ” መልኩ በድብቅ ይዟል ሲል ከሷል።
“እነዚህ ስደተኞች ላልተወሰነ ጊዜ የታሰሩት እስር ቤት በሚመስል ሁኔታ ነው። ከውጭው ዓለም ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት የላቸውም። እንዲሁም የአገር ውስጥ ሚኒስቴር፣ የአገር ውስጥ ደኅንነት መሥሪያ ቤት እና ሌሎች የግል ድርጅቶች ግልጽነት እና ተጠያቂነት ሳይኖር በሚፈጸም የቅጣት ሥርዓት ውስጥ ተይዘዋል” ሲል ሪፖርቱ ያትታል።
የሕገ መንግሥት መብቶች ማዕከል ዋና ዳይሬክተር ቪንስ ዋረን ውሳኔውን “ሁላችንንም ሊያስደነግጠን ይገባል” ብለዋል።
በመግለጫቸው “ስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች እንደ የሽብር ስጋት ተቆጥረው በደሴቲቱ እስር ቤት መጣል፣ ከሕግ እና ከማኅበራዊ አገልግሎቶች እና ድጋፎች ሊወገዱ የሚገባ መሆኑን በግልጽ መልዕክት ያስተላልፋል” ብሏል።
የዓለም አቀፍ የስደተኞች እርዳታ ፕሮጀክት ሌሎች በእስር ላይ የሚገኙትን ስደተኞች እና የጓንታናሞ የስደተኞች ኦፕሬሽን ሴንተር የቀድሞ ሠራተኞችን ያነጋገሩ ማቆያ ማዕከሉ “ያረጀ፣ በሻጋታ የተሞላ እና የፍሳሽ ችግር ያለበት” ሲሉ ገልጸውታል።
“ታሳሪዎች ከጠበቆቻቸው ጋርም ሆነ ከሌሎች ጋር የስልክ ጥሪ ማድረግ አይፈቀድላቸውም፤ የሚደርስባቸውን በደል ለመናገር ቢሞክሩ ደግሞ ቅጣት ይጠብቃቸዋል” ሲል ድርጅቱ ገልጿል።

አሜሪካ ለምን በኩባ የጦር ሠፈር ኖራት?
አሜሪካ ጓንታናሞ ቤይ በአውሮፓውያኑ ከ1898 የስፔን አና የአሜሪካ ጦርነት ጀምሮ፣ ከኩባ ከአንድ መቶ ዓመት ለሚበልጥ ጊዜ በሊዝ ተከራይታለች።
አሜሪካ ስፔንን ካሸነፈች በኋላ ኩባ ነፃነቷን ያገኘችው አሜሪካ ባስቀመጣቸው ቅድመ ሁኔታዎች ነው።
ይህ ቅድመ ሁኔታ በኩባ ጉዳይ ጣልቃ የመግባት መብት እና ለባሕር ኃይል ጦር ሰፈር መሬት የመከራየት መብትን ይጨምራል።
በአውሮፓውያኑ 1903 አሜሪካ እና ኩባ፣ አሜሪካ የጓንታናሞ ቤይ ግዛትን እንድትቆጣጠር የሚያስችል የሊዝ ስምምነት ተፈራርመዋል።
በዚህ ስምምነት መሠረት አሜሪካ በዓመት 2,000 ዶላር የወርቅ ሳንቲሞች ኪራይ ትከፍላለች።
ይህ ግን በ1934 ተመጣጣኝ ዋጋ ነው ተብሎ ወደተተመነው 4,085 ዶላር ተስተካክሏል። ነገር ግን ክፍያው በአብዛኛው የይስሙላ ነው።
ኩባ የሊዝ ውሉን እና የአሜሪካን የኪራይ ክፍያዎችን ስልታዊ በሆነ መንገድ ውድቅ ታደርጋለች።
አሜሪካ ኩባ በዚህች ትንሽ ደሴት ላይ ያላት ሉዓላዊነት እንደተጠበቀ መሆኑን ትገልጻለች።
ነገር ግን የአሜሪካ እዚያ መገኘት በዋሽንግተን እና በኩባ መካከል የውጥረት መንስኤ ሆኖ ቆይቷል።
በአውሮፓውያኑ 1959 ከኩባ አብዮት በኋላ፣ የፊደል ካስትሮ መንግሥት ጓንታናሞ ይመለስልኝ ሲል መጠየቅ ጀምሯል።
የሊዝ ውሉ በግዳጅ የተፈፀመ እና በዓለም አቀፍ ሕግ መሠረት ተቀባይነት የሌለው በማለትም ተከራክሯል።