
ከ 2 ሰአት በፊት
ወደ ለንደን ጋትዊክ አየር ማረፊያ ለማቅናት ከተነሳ በኋላ በምዕራባዊ ሕንድ በተከሰከሰው የሕንድ አውሮፕላን ተሳፍረው ከነበሩ መንገደኞች መካከል ከአንድ ሰው በስተቀር ሁሉም ሕይወታቸው አልፏል።
በአውሮፕላኑ ላይ 169 የህንድ፣ ሰባት የፖርቹጋል እና አንድ የካናዳ ዜጎችን ጨምሮ 242 መንገደኞች እና የበረራ አስተናጋጆች ተሳፍረው ነበር
ባለሥልጣናት ቀደም ብለው አደጋው በደረሰበት አህመዳባድ አካባቢ የነበሩ ሰዎችም ሳይሞቱ አንዳልቀረ ተናግረዋል።
ቪሽዋሽኩማር ራምሽ የተባለ አንድ እንግሊዛዊ መንገደኛ ብቻ ከአደጋው መትረፍ የቻለ ሲሆን በሆስፒታል ሕክምና እየተደረገለት ይገኛል።
ስለ አደጋው ዝርዝር መረጃዎች እየወጡ ነው። እስካሁን በአደጋው ሕይወታቸው እንዳጡ በቢቢሲ የተረጋገጡ ሰዎች እነዚህ ናቸው።
የናናባዋ ቤተሰብ

በአደጋው ሕይወታቸውን እንዳጡ ከተነገረው እግሊዛውያን መካከል በግሎውሴስተር ነዋሪ የነበሩ ሦስት የአንድ ቤተሰብ አባላት ይገኙበታል።
አኪል ናናባዋ እና ባለቤቱ ሃና ቮራጅ እና የአራት ዓመት ልጃቸው ሳራ ናናባዋ በአውሮፕላኑ ላይ ተሳፍረው ነበር።
ከክውሲስተር ሙስሊም ማኅበረሰብ በሰጠው መግለጫ በአደጋው ሕይወታቸውን ላጡት የተሰማውን ሀዘን ገልጿል።
” የአደጋው ሰለባ ቤተሰቦች ሀዘን የሚያፅናና ምንም ዓይነት ቃል የለም። ሆኖም ቤተሰቦቻቸው እንዲፅናናኑ እና እንዲበረቱ እንፀልያለን” ብሏል።
አዳም እና ሃሲና ታጁ እና የልጃቸው ባል አልታፍሁሴን ፓቴል
የ72 ዓመት አዛውንቱ አዳም ታጁ እና የ70 ዓመቷ ባለቤታቸው ሃሲና ከ51 ዓመቱ የልጃቸው ባል አልታፍሁሴን ጋር ሆነው ነበር ከአህመዳባድ የተነሱት። ሁሉም በለንደን ከተማ ነበር የሚኖሩት።
የጥንዶቹ የልጅ ልጅ አማራህ ታጁ በአደጋው እጅግ መደናገጧንና ቤተሰቦቿን ማጣቷን ማመን እንዳልቻለች ተናግራለች።
እርሷ እንደምትለው ከአውሮፕላኑ አደጋ መረጃዎች ሲደርሳቸው አባቷ አልታፍ ታጁ እህታቸውን ለመቀበል ወደ ለንደን እያሽከረከሩ ነበር።
ፊዮንጋል እና ጀሚ ግሪንሎው -ሚክ

ፊዮና እና ጃሚ ግሩኢንሎው -ሚክ እንግሊዛዊ ጥንዶች ናቸው። በለንደን መንፈሳዊ የጤና ማዕከል አላቸው።
ጥንዶቹ አደጋው ከመድረሱ ቀደም ብለው በኢንስታግራም ገጻቸው ላይ ከአህመዳባድ አየርማረፊያ ለሊሳፈሩ መሆኑን በቪዲዮ አጋርተው ነበር።
በቪዲዮው ላይ ጥንዶቹ ሲስቁ እና ስለ ሕንዱ ጉዟቸው እርስ በርስ ሲቀላለዱ ታይተዋል።
ስይድ ቤተሰብ

አጃይ ኩማር ራምሽ
አጃይ ኩማር ራምሽ በአውሮፕላኑ ውስጥ የነበረ ሲሆን በሕይወት ከተረፈው እንግሊዛዊው ወንድሙ ቪሽዋሽኩማር ጋር ጎን ለጎን ነበር የተቀመጠው።
የአክስቱ ልጅ አጃይ ቫልጅ ለቢቢሲ እንደተናገሩት ቪሽዋሽኩማር ራምሽ ወደ ቤተሰቦቹ ደውሎ ደኅና እንደሆነ የተናገረ ሲሆን ወንድሙ ግን የት እንዳለ እንደማያውቅ ገልጿል።
ቪጃይ ሩፓኒ

ቪጃይ ሩፓኒ በጉጃራት ግዛት ሚኒስትር ነበሩ። ቪጃይ በአደጋው መሞታቸውን የአገሪቷ ሲቪል አቪየሽን ሚኒስትር ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።
ሩፓኒ የምዕራባዊ ሕንድ ግዛትን ከአውሮፓውያኑ 2016 እስከ 2021 ድረስ ሚኒስትር ሆነው አገልግለዋል።
የገዥው ብሃራቲያ ጃናታ ፓርቲ (ቢጄፒ) ፓርቲም አባል ነበሩ።
ሲንግሰን
ሲንግሰን የበረራ ቁጥሩ 171 በሆነው ኤርኢንዲያ የበረራ ቡድን አባል እንደነበረች ቤተሰቦቹ ተናግረዋል።
በአህመዳባድ በሚገኘው የሕዝብ ሆስፒታል የአክስቱ ልጅ ቲ ታንግሊንጎ ሃኦኪፕ ስለ እርሷ መረጃ ለማግኘት እየሞከረ አንደነበርና እንዳልተሳካለት ለቢቢሲ ገልጿል።
ጨምሮም ሲንግሰን በቤተሰቧ ውስጥ የገቢ ምንጭ ያላት እርሷ ብቻ ስለሆነች ሙሉ በሙሉ በእርሷ ላይ ጥገኛ የሆኑትን እናቷን እና ወንድሟን ታስዳድር ነበር።