ዳታን በመቆጠብ ጽሑፍ ብቻ ለማንበብ

በሕንድ የደረሰው የአውሮፕላን አደጋ

ከ 4 ሰአት በፊት

በሕንድ አውሮፕላን አደጋ የበረራ አስተናጋጆችን ጨምሮ 241 ሰዎች እንዲሁም በተከሰከሰበት ሥፍራ የነበሩ በርካታ ሰዎች ሕይወት አልፏል።

አውሮፕላኑ የተከሰከሰው ትናንት ሐሙስ ከሕንድ ወደ ለንደን ለመብረር ከተነሳ በኋላ ብዙም ሳይቆይ ነበር።

ከምዕራባዊ ሕንድ አህመዳባድ ከተማ የተነሳው ቦይንግ 787- 8 ድሪምላይነር አውሮፕላን፣ የሆስፒታል ሕንፃ እና የሕክምና ተማሪዎች ማደሪያ በሚገኝበት መኖሪያ አካባቢ ላይ ነው የተከሰከሰው።

ከዚህ አደጋ በአውሮፕላኑ 11ኤ የወንበር ቁጥር ላይ ተቀምጦ የነበረ የእንግሊዝ ዜግነት ያለው መንገደኛ ብቻ በአስገራሚ ሁኔታ በሕይወት ተርፏል። ግለሰቡ በኋላ ላይ “እንዴት እንደተረፍኩ አላውቅም” ሲል ለቤተሰቡ ተናግሯል።

የሕንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ “ከቃላት በላይ የሆነ ልብ ሰባሪ ክስተት” ሲሉ የገለጹት አደጋ መንስኤ እስካሁን ግልጽ አይደለም።

በሕንድ ታሪክ በርካቶች በሞቱበት በዚህ የአውሮፕላን አደጋ የሞቱ ሰዎች ቁጥር ሊጨምር እንደሚችልም ባለሥልጣናት ገልጸዋል።

‘ኤይር ኢንዲያ’ የበረራ ቁጥር ኤአይ171 ከሳርዳርቫላብህባይ ፓትል ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ የተነሳው ከረፋዱ 5፡09 ላይ የነበረ ሲሆን ከአምስት ሰዓት በረራ በኋላ ለንደን ጋትዊክ አውሮፕላን ማረፊያ ለመድረስ ነበር።

በአውሮፕላኑ 169 የሕንድ ፣ 53 የእንግሊዝ፣ ሰባት የፖርቹጋል፣ አንድ የካናዳ ዜጎች በአጠቃላይ 230 መንገደኞችንና 12 የበረራ ቡድን አባላትን አሳፍሮ ነበር።

የአካባቢው ፖሊስ ለቢቢሲ እንደገለጸው እስካሁን 204 አስክሬኖች የተገኙ ሲሆን እነዚህ ሟቾች ግን አውሮፕላኑ በወደቀበት የመኖሪያ አካባቢ የነበሩ ይሁኑ በአውሮፕላኑ ውስጥ የነበሩ አልታወቀም።

ምስሎችም በአደጋው ሥፍራ የአውሮፕላኑ ስብርባሪዎች ወዳድቀውና የአውሮፕላኑ የተወሰነ አካል ሕንፃ ላይ ተቀርቅሮ አሳይተዋል።

በርካቶች ካለቁበት ከዚህ አደጋ አንድ ሰው በሕይወት የመትረፉ አስገራሚ ዜናም የዓለም አቀፍ ሚዲያው መነጋገሪያ ሆኗል።

ከአደጋው የተረፈው እንግሊዛዊው ቪሽዋሽኩማር ራምሽ በእግሩ እየተራመደ ወደ አምቡላንስ ሲያመራ ታይቷል።

” አውሮፕላኑ ከተነሳ ከ30 ሰኮንድ በኋላ ከፍተኛ ድምጽ ተሰማ፤ ሁሉም ነገር የሆነው በቅጽበት ነበር” ሲል ሆስፒታል ውስጥ ሆኖ ለአካባቢው መገናኛ ብዙሃን ስለ ክስተቱ ተናግሯል።

የቅርብ ዘመዱ አጃይ ቫልጊ እንዳሉት ራምሽ ደኅና መሆኑን ለመግለጽ ወደ ዘመዶቹ ስልክ ደውሎ ነበር። ሆኖም አብሮት ተሳፍሮ የነበረው ወንድሙ አጃይ የት እንዳለ እንደማያውቅ ተናግሯል።

ሐሙስ ዕለት የተከሰተው አደጋ እንደ አውሮፓውያኑ 2011 ለመጀመሪያ ጊዜ በተዋወቀው 787 ድሪምላይነር አውሮፕላን ላይ የደረሰ በርካቶች የሞቱበት አደጋ ነው።

ቦይንግ በመግለጫው በሕንድ አውሮፕላን አደጋ የምርመራ ቢሮ የሚመራውን ምርመራ ለመደገፍ ዝግጁ መሆኑን ገልጿል።

የአሜሪካ እና የእንግሊዝ መርማሪዎችም ከብሔራዊ ትራንስፖርት ደኅንነት ቦርድ ጋር በመሆን የሕንድ ባለሥልጣናትን ለመርዳት ወደ ሕንድ እንደሚጓዙ ገልጸዋል።

የሕንድ የሲቪል አቪየሽን ዳይሬክቶሬት ጀነራል አውሮፕላኑ ከተነሳ ከሰከንዶች በኋላ ወደ አየር ትራፊክ መቆጣጠሪያ ክፍል ተደውሎ ነበር ብሏል።

ከዚያ በኋላ ከአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪው ጋር ያለው ግንኙነት የተቋረጠ ሲሆን ከአየር ማረፊያው ብዙም ሳይርቅ ተከስክሷል።

አውሮፕላኑ የተከሰከሰበት የመኖሪያ አካባቢ 10 ስፔሻላይዝድ የሚደረግባቸው ማዕከላትን የያዘ የሕክምና ግቢዎች የሚገኝበት ነው።

የቢቢሲ ዘጋቢ ሳቺን ፒትቫ በሥፍራው ትርምስ እንደሚታይ እና የአደጋ ጊዜ ሰራተኞች የቀሩትን ሰዎች ለማውጣት እየጣሩ እንደሆነ ገልጿል።

የጉጅራት የጤና ኃላፊ አውሮፕላኑ በብይራምጅ ጂጂብሆይ የሕክምና ኮሌጅ እና ሲቪል ሆስፒታል የተማሪዎች ማደሪያ እና የሰራተኞች መኖሪያ ላይ ማረፉን አረጋግጠዋል።

አደጋው በደረሰበት ሕንፃ ውስጥ ሆኖ ወደ ላይ የአውሮፕላኑን አካል ክፍል የሚመለከት ግለሰብ
የምስሉ መግለጫ,አውሮፕላኑ የተከሰከሰው በአህመዳባድ በርካታ ሕንፃዎች በሚገኙበት የመኖሪያ አካባቢ ነው።