
ከ 1 ሰአት በፊት
በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ኧርቪን ማሲንጋ ከሳምንታት በፊት የፌደራል መንግሥት “በራሱ ሕዝብ ላይ” የሚፈጽማቸውን የድሮን ጥቃቶች “በአፋጣኝ እንዲያቆም” በሚል በኤምባሲው ማኅበራዊ ገጾች የተላለፈው መልዕክት “በአስተዳደራዊ ስህተት” የወጣ ነው አሉ።
አምባሳደር ማሲንጋ ግንቦት 15/2017 ዓ.ም ያስተላለፉት ይህ መልዕክት ከኤምባሲው የፌስቡክ እና ኤክስ ገጾች ላይ ተነስቶ በተመሳሳይ ቀን ተሻሽሎ እንዲወጣ ተደርጓል።
አምባሳደሩ ሐሙስ፣ ሰኔ 5/2017 ዓ.ም ለጥቂት የኃገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን በሰጡት መግለጫ በሳቸው ስም የወጣውን መልዕክት ቀድመው እንደማያውቁትና በአስተዳደራዊ ስህተት የወጣ እንደሆነ ተናግረዋል።
“ስህተት ነበር። ከስህተት ያለፈ ትርጉም የሚሰጠው አይደለም። በአስተዳደራዊ ግድፈት ምክንያት ቀድሞ የነበረ እኔ ያልተመለከትኩት እና ይሁንታ ያልሰጠሁበትን ረቂቅ ነበር የተጠቀምነው [ማኀበራዊ ሚዲያ ላይ የወጣው]። ከዚያ በኋላ የኛን ትክክለኛ አቋም የሚያንጸባርቅ መልዕክት እንዲወጣ ተደርጓል ” ሲሉ ገልጸዋል።
የአሜሪካ ኤምባሲ፤ አውጥቶት የነበረውን እና አምባሳደር ኧርቪን ማሲንጋ የፌደራል መንግሥት “በራሱ ሕዝብ ላይ” የሚፈጽማቸውን የድሮን ጥቃቶች “በአፋጣኝ እንዲያቆም” ጥሪ ያቀረቡበት መልዕክት በኤምባሲው የፌስቡክ እና ኤክስ ገጾቹ ላይ ነበር የተለጠፉት።
ከጥቂት ሰዓታት በኋላ ይህ መልዕክት ተነስቶ በአዲስ ተቀይሯል።
እንደ አዲስ የወጣው የአምባሳደሩ መልዕክት ላይ የድሮን ጥቃትን በተመለከተ ለፌደራል መንግሥት የቀረበው ጥሪ “መንግሥት ከኃይል ውጪ ያሉ ሰላማዊ አማራጮችን መፈለጉን እንዲቀጥል” በሚጠይቅ ጥሪ ተተክቷል።
ለፌደራል መንግሥቱ ቀርቦ የነበረው የአምባሳደሩ መልዕክት ሁለት ሀሳቦችን ያዘለ የነበረ ሲሆን፣ አንደኛው በመንግሥት የሚፈጸሙ የድሮን ጥቃቶች እንዲቆሙ የሚጠይቅ ነው።
አምባሳደሩ ተጠቅመውበት የነበረው አገላለፅ የመንግሥት የድሮን ጥቃቶች “በራስ ሕዝብ ላይ” የሚፈጸሙ እንደሆኑ የሚያመለክት ነበር።
አምባሳደሩ በመጀመሪያው መልዕክታቸው፤ “የፌደራል መንግሥት በአፋጣኝ በራሱ ሕዝብ ላይ ድሮን መጠቀም እንዲያቆም እና ስምምነትን እንዲያመቻች እንጠይቃለን” ብለዋል።
ይህ ጥሪ የተካተተበት የአምባሳደር ማሲንጋ መልዕክት ከሰዓታት ቆይታ በኋላ ከኤምባሲው የፌስቡክ እና የኤክስ ገጾች ተነስቷል።
አምባሳደሩ በትናንትናው ዕለት በሰጡት መግለጫ ላይ ተሻሽሎ የወጣው መልዕክት ለሚመለከታቸው አካላት ደርሷል ሲሉም ገልጸዋል።
ሰባት ሰዓት ገደማ ላይ በድጋሚ የተለጠፈው የአምባሳደሩ መልዕክት የድሮንን ጥቃትን የተመለከተውን ክፍል ያስወጣ እና ለፌደራል መንግሥት የቀረበውን ጥሪ ያሻሻለ ነው።
አዲሱ መልዕክት “የፌደራል መንግሥት ከኃይል ውጪ የሆኑ ሰላማዊ አማራጮችን መፈለጉን እንዲቀጥል” የሚጠይቅ ሲሆን፣ በተጨማሪም አምባሳደሩ መንግሥት “የዜጎቹን ደኅንነት እና የመኖር ዋስትና እንዲያስቀድም” ጥሪ አቅርበዋል።
በአምባሳደሩ መልዕክት ላይ ከዚህ ውጪ የተደረገው ሌላው ማሻሻያ ለፋኖ ኃይሎች በተላለፈው መልዕክት ላይ “ጥሪ እናቀርባለን” የሚለውን “እናሳስባለን” በሚል የተካ ነው።
በመጀመሪያው መልዕክት ላይ፤ “ዩናይትድ ስቴትስ ፋኖ ከተጨባጭ እና ሰላማዊ ዓላማዎች ጋር ወደፊት እንዲመጣ ጥሪ ታቀርባለች” ይል ነበር።
አምባሳደሩ፤ “በኦሮሚያ የሚካሄደውን ግጭትን ለማቆም የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ድርድሮችን እንዲቀጥል ጥሪ እናቀርባለን” በማለት ለሌላኛው ታጣቂ ቡድን ያስተላለፉት ጥሪ አልተቀየረም።
የመንግሥት ኃይሎች በአማራ እና በኦሮሚያ ክልሎች ውስጥ ከሚንቀሳቀሱ ታጣቂ ቡድኖች ጋር በሚያደርጉት ግጭት በሰው እና በንብረት ላይ ጉዳት እየደረሰ ከመሆኑ በተጨማሪ የሕዝብ መደበኛ እንቅስቃሴ በከፍተኛ ሁኔታ እየተስተጓጎለ መሆኑን ነዋሪዎች ይናገራሉ።
ከእነዚሁ ግጭቶች ጋር በተያያዘ በሚፈጸሙ የድሮን ጥቃቶች በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ውስጥ ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸውን መንግሥታዊው የሰብአዊ መብት ኮሚሽንን ጨምሮ ሌሎች ሪፖርቶች ማመልከታቸው ይታወሳል።