
ከ 4 ሰአት በፊት
እስራኤል በኢራን የኒውክሌር ሥፍራዎች እና የጦር አዛዦቿ ላይ ያነጣጠረ ከፍተኛ ጥቃት መፈጸሟን የእስራኤል መከላከያ ኃይል አስታወቀ።
በዚህ ከባድ በተባለው ጥቃት የኢራን አብዮታዊ ዘብ ኃላፊ ሆሴይን ሳላሚ መገደላቸውን የኢራን መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።
እስራኤል ኢላማ ያደረግኩት ወታደራዊ ይዞታዎችን ነው ብትልም፤ የኢራን መገናኛ ብዙኃን በበኩላቸው በቴህራን የመኖሪያ ቤቶች ጥቃት እንደተፈጸመባቸው እና ከተገደሉትም መካከል ሲቪሊያን ይገኙበታል ብለዋል።
በኢራን መዲና ቴህራን ከፍተኛ ፍንዳታ እየተሰማ መሆኑም ተገልጿል።
የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ አገራቸው በኢራን የፈጸመችው ጥቃት ‘ኦፕሬሽን ራይዚንግ ላየን’ [የሚያንሰራራ አንበሳ ዘመቻ] ሲሉ የጠሩት አካል ነው ብለዋል።
በተጨማሪም ኢራን ለእስራኤል የህልውና ስጋት መሆኗን ተናግረዋል።
ኢራን በምላሹ በቅርቡ አጸፋዊ የመልሶ ማጥቃት ልታደርስ እንደምትችል የገለጸችው እስራኤል የአስቸኳይ ጊዜ አውጃለች።
የኢራን መንግሥታዊ ቴሌቪዥን እስራኤል በፈጸመችው ጥቃት ህጻናትን ጨምሮ ሰላማዊ ዜጎች መገደላቸውን ዘግቧል።
ሆሴይን ሳላሚ በዚህ ጥቃት ከተገደሉት ከፍተኛ አመራሮች መካከል አንዱ ናቸው።
የአገሪቱ የአቶሚክ ኢነርጂ ድርጅት ኃላፊ የነበሩት የኒውክሌር ሳይንቲስቱ ፍሬይዱን አባሲ መገደላቸውን የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።
ፍሬይዱን አባሲ ለኢራን የኒውክሌር ማበልጸግ የአንበሳውን ድርሻ እንደተጫወቱ ይነገርላቸዋል።
ሳይንቲስቱ ከዚህ ቀደም በአውሮፓውያኑ 2010 በቴህራን ጎዳና ላይ ከተቃጣባቸው የግድያ ሙከራ ተርፈው ነበር።
ሌላኛው በዚህ ጥቃት የተገደሉት የኒውክሌር ሳይንቲስት በቴህራን የሚገኘው የእስላሚክ አዛድ ዩኒቨርስቲ ፕሬዚዳንት መህዲ ቴህራንቺ ናቸው።

ኢራን አሜሪካ የእስራኤልን ጥቃት ደግፋለች ስትል የከሰሰች ሲሆን የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ በበኩላቸው አገራቸው እንዳልተሳተፈች ተናግረዋል።
የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በበኩላቸው ጥቃቶቹ እንደሚፈጸሙ እንደሚያውቁ፤ ነገር ግን አገራቸው እንዳልተሳተፈች ለፎክስ ኒውስ ገልጸዋል።
ኢራን የኒውክሌር መርሃ ግብሯን ለመቀነስ ከአሜሪካ ጋር የምታደርገውን ድርድር እንደምትቀጥል ተስፋ እንዳላቸው በድጋሚ ተናግረዋል።
“ኢራን የኒውክሌር ቦምብ ሊኖራት አይገባም እናም ወደ ወደ ድርድር ጠረጴዛው ለመመለስ ተስፋ እናደርጋለን” ሲሉ ተናግረዋል።
ኢራን አለም አቀፉ ማህበረሰብ እስራኤል የፈጸመችባትን ጥቃት እንዲያወግዝ ጥሪ አቅርባለች።
የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጥቃቱ “የዓለምን ደህንነት ታይቶ ለማያውቅ ስጋት አጋልጦታል” ብሏል።
የእስራኤል ዋና አጋር አሜሪካ ለጥቃቱ መዘዝ ተጠያቂ እንደምትሆንም ነው ሚኒስቴሩ ያስጠነቀቀው።
ጥቃቱን ተከትሎ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሁለቱም ወገኖች “ከፍተኛ መቆጠብ” እንዲያሳዩ ሲጠይቅ አውስትራሊያ በበኩሏ በዚህ መልኩ ማገርሸቱ “አስጊ” ነው ብላለች።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ እስራኤል በኢራን ነውክሌር ይዞታዎች ላይ ያደረሰችውን ጥቃት አውግዘው ሁለቱም ወገኖች ቀጠናው ወደ ከፋ ጦርነት እንዳይገባ እንዲቆጠቡ ጥሪ አድርገዋል።