ዳታን በመቆጠብ ጽሑፍ ብቻ ለማንበብ

ተስፋለም ወልደየስ

ከ 1 ሰአት በፊት

የ’ኢትዮጵያ ኢንሳይደር’ የበይነመረብ ሚዲያ መሥራች እና ዋና አዘጋጅ ጋዜጠኛ ተስፋለም ወልደየስ ከእስር መፈታቱን ጠበቃው አቶ ቤተማርያም አለማየሁ ለቢቢሲ ተናገሩ።

ተስፋለም ከእስር የተፈታው ዛሬ አርብ፣ ሰኔ 6/2017 ዓ.ም እስጢፋኖስ አካባቢ ከሚገኘው የፖሊስ መምሪያ መሆኑን ቤተማርያም ገልጸዋል።

ባለፈው ማክሰኞ ሰኔ 3/ 2017 ዓ.ም የአዲስ አበባ ከተማ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት፣ ቂርቆስ ምድብ ችሎት በ15 ሺህ ብር የገንዘብ ዋስትና ከእስር እንዲፈታ ወስኖ ነበር። ሆኖም ፖሊስ ለአዲስ አበባ ይግባኝ ሰሚ ችሎት አቤቱታ በማቅረቡ ሳይፈታ ቀርቷል።

ይግባኝ ሰሚ ችሎት ሰኔ 4/ 2017 ዓ.ም. ጉዳዩን ከመረመረ በኋላ የፖሊስን አቤቱታ ውድቅ በማድረግ የስር ፍርድ ቤቱን ውሳኔ በማጽናት ጋዜጠኛው የዋስትና መብቱ እንዲጠበቅለት በድጋሚ በይኗል።

ነገር ግን ፖሊስ የይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት ውሳኔን በመቃወም ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሰበር ሰሚ ችሎት በድጋሜ አቤቱታ አቅርቧል።

ሰበር ሰሚ ችሎቱ ሐሙስ፣ ሰኔ 5/ 2017 ዓ.ም የፖሊስ ይግባኝ አቤቱታ “አያስቀርብም” በሚል መወሰኑን የኢትዮጵያ ኢንሳይደር ባለቤት ሐቅ ሚዲያና ኮሚኒኬሽን ባወጣው መግለጫ ላይ አስታውቋል።

ተስፋለም የመጀመሪያውን ሌሊት ካሳለፈበት እስጢፋኖስ አካባቢ ከሚገኝ የፖሊስ መምሪያ ሰኞ ሰኔ 2 ቀን፤ 2017 ቄራ አካባቢ ወደሚገኝ የፖሊስ መምሪያ ተዘዋውሮ ነበር።

ጠበቃ ቤተማርያም “ኃላፊዎች አነጋግረውት ነው የሚወጣው” ተብሎ እስጢፋኖስ አካባቢ ወደሚገኘው ፖሊስ መምሪያ ዛሬ ረፋድ መመለሱን አስረድተዋል።

የተስፋለም የዋስትና መብት ላይ ፖሊስ ያቀረበው አቤቱታ በአዲስ አበባ ከተማ ሰሚ ችሎት “አያስቀርብም” በሚል ውድቅ የተደረገው ትናንት ረፋድ ነበር።

ነገር ግን “የፍርድ ቤቱን ትዕዛዝን ለቂርቆስ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ ለማስረከብ ቢሞከርም ተቀባይ አልተገኘም” ሲል ሐቅ ሚዲያ እና ኮሚዩኒኬሽን ትላንት ባወጣው መግለጫ አስታውቆ ነበር።

የክፍለ ከተማው ፖሊስ ጋዜጠኛ ተስፋለም ወልደየስን “ለፌደራል ፖሊስ የማስረከብ ፍላጎት እንዳለው” መገንዘቡንም ሐቅ ሚዲያና ኮሚኒኬሽን በመግለጫው ጠቁሞ ነበር።

ተስፋለም ወልደየስ ለእስር ከተዳረገ በኋላ ፍርድ ቤት በቀረበበት ወቅት ፖሊስ “ሐሰተኛ መረጃ በማሰራጨት” እንደጠረጠረው አስታውቆ ነበር።

አምነስቲ ከትላንት በስቲያ ባወጣው መግለጫ የተስፋለምን እስር አውግዞ የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ በአስቸኳይ እንዲፈቱት ጠይቆ ነበር።

ተቋሙ “ይህ ክስተት ባለሥልጣናት የሰዎችን የግል ሕይወት እና አስተያየቶችን የሚከታተሉበት አሳሳቢ አዲስ እውነታን የሚያንጸባርቅ ነው። የእሱ የዘፈቀደ እስር በአገሪቷ ውስጥ ጨቋኝ ልምምዶች እየተስፋፉ መምጣታቸውን ያሳያል” ብሏል።

የጋዜጠኞች መብት ተሟጋቹ ሲፒጄም በተመሳሳይ ቀን ባወጣው መግለጫ ተስፋለም ወልደየስ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ከእስር እንዲለቀቅ አሳስቦ ነበር።

የሲፒጄ የአፍሪካ ፕሮግራም አስተባባሪ ሙቶኪ ሙሞ “ፍርድ ቤት እንዲለቀቅ ትዕዛዝ ካስተላለፈ በኋላ ተስፋለም ወልደየስ በእስር ላይ መቆየቱ የኢትዮጵያ መንግሥት ለፍትህ ሂደቶች እና የፕሬስ ነጻነት ግድየለሽ መሆኑን ያሳያል” ብለዋል።

የኢትየጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ማኅበር በበኩሉ ትላንት ሐሙስ ባወጣው መግለጫ ጋዜጠኛው የዋስ መብቱ ተጠብቆለት ከእስር እንዲለቀቅ መጠየቁ ይታወሳል።

ተስፋለም ወልደየስ ከጋዜጠኝነት ስራው ጋር በተያያዘ ለእስር ሲዳረግ ይህ የመጀመሪያው አይደለም።

ከሦስት ዓመት በፊት መስከረም 22/2014 ዓ.ም. በፖሊስ ታስሮ ከሶስት ቀናት በኋላ ተፈትቷል።

ከዚህ በተጨማሪም ከዓመታት በፊት ከዞን ዘጠኝ ጦማሪዎች ጋር ለረዥም ጊዜ ታስሯል።

ተስፋዓለም ከእስር ከወጣ በኋላ በኬንያና በኡጋንዳ ውስጥ በስደት በቆባቸው ጊዜያት ኢትዮጵያን እና የአካባቢው አገራትን የሚመለከቱ ዜና እና የተለያዩ ፊቸሮች የሚቀርቡበት ‘ሐበሻዊ ቃና’ የተሰኘ ጋዜጣ መስርቶ ነበር።

ተስፋለም በአገር ውስጥ በሰብ ሰሃራን ኢንፎርመር፣ አዲስ ፎርቹን እና በአዲስ ነገር ጋዜጦች ላይ የሠራ ሲሆን ወደ ጀርመን በመሄድ የጀርመን ድምጽ የአማርኛው ክፍል ውስጥ ሲሰራ ነበር።