
25 ሰኔ 2024
ተሻሽሏል ከ 5 ሰአት በፊት
እስራኤል በፈጸመችው ጥቃት በርካታ የአገሪቱ ከፍተኛ ወታደራዊ አዛዦች እና የኒውክሌር ሳይንቲስቶች መገደላቸውን ኢራን አረጋግጣለች።
በጥቃቱ የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ የአየር ኃይል አዛዥን ጨምሮ ቢያንስ 20 የኢራን ወታደራዊ ኃይል ከፍተኛ አዛዦች ተገድለዋል። ይህ ኢራን የምትመካበት ወታደራዊ ኃይል ማን ነው? ምንስ አቅም አለው?
* * * *
የኢራን እስላማዊ አብዮት የምዕራባዊያን ወዳጅ የነበረውን የሻህ መንግሥትን ከሥልጣን አውርዶ ቦታውን ከያዘ በኋላ ኢራን እና ምዕራባዊያን አስርታትን ያስቆጠረ ጠላትነት ውስጥ ናቸው።
ኢራን በወታደራዊ ኃይል እየተጠናከረች በመምጣት ታካሂደዋለች የሚባለው የኒውክሌር ግንባታ ዋነኛ ስጋት ከመሆኑ በተጨማሪ፣ በመካከለኛው ምሥራቅ ውስጥ ኃያል የሚባሉ ታጣቂ ቡድኖችን በግልጽ በመደገፍ ምዕራባውያን እና ወዳጆቻቸውን እንቅልፍ ነስታለች።
የአገሪቱን እስላማዊ ሥርዓት ለመጠበቅ እንዲሁም መደበኛ ጦር ሠራዊቱን ለመደገፍ በሚል ከ40 ዓመታት በፊት የተቋቋመው የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብም ዘወትር በምዕራባውያን ስሙ የሚነሳው የአገሪቱ የጦር ክፍልም ተጠቃሽ ነው።
አብዮታዊው ዘብ በተለያዩ “የሽብር እና የመብት ጥሰት ተግባራት ውስጥ ተሳትፏል” በሚል አሜሪካ እና ካናዳ የጦር ክፍሉን ብርተኛ ብለው ፈርጀውታል።
አብዮታዊ ዘቡ በአሁኑ ወቅት በኢራን ውስጥ ዋናው የጦር፣ የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ኃይል ሆኗል። ከአገሪቱ የበላይ መሪ አያቶላህ አሊ ኻሜኒ እና ከሌሎች ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋርም የቅርብ ግንኙነት አለው።
የኢራን አብዮታዊ ዘብ ከ190 ሺህ በላይ ወታደሮች እንደሚኖረው የሚገመት ሲሆን፤ የራሱን የምድር፣ የባሕር እና የአየር ኃይል አጠናክሯል። ወሳኝ የሚባሉትን የኢራንን ስልታዊ የጦር መሣሪያዎችንም የሚቆጣጠረውም ይኸው ኃይል ነው።
ከዚህም በተጨማሪም በአገር ውስጥ የሚነሱ ተቃውሞችን ማፈን ዋነኛ ሚናው የሆነው “ባሲጅ” በመባል የሚታወቀው የሚሊሻ ኃይልን እንዲሁም የአገሪቷ የኢኮኖሚ አካል ተደርገው የሚቆጠሩትን ግብረ ሰናይ ድርጅቶችንም ያስተዳድራል።
ይህ ብቻም ሳይሆን አብዮታዊ ዘቡ ከኢራን ውጪ በሚንቀሳቀሰው “ኩድስ” (ኢየሩሳሌም) ተብሎ በሚጠራው የጦር ክንፉ አማካኝነት በመካከለኛው ምሥራቅ ለሚገኙ አጋር መንግሥታት እና ታጣቂ ቡድኖች ገንዘብ፣ የጦር መሣሪያ፣ ቴክኖሎጂ፣ ሥልጠናዎችን እንዲሁም ምክር በመስጠት ተፅዕኖ ያሳድራል።
አሜሪካ ኩድስ ኃይልን ሽብርተኛ ቡድኖችን በመደገፍ እንዲሁም በኢራቅ እና በመካከለኛው ምሥራቅ በመቶዎች ለሚቆጠሩ አሜሪካውያን እና የአጋር አገራት ጦር ሠራዊት አባላት ሞት ምክንያት የሆነ ጥቃትን በመፈፀም ትከሰዋለች።
በዚህም እአአ ጥር 3/2020 አሜሪካ በባግዳድ በፈፀመችው የድሮን ጥቃት የኩድስ ኃይልን ዋና አዛዥ የነበሩትን ሜጀር ጄነራል ቃሲም ሶሌይማኒን ገድላለች።
በወቅቱ የመከላከያ መሥሪያ ቤቷ ሶሌይማኒ በኢራቅ አሜሪካዊ ተቋራጭን የገደለ የሮኬት ጥቃት ማቀነባበራቸውን እና አሜሪካዊ ዲፕሎማቶች እንዲሁም ወታደሮች ላይ ጥቃት ለመፈፀም ዕቅድ እንደነበራቸው ገልጿል።
አያቶላህ ኻሜኒም ለጄነራላቸው ግድያ “የኃይል የበቀል እርምጃ” እንዲወሰድ ጥሪ አቅርበው የነበሩ ሲሆን፣ ይህም ወደ ባሰ ግጭት ሊያመራ ይችላል የሚል ስጋትን በወቅቱ ፈጥሮ ነበር።

የአብዮቱ ጠባቂዎች
ከአውሮፓውያኑ የ1979 አብዮት በፊት የኢራኑ የመጨረሻው ንጉሥ መሐመድ ሪዛ ፓህላቪ ብሔራዊ ፀጥታን ለማረጋገጥ እና ሥልጣናቸውን ለማስጠበቅ የሚተማመኑት በጦር ኃይላቸው ነበር።
በአያቶላህ ሩሆላህ ኻሜኒ የሚመሩት አዲሶቹ እስላማዊ ባለሥልጣናትም ይህንን በመከተል ነበር አብዮታቸውን እና አመራራቸውን ለማጠናከር ቁርጠኛ የሆነ ጠንካራ ኃይል እንደሚያስፈልጋቸው የተገነዘቡት።
በመሆኑም የሃይማኖት መሪዎቹ፤ መደበኛ ጦሩ (አርተሽ) የኢራንን ዳር ድንበር እንዲጠብቅ፣ የውስጥ ወሰኖችን ሥርዓትን እንዲያስከብር፤ ሌላ የጥበቃ ቡድን ደግሞ እስላማዊ ሥርዓቱን እንዲከላከል የሚፈቅድ አዲስ ሕገ መንግሥት አወጡ።
በተግባር ግን የጥበቃ ቡድኑ በሕገ መንግሥቱ ከተሰጠው ሚና ሲወጣ ይታይ ነበር። አብዮታዊ ዘቡ ከተሰጠው ኃላፊነት ውጪ ሕዝቡን ደንብ እና ሥርዓት እንዲያከብር የሚያደርግ ሲሆን የራሱን ጦር፣ የባሕር እና የአየር ኃይልም አቋቁሟል።
አብዮታዊ ዘቡ መደበኛ ጦሩ ካሉት 230 ሺህ ወታደሮች ያነሱ ሠራዊት ቢኖረውም፣ በኢራን እንዲሁም አገሪቷ ከፈፀመቻቸው ወታደራዊ ዘመቻዎች ጀርባ ያለ ዋነኛ ወታደራዊ ኃይል ተደርጎ ነው የሚታሰበው።
በእስራኤል ጥቃት የተገደሉት የአብዮታዊ ዘቡ ዋና አዛዥ ሜጀር ጄኔራል ሆሴን ሳላሚ እና ከፍተኛ መኮንኖችም የአገሪቱ የበላይ መሪን ሲያማክሩ ቆይተዋል።
የአብዮታዊ ዘቡ የባሕር ኃይልም 20 በመቶ የሚሆነው የዓለም የነዳጅ አቅርቦት የሚያልፍበትን እና የባሕረ ሰላጤ አገራትን ከሕንድ ውቅያኖስ ጋር የሚያገናኘውን የሆርሙዝ ባሕር ወሽመጥ የመቆጣጠር ኃላፊነት አለው።
የባሕር ኃይሉ በዚህ ሥልጣኑ ያሉትን አነስተኛ የጦር ጀልባዎች በመጠቀም ወደ ኢራን የውሃ ግዛት ቀርበዋል ያላቸውን የአሜሪካ የጦር መርከቦች ማስቆሙ እና ዓለም አቀፍ የመርከብ ጉዞዎችን አቅጣጫ ማስቀየሩ መነጋገሪያ ሆኖ ነበር።

የውጊያ አውሮፕላኖች በሥሩ የሌሉት የአብዮታዊ ዘቡ አየር ኃይል ኢራን ያሏትን ሚሳዔሎች የመቆጣጠር ኃላፊነት አለው።
አሜሪካ እንደምትለው ኢራን የተጠናቀቁ አሊያም በመበልጸግ ላይ ያሉ ከአስር በላይ የባሊስቲክ ሚሳዔል ሥርዓቶች እንዲሁም በመቶዎች የሚቆጠሩ ሚሳዔሎች ክምችት ያላት ሲሆን፣ በመካከለኛው ምሥራቅ ትልቅ የባሊስቲክ ሚሳዔል ኃይል ባለቤት ናት።
አሁን እስራኤል በኢራን ውስጥ ያሉ የኒውክሌር ማዕከላት፣ የሚሳዔል ማስወንጨፊያዎችን እና የአየር ጥቃት መከላከያ ሥርዓቶች ላይ ፈጸምኩ ባለችው ጥቃት ምን ያህሎቹ እንደወደሙ የታወቀ ነገር የለም።
ኢራን ከዚህ ቀደም በእስራኤል የተፈጸሙባትን ጥቃቶች ለመበቀል ከፍተኛ መጠን ያላቸው ድሮኖችን እንዲሁም ሚሳዔሎችን መጠቀሟ ይታወሳል።
ኢራን በአውሮፓውያኑ 2018 በሰሜን ኢራቅ እና ፓኪስታን ውስጥ በሚንቀሳቀሱ ኢራናውያን ቡድኖች እና በሶሪያ ባለው የእስላማዊ መንግሥት ቡድን ላይ የባሊስቲክ ሚሳዔሎችን ጥቃት በተደጋጋሚ ፈጽማ ነበር።
የባሕር ማዶ ኦፕሬሽኖች
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የኢራን መንግሥት የውጭ ፖሊሲውን ለማስፈፀም ይጠቀምበታል የሚባለው የአብዮታዊ ዘብ ክፍል የሆነውን ኩድስ ኃይልን ነው።
ኢራንም የኩድስ ኃይል በሶሪያ ከአስር ዓመታት በላይ በተካሄደው የእርስ በርስ ጦርነት ወቅት ከሥልጣን የተባረሩትን ባሻር አል አሳድን በመደገፍ ጉልህ ሚና ሚና ነበረው።
ኃይሉ ለፕሬዝዳንት ባሽር አል አሳድ ታማኝ የሆኑ ኃይሎችን በማማከር እና ከእነርሱ ጋር በመሆን የሚዋጉ በሺዎች የሚቆጠሩ የሺዓ ሙስሊም ሚሊሻዎችን እንዲሁም በኢራቅ አይኤስን ለማሸነፍ የረዳውን በሺዓዎች የበላይነት የሚመራውን ልዩ ኃይል በማስታጠቅ ሲደግፍ ቆይቷል።
ይህ በሶሪያ እና በአካባቢዋ የተካሄዱት ግጭቶች የእስላማዊ አብዮታዊው ቡድኑ አዛዥ የነበሩት ጄነራል ሱሌይማኒ በኢራን ውስጥ ይበልጥ እንዲታወቁ አድርጓቸዋል።
ነገር ግን ጄነራሉ ከአምስት ዓመት በፊት በዶናልድ ትራምፕ ጥቃት ኢራቅ ባግዳድ ውስጥ መገደላቸው ይታወሳል።

አሜሪካም የኩድስ ኃይል ኢራን በሊባኖስ የሚንቀሳቀሰውን ሔዝቦላህን እና የፍልስጤሙን እስላማዊ ጂሃድን ጨምሮ በመካከለኛው ምሥራቅ የሚንቀሳቀሱ እና በሽብርተኝነት ለተፈረጁ ቡድኖች ዋነኛ የድጋፍ ምንጭ ነው ትላለች።
ኢራን ይህንን የአብዮታዊ ዘብ አካል የሆነውን ኩድስ የተባለውን ቡድን “ገንዘብ፣ ሥልጠና፣ የጦር መሣሪያዎችን እና ቁሳቁሶችን በመስጠት ለማጠናከር እና ለመርዳት የምትጠቀምበት ዋነኛ ዘዴዋ ነው” ስትል ዩናይትድ ስቴትስ በይፋ ትከሳለች።
የኩድስ ኃይል በቀጥታ አሊያም በሌሎች ተላላኪዎቹ አማካኝነት ከሰባቱ አህጉራት በአምስቱ የሽብር ጥቃቶች እንዲፈፀም በማሴር እና በመፈፀም በአሜሪካ ሲከሰስ ቆይቷል።
በአውሮፓውያኑ 2011 በጆርጅታውን በሚገኝ ምግብ ቤት ቦምብ በማፈንዳት በአሜሪካ የሳዑዲ አረቢያ አምባሳደርን ለመግደል በተያዘው ዕቅድ የኩድስ ኃይል ተሳትፎ እንደነበረውም ተገልጿል።
ከአንድ ዓመት በፊትም የጀርመን ፍርድ ቤት የጀርመን – እስራኤል ቡድን የቀድሞ መሪ እና ከቡድኑ ጋር ግንኙነት ያላቸውን ሰዎች ሲሰልል በተገኘ የኩድስ ኃይል አባል ላይ የጥፋተኝነት ብይን አስተላልፏል።
እንዲህ ዓይነት ድርጊቶችም አሜሪካ እአአ ሚያዝያ 2019 የኢራን አብዮታዊ ዘብን “በውጭ ሽብርተኛ ቡድንነት” እንድተፈርጀው ምክንያት ሆኗል።
በይፋ የሚታወቅ እና መንግሥታዊ የሆነ ወታደራዊ ኃይል በሽብርተኝነት ሲፈረጅም ይህ የመጀመሪያው ነው።
ከዚህም በተጨማሪ አሜሪካ በኢራን የነዳጅ ዘይት የውጭ ንግድ ላይ የጣለችውን ማዕቀብ በማጥበቅ ምጣኔ ሃብቷ ይበልጥ እንዲዳከም እያደረገች ነው።
በምላሹም ኢራን የአጸፋ እርምጃ ወስዳለች። አብዮታዊ ዘቡ የአሜሪካ የጦር የቅኝት ድሮንን በሆርሙዝ የባሕር ወሽመጥ ላይ መትቶ የጣለ ሲሆን፣ በማስከተልም የዩናይትድ ኪግንደም ንብረት የሆነ ነዳጅ ጫኝ መርከብን በቁጥጥር ሥር አውሏል።
በተጨማሪም በኦማን ባሕረ ሰላጤ ላይ በስድስት ነዳጅ ጫኝ መርከቦች ላይ ውድመትን ካስከተሉ ተከታታይ ፍንዳታዎች ጀርባ የኢራን እጅ አለበት ስትል አሜሪካ ወንጅላለች።
ከዚያ በኋላም በሁለት የሳዑዲ አረቢያ የነዳጅ ተቋማት ላይ የድሮን እና የክሩዝ ሚሳዔል ጥቃት በመፈፀም፣ እንዲሁም የአሜሪካ ወታደሮች በሚጠቀሙበት የኢራቅ የጦር ሰፈርን በማጥቃት አንድ አሜሪካዊን በመግደልም ከሳታለች።
ኢራን ግን ክሱን አስተባብላለች።
የሮኬት ጥቃቱን ተከትሎም በአሜሪካ እና በኢራን መካከል የተፈጠረው ግጭት ተባብሶ ነበር።
ይህንንም ተከትሎ አሜሪካ የሮኬት ጥቃቱን ፈፅሞታል ብላ ባመነችው እና በኢራን በሚደገፈው የኢራቅ ሚሊሻ ቡድን – ካታይብ ሂዝቦላህ ጋር ግንኙነት አላቸው ባለቻቸው በኢራቅ እና በሶሪያ በሚገኙ አምስት የጦር ሰፈሮች ላይ የአየር ድብደባ ፈፅማለች።
በአየር ድብደባው ቢያንስ 25 ተዋጊ ሚሊሻዎች የተገደሉ ሲሆን፣ ይህም በባግዳድ በሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ አካባቢም ከፍተኛ ተቃውሞን አስነስቶ ነበር።
ከቀናት በኋላ ደግሞ የአሜሪካ ድሮን ከባግዳድ አየር ማረፊያ እየወጣ ባለ ተሽከርካሪ ላይ በተኮሳቸው ሚሳዔሎች ጄኔራል ሶሌይማኒ እና የካታኢብ ሂዝቦላህ አዛዥ የነበሩትን አቡ ማህዲ አል ሙሃንዲስን ጨምሮ በርካታ የሚሊሻ ቡድኑ መሪዎች ተገድለዋል።

የምጣኔ ሃብት አቅም
የኢራን አብዮታዊ ዘብ በአገሪቱ የሲቪል ተቋማት ላይ ወሳኝ ድርሻ አለው።
ወደ 100 ሺህ የሚጠጉ ወንድ እና ሴት እስላማዊ በጎ ፈቃደኛ ሚሊሻ ያሉትን ባሲጅ ታጣቂ ኃይልን ይቆጣጠራል። ባሲጅ ለአብዮቱ ታማኝ ሲሆን፣ ብዙ ጊዜ በአገሪቱ ውስጥ የሚፈጠሩ ተቃውሞዎችን ለመበተን ይጠቀምበታል።
አብዮታዊ ዘቡ እና ባሲጅ በአውሮፓውያኑ 2009 አወዛጋቢ የነበረውን የቀድሞው ፕሬዝዳንት መሐመድ አሕመዲነጃድ እንደገና መመረጥን ተከትሎ የተቀሰቀሰውን ተቃውሞ አስቁመዋል።
በዚህ ተቃውሞ በርካታ የተቃዋሚ ደጋፊዎች የተገደሉ ሲሆን፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ታስረው ነበር።
የአብዮታዊ ዘቡ ኃይል፣ ከአያቶላህ ኻሜኒ ጠንካራ ድጋፍ ጋር በኢራን ፖለቲካ ቁልፍ ተዋናይ መሆን ችሏል።
የአብዮታዊ ዘብ መኮንኖችም በመንግሥት፣ በምክር ቤት እና በሌሎች ተቋማት ላይ ወሳኝ ቦታዎችን ይዘዋል።
የአብዮት ዘብ መኮንኖችም በተደጋጋሚ የመንግሥትን ፖሊሲዎች ይተቻሉ።
የቀድሞው ዋና ኮማንድ ሜጀር ጄነራል መሐመድ አሊ ጃፋር፣ ኢራን በ2015 ከዓለም ኃያላን ጋር ካደረገችው የኒውክሌር ስምምነት ጋር በተያያዘ በፕሬዝዳንት ሐሰን ሩሃኒ የቀረቡ ሃሳቦችን በግልጽ ሲቃወሙ ነበር።
በኢራን ወታደራዊ እና ፖለቲካዊ መድረኮች ላይ ጉልህ ሚና ያለው አብዮታዊ ዘቡ፣ የአገሪቱን ምጣኔ ሃብትን ሲሶ ያህሉን እንደተቆጣጠረውም ይታሰባል።
ከወታደራዊ ዘርፉ ባሻገር አብዮታዊ ዘቡ በቤቶች፣ በግድብ እና በመንገድ ግንባታ፣ በነዳጅ እና ጋዝ ፕሮጀክቶች፣ በምግብ፣ በትራንስፖርት እንዲሁም በትምህርት እና በባህል ተግባራት ላይ በንቃት ይሳተፋል።
የአብዮታዊ ዘቡ የምህንድስና ክንፍ “ኻታም ኦል አንቢያም” በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሠራተኞች እንዳሉት የሚነገር ሲሆን፣ በግንባታ እና በምህንድስና ውሎች በቢሊዮኖች የሚቆጠሩ ዶላሮችን ያገኛል።
ከኢራን ምጣኔ ሃብት መዳከም ጋር በተያያዘ ተቃውሞዎች ሲያጋጥማቸው የነበሩት ፕሬዚደንት ሮሃኒ፣ የተንሰራፋውን የአብዮታዊ ዘቡን የንግድ ኢምፓየር በተደጋጋሚ ተችተዋል።
በአንድ ወቅትም ቡድኑን የመንግሥት ተቋማትን ያስፈራ “መሣሪያ ያለው መንግሥት” ሲሉ ገልጸውት ነበር።