
ከ 1 ሰአት በፊት
የሕንድ አውሮፕላን በተከሰከሰበት አህመዳባድ የበረራ መረጃዎችን የያዘው ጥቁር ሳንዱቅ መገኘቱን የአገሪቷ ሲቪል አቪየሽን ሚኒስትር ገለጹ።
ጥቁሩ ሳንዱቅ አደጋው ከደረሰ ከ28 ሰዓታት በኋላ በሕንድ የአውሮፕላን አደጋ ምርመራ ቢሮ መገኘቱን ሚኒስትር ሞሃን ናይዱ ኪንጃራቡ አረጋግጠዋል።
አውሮፕላኑ ሐሙስ ዕለት ወደ ለንደን ለመብረር ከተነሳ ከ60 ሰከንዶች በኋላ ነበር በመኖሪያ አካባቢ ተከስክሶ ከአንድ ተሳፋሪ በስተቀር የሁሉም 241 ተሳፋሪዎች ሕይወት ያለፈው።
አንድ ባለሥልጣን ለቢቢሲ እንደተናገሩት አውሮፕላኑ በወደቀበት ሥፍራ የነበሩ ስምንት ሰዎችም ሕይወታቸውን አጥተዋል።
የአደጋው ምክንያት እስካሁን ግልጽ አይደለም።
ሚኒስትር ኪንጃራቡ ” የጥቁሩ ሳንዱቅ መገኘት የአደጋውን ምክንያት ለመመርመር እንዲሁም የሚነሱ ጥያቄዎችን ለመመለስ ወሳኝ እርምጃ ነው” ብለዋል።
አውሮፕላን ትንሽ፣ ነገር ግን የበረራ መረጃዎችን የሚቀዱ ሁለት ጥቁር ሳንዱቆች አሉት።
አንደኛው እንደ ከፍታና ፍጥነት ያሉ የበረራ መራጃዎችን ይመዘግባል። ሌላኛው ደግሞ ከአብራሪው አንዳንድ ጊዜም ከበረራ አስተናጋጆች የበረራ መቆጣጠሪያ ክፍል የሚወጡ መረጃዎችን የሚቀዳ ነው።
በመሆኑም መርማሪዎች አብራሪዎች ምን እንዳሉና የተሰሙ ያልተለመዱ ድምጾችን ከሳንዱቁ ማዳመጥ ይችላሉ።
ምርመራው በሕንድ የአውሮፕላን አደጋ ምርመራ ቢሮ እየተመራ ሲሆን በአሜሪካ እና በዩናይትድ ኪንግደም የምርመራ ቡድኖች ድጋፍ እየተደረገለት ነው።
የአውሮፕላን አምራቹ ቦይንግ ዋና ኃላፊ ኬሊይ ኦርትበርግ በበኩላቸው ድርጅታቸው ለምርመራው ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
ኤር ኢንዲያ እንዳለው በቦይንግ 787 ድሪምላይነር አውሮፕላኑ 169 የሕንድ፣ 53 የእንግሊዝ፣ ሰባት የፖርቹጋል እና አንድ የካናዳ ዜጎች ተሳፍረው ነበር።
የበረራ ቁጥሩ ኤአይ171 ከአሕመዳባድ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ለንደን ጋትዊክ አየር ማረፊያ ለመድረስ አልሞ ነበር የተነሳው።
አርብ ዕለት በአደጋው ሥፍራ በጭስ የጠቆረው የአውሮፕላኑን ክንፍ ጨምሮ በስብርባሪዎች ተሞልቶ እና ትልቁ የአውሮፕላኑ ክፍልም በሕንፃ ላይ ተቀርቅሮ ታይቷል።
የአደጋው ሰለባዎች ቤተሰቦችም የዘመዶቻቸው አስክሬን እንዲሰጣቸው በሀዘን እየተጠባበቁ ነው።
አንድ ዶክተር የአደጋውን ሰለባዎች ማንነት ለመለየት የዘረመል ምርመራ ከማድረግ ውጭ አማራጭ አለመኖሩን ለቢቢሲ ተናግረዋል።
በአስክሬን ምርመራ ክፍል የሚሰሩት አንድ የፖሊስ ባለሥልጣንም ቤተሰቦቻቸው በፊት ገጻቸው ማንነታቸውን መለየት በመቻላቸው እስካሁን የስድስት ሟቾችን የአስክሬን ቁርጥራጭ ለቤተሰብ መሰጠቱን ለቢቢሲ ገልጸዋል።
ወንድሙ እና ቤተሰቡ በአውሮፕላኑ ተሳፍረው እንደነበር የሚገልጸው ኢምቲያዝ፣ የወንድሙን አስክሬን እስካላየ ድረስ ሞቷል ብሎ እንደማያምን ተናግሯል።
አውሮፕላኑ ሜጋኑ በተባለ የመኖሪያ አካባቢ የተከሰከሰ ሲሆን ስብርባሪውም 200 ሜትር ድረስ መበታተኑን ነዋሪዎች ገልጸዋል።
በመሆኑም ምድር ላይ የነበሩ ምን ያህል ሰዎች እንደሞቱ እስካሁን በውል አልታወቀም።ሆኖም ከአውሮፕላኑ ተሳፋሪዎች ውጭ ቢያንስ ስምንት ሰዎች መሞታቸውን ቢቢሲ ሰምቷል።
የቢጄ ሜዲካል ኮሌጅ እና ሲቪል ሆስፒታል ዲን የሆኑት ዶክተር ሚናክሽ ፓሪክህ፣ አውሮፕላኑ በኮሌጁ ውስጥ በሚገኝ ሕንፃ ላይ በመውደቁ አራት ተማሪዎቻቸው መሞታቸውን ገልጸዋል።
ዶ/ር ፓሪክሽ ጨምረውም “የዶክተሮቻችን አራት ዘመዶች አውሮፕላኑ ሲከሰከስ ግቢው ውስጥ ነበሩ፤ እነርሱም ተገድለዋል” ብለዋል።
“ስህተት መስራት ስለሌለብን ማንነታቸውን ለመለየት የዘረመል (ዲኤንኤ) ምርመራ ነው የምናደርገው። በቅንነት እየሰራን ነው። ዘመዶቻቸውም እንዲረዱንና በትዕግስት እንዲጠብቁን እንፈልጋለን። በተቻለ ፍጥነት የአስክሬን ክፍላቸውን ለቤተሰብ መስጠት እንፈልጋለን” ብለዋል።
አርብ ዕለት የሕንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ በአደጋው ሥፍራ በመገኘት ለ20 ደቂቃ ያህል ተዘዋውረው ተመልክተዋል።ሆኖም በወቅቱ ለጋዜጠኞች ያሉት ነገር የለም።

በዚያው ዕለትም የኤር ኢንዲያ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ካምፔል ዊልሰን በአደጋው ሥፍራ የተገኙ ሲሆን አደጋውን ” ልብ የሚነካ” ብለውታል።
በረራዎችን እንደሚከታተለው ፍላይትራዳር24 ድረገጽ ከሆነ ቦይንግ ዲሪምላይነር 787-8 በዓመት ከ700 በላይ በረራዎችን አድርጓል።
ኤር ኢንዲያ አውሮፕላን 11 ዓመት እድሜ ያለው ሲሆን ከሙምባይ ወደ ዱባይ ፣ ከመዲናዋ ኒው ደልሂ የአውሮፓ መዳረሻ ወደሆኑት ሚላን ፣ ፓሪስ እና አምስተርዳም ከተለመዱት የበረራ መስመሮቹ መካከል ይጠቀሳሉ።
አውሮፕላኑ ባለፉት ሁለት ዓመታት ብቻ ከአህመዳባድ ወደ ለንደን ጋትዊክ አየር ማረፊያ 25 በረራዎችን አድርጓል።
የሕንድ አቪየሽን ተቆጣጣሪ የሆነው የሲቪል አቪየሽን ዳይሬክተር ጀኔራል “የአደጋ መከላከል እርምጃ” እንደሆነ በመግለጽ በኤር ኢንዲያ ቦይንግ 787 -8 እና 787-9 ላይ ተጨማሪ የደኅንነት ፍተሻዎች እንዲደረግ አዟል።