Mesfin Mamo Tessema 

* በዓለ ደብረ ታቦር እና የቡሄ በዓል ትውፊትና አከባበሩ፤

ደብረ ታቦር ማለት የታቦር ተራራ ማለት ነው። ከ9ኙ ዓበይት በአላት መካከል አንዱ ነው።ጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በደብረ ታቦር ብርሃነ መለኮቱን፣ ክብረ መንግሥቱን መግለጡን በማሰብ በየዓመቱ ነሐሴ ፲ ፫ (13) ቀን በዓሉ በድምቀት ይከበራል፡፡ ይህ በዓል በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ምእመናን ዘንድ ‹ቡሄ› በመባል ይታወቃል፡፡ ቡሄ ማለት ‹መላጣ፣ ገላጣ› ማለት ነው፡፡ በአገራችን ክረምቱ፣ ጭጋጉ፣ ደመናው ተወግዶ የብርሃን ወገግታ የሚታይበት በዚሁ በዓል አካባቢ ስለ ኾነ በዓሉ ‹ቡሄ› ተብሎ ይጠራል፡፡ በዓለ ደብረ ታቦር ጌታችን ምሥጢረ መለኮቱን የገለጠበት፤ ብርሃን የታየበትና ድምፀ መለኮቱ የተሰማበት ዕለት ስለ ኾነ ‹የብርሃን› ወይም ‹የቡሄ› በዓል ይባላል፡፡

ቡሄ ሲመጣ የክረምቱ ጨለማነት አልፎ ወደ ብርሃን፣ ወደ ጥቢ የሚያመራበት፤ ወደ መፀው የሚገባበት፤ ወገግታ የሚታይበት፤ ሰማይ ከጭጋጋማነት ወደ ብሩህነት የሚሸጋገርበት ወቅት በመኾኑ ከቡሄ በኋላ የጠነከረ ክረምት አይኖርም፡፡ ‹‹ቡሄ ከዋለ የለም ክረምት፤ ዶሮ ከጮኸ የለም ሌሊት›› እንዲሉ፡፡ በአንዳንድ የአገራችን አካባቢዎች የቡሄ ዕለት ማታ ምእመናን ችቦ ያበራሉ፡፡ ይህም በደብረ ታቦር ለታየው ብርሃነ መለኮት ምሳሌ ነው፡፡ ሕፃናቱ ይህ በዓል ከመድረሱ በፊት ቀደም ብለው ጅራፍ ሲገምዱና ሲያጮኹ (ሲያኖጉ) ይሰነብታሉ፡፡ እናቶችም ለዚህ በዓል የሚኾን ዳቦ ለመጋገር ስንዴያቸውን ሲያጥቡ፣ ሲፈትጉ ይሰነብታሉ፡፡ በበዓሉ ዋዜማ (ነሐሴ ፲ ፪ (12) ቀን) ሕፃናት በየቤቱ እየዞሩ ‹‹ቡሄ ና በሉ፤ ቡሄ በሉ፡፡ ቡሄ መጣ፤ ያ መላጣ፤ ቅቤ ቀቡት እንዳይነጣ …›› እያሉ ይጫወታሉ፡፡ በዚህ ጊዜ እናቶች ካዘጋጁት ዳቦ እያነሡ ይሰጧቸዋል፡፡ ሕፃናቱ ‹ቡሄ› የሚሉትም ዳቦውን ነው፡፡

ጌታችን ብርሃነ መለኮቱን በገለጠበት ዕለት እረኞች ከብርሃኑ የተነሣ እየተገረሙና እየተደነቁ ወደ ቤት አልተመለሱም ነበር፡፡ የልጆቹን መዘግየት ያዩ ወላጆች ችቦ አብርተውና ዳቦ ይዘው ፍለጋ ወጥተዋል፡፡ ‹ቡሄ› ለሚሉ ልጆች ሙልሙል ዳቦ የሚሰጠውና በበዓሉ ችቦ የሚበራውም ከዚህ ታሪክ በመነሣት ነው፡፡ ለክርስትና ልጅ፣ ለአማች፣ ለምራት፣ ለዘመድ አዝማድ ዅሉ የቡሄ ዳቦ ይሰጣል፡፡ ልጆችም ዳቧቸውን እየገመጡ ጅራፍ ሲገርፉ ይውላሉ፡፡ የጅራፉ መጮኽ የድምፀ መለኮት ምሳሌ ሲኾን፣ ጅራፉ ሲጮኽ ማስደንገጡም ነቢያትና ሐዋርያት በድምፀ መለኮት መደንገጣቸውንና መውደቃቸውን ያስታውሳል፡፡

መምህረ ሐዋርያት ኢየሱስ ክርስቶስ ሦስቱን ተማሪዎቹን ጴጥሮስን፣ ያዕቆብንና ዮሐንስን ይዞ በደብረ ታቦር ምሥጢር መግለጡን በማስታዎስ የአብነት ተማሪዎች ከመምህራቸው ጋር በመኾን በዓለ ደብረ ታቦርን (ቡሄን) ያከብራሉ፤ ስሙን ይጠራሉ፡፡ የአብነት ተማሪዎች ‹‹ስለ ደብረ ታቦር›› እያሉ እኽል ከምእመናን በመለመንና ገንዘብ በማዋጣት ጠላውን ጠምቀው፣ ዳቦውን ጋግረው፣ ቆሎውን ቆልተው ለደብረ ታቦር ዕለት ሊያስቀድሱ የመጡትን ምእመናን በመጋበዝና እርስበርስ በመገባበዝ፣ እንደዚሁም ቅኔ በማበርከት በዓለ ደብረ ታቦርን በታላቅ ድምቀት ያከብራሉ፡፡ ይህም እስከ አሁን ድረስ በአብነት ትምህርት ቤቶች የሚሠራበት ነባር ትውፊት ነው፡፡

በቡሄ በዓል ወቅት የሚፈጸሙ ስረዓቶች ምሥጢር እና ውክልና

* ጅራፍ

በደብረ ታቦር በዓል በትውፊታዊ መልኩ የሚታየው ምስጢር በኢየሩሳሌም ስለሚሆነው የጌታችን ምስጢራዊ ሞቱ ነው፡፡ ጅራፍ መገመድ እና ጅራፍ ማጮኽ ሁለት ዓይነት ምስጢር ይዞ የሚከወን ትውፊታዊ ተግባር ነው፡፡ የመጀመሪያው ግርፋቱንና ሞቱን እናስብበታለን፡፡ እንዲሁም ድምፁን ስንሰማ የባሕርይ አባቱን የአብን ምስክርነት ቃል፣ እንደ ነጎድጓድ ድምፅ ያስታውሰናል፡፡

ወደ ሃገራችን ባህላዊ እንድምታው መለስ ስንል ደግሞ የታሪክ ተመራማሪው አበባው አያሌው እንደሚነግረን ልጆች ከነሃሴ አጋማሽ አከባቢ እስከ ጥቅምት የተዘራውን እህል፣ ያፈራውን አዝመራ አውሬና ወፎች እንዳይበሉት በመጠበቅ የሚተጉበት ወቅት ነው። ለዚህም ተግባራቸው እንዲረዳቸው ልጆች ከሌላው ጊዜ በተለየ ጅራፍን ይጠቀማሉ። የያዙትን ጅራፍ በማጮህ ከሩቅ ያለ አውሬን እና ወፎችን ደንግጠው እንዲበረግጉ ያደርጋሉ።

* ችቦ

ችቦ የጌታችንን ብርሃነ መለኮት መገለጥ የሚያመለክት ነው፡፡ በመሆኑም ችቦ ለኩሰን በዓሉን እናከብራለን፡፡ የዚህ ትውፊታዊ የት መጣ ግን በብርሃኑ ድምቀት የቀኑን መምሸት ያልተረዱ እረኞች በሜዳ ቀርተዋልና ወላጆች ከመንደር ችቦ ለኩሰው ልጆቻቸውን ፍለጋ ሔደዋልና ታሪኩን እያዘከርን በዓሉት እናከብራለን፡፡ የችቦው መንደድም ሌላ ትርጉም አለው፡፡ አንድ ምእመን ለሌላው ምእመን መካሪ አስተማሪ መሆኑን፣ መከራ እየተቀበለም አርአያ ምሳሌ ብርሃን መሆኑን ያሳያል፡፡ በሃይማኖትም አርአያ ምሳሌ ይሆንላቸዋል፡፡

* ሙልሙል

በችቦ ብርሃን ልጆቻቸውን ፍለጋ የወጡ ወላጆች ዳቦ ጋግረው ይዘውላቸው ወጥተዋል፡፡ ስጦታው ቤተሰባዊነትን፣ ፍቅርንና መተሳሰብን መግለጫ ነው፡፡ ወደ ቤታችን “ቡሄ” እያሉ ለሚመጡ አዳጊዎችም ዘምረው እንዳበቁ የሚሰጥ “ሙልሙል” ዳቦ አለ፡፡

የቡሄ ዳቦ የሚሉት ሙልሙል

ጎበዝ ተሰብሰብ ቡሄ እንበል።

ሆያ ሆዬ ጉዴ

ሙልሙል ሙልሙል ይላል ሆዴ።

ሕፃናቱም ሊዘምሩ ሲመጡ ዳቦ መስጠት ልማዳዊ ብቻ አይደለም፡፡ ሕፃናቱ የደቀመዛሙርት ምሳሌ ናቸው፡፡ መዝሙራቸው ደግሞ ሐዋርያት “የምሥራች” ይዘው የመምጣታቸው ምሳሌ ነው፡፡ ሐዋርያት በገቡበት አገር አስተምረው አጥምቀው የጸጋ ልጅነትን አሰጥተው በረከት አድለው እንደሚሔዱም፣ ልጆችም ዘምረው፣ አመስግነው፣ መርቀው “ውለዱ ክበዱ፣ ሃብት አግኙ፣ የመንግሥተ ሰማያት ወራሾች ያድርጋችሁ ….” ይላሉ፡፡

* የቡሄ ጭፈራ ግጥሞች

ለቡሄ ጭፈራ የሚመጡ ወጣቶች ቡሄ ወደሚጨፍሩበት ቤት በተጠጉ ጊዜ እንዲህ በማለት መምጣታቸውን ያሳውቃሉ….

መጣና መጣና ደጅ ልንጠና

ክፈት በለው በሩን የጌታዬን

ክፈት በለው ተነሳ ያንን አንበሳ

መጣና በዓመቱ እንዴት ሰነበቱ?

መጣሁኝ በዝና ተው ስጠኝ ምዘዝና

ከዛም በሩ ተከፍቶ እንዲጨፍሩ ሲፈቀድላቸው የቤቱን ጊታና የቤቱን እመቤት በግጥምና በዜማቸው ማወደስና ማሞገሱን ይያያዙታል….. በዚህም መሰረት የቤቱን አባወራ…

ወይ የኔ ጌታ የሰጠኝ ሙክት

እግንባሩ ላይ አለው ምልክት

መስከረም ጠባ እሱን ሳነክት።

የኔማ ጌታ የገደለበት

ስፍራው ጎድጉዶ ውሃ ሞላበት

እንኳን ሰውና ወፍ አይዞርበት

የአሞራ ባልቴት ውሃ ትቅዳበት።

የኔማ ጌታ የሰጠኝ ካራ

እዚህ ብመዘው ጎንደር አበራ።

በጌታዬ ቤት በጉልላቱ

ወርቅ ይፍሰስበት ባናት ባናቱ።

የኔማ ጌታ ጌታ ነው ጌታ

ሲቀመጥ ሲያምር ሲቆም ሲረታ።

የኔማ ጌታ የሰጠኝ ላም

አስር ዓመትዋ ኖረች በዓለም።

እያሉ ሲያሞግሱ እማወራዋን ደግሞ….

የኔማ እመቤት መጣንልሽ

የቤት ባልትና ልናይልሽ።

የኔማ እመቤት የጋገረችው

የንብ እንጀራ አስመሰለችው።

የኔማ እመቤት ብትሰራ ዶሮ

ሽታው ይጣራል ገመገም ዞሮ።

ወይ የኔ እመቤት የፈተለችው

የሸረሪት ድር አስመሰለችው

ሸማኔ ጠፍቶ ማሪያም ሰራችው

ለዚያች ለማሪያም እዘኑላት

ዓመት ከመንፈቅ ወሰደባት።

የማነው እንዝርት ከግልገሉ ላይ

የዚያች እመቤት የቀጭን ፈታይ።

እንዲህ እንዲህ ከጨፈሩና የሚሸለሙትን ከተሸለሙ በኋል ለዓመቱ በሰላም እንዲያደርሳቸው ተመኝተው ተመራርቀው ይለያያሉ። እኛም ለዓመቱ በሰላም እንዲያደርሰን ተመኝተን ተመራርቀን እንሰነባበት….

ክበር በስንዴ

ክበር በጤፍ

ምቀኛህ ይርገፍ

ክበር በስንዴ

ክበር በጤፍ

ምቀኛህ ይርገፍ

መልካም በዓል!!!

የዓመት ሰው ይበለን!!

ምንጭ፦ 1. የማኅበረ ቅዱሳን ድረ-ገጽ

2. ዓምደ ተዋሕዶ ድረ-ገጽ

3. “JOYFUL BOYS SINGING HOYA HOYE: BIBLICAL, SOCIAL, AND CULTURAL

CONNOTATIONS AND SYMBOLISM OF THE BUHE CELEBRATION IN ETHIOPIA”

[ በትምክህት ተፈራ – am.sewasew.com ]