መስከረም ጌታቸው /Meskerem Getachew ·Follow

ኢንጅነር ያኔ ያስረዳኸኝ ዛሬ ገብቶኛል።

2003 ዓ.ም ለ”እንደገና” ዘጋቢ ፊልም ሥራ ስንሄድ መሠረት ድንጋይ ከተጣለ ከወራት በኋላ ነበርና ከባድ መኪኖች ሲንቀሳቀሱ፣ ተራራ ንደው ሚደለድሉ፣ አᎆራው ሙቀቱ ብቻ የግርግር ቦታ ሁኖ ደረስን።

ሰውዬው ሲያወሩም ሲወስኑም በጣም ፈጣን ናቸው። ሁሌም ጊዜ የላቸውም።

እኛ አስር ጊዜ ላባችንን እየጠረግን እሳቸው ግን እንደወታደር ንቅንቅ ሳይሉ ቀረጽናቸው። እውነት ለመናገር የግድቡን ዲዛይን መሬት አውርደው ለማስረዳት ቢሞክሩም ሚታየው ሜዳና ተራራ ስለሆነ ብዙ ግልጽ አልሆነልኝም።

እናም ከቀረጻ በኋላ በድጋሚ እኔ ምልዎት ኢንጅነር ግድቡ የት ጋ ነው ሚሆነው? ውሃው፣ ሐይቁ ፣ ማመንጫው እያልሁ ጠየቅሁ። ደከመኝ ሳይሉ በዛ በረሃ ነይ ወደዚህ አሉና ከፍ ወዳለች ቦታ ወሰዱኝ።

ኢንጅነር- ያ ይታይሻል?

እኔ- የቱ?

እሳቸው- ተራራው። ከእሱ ጀምሮ እስከዚህ ግድቡ ነው። ነይ ወደዚህ ያ ማዶስ ይታይሻል?

እኔ- ከፀሐይ ቃጠሎ የተነሳ መተንፈስ እያቃተኝ በውስጤ ምነው ባልጀምርሁ ባይገባኝስ እያልሁ የቱ? አልሁ

ኢንጅነር- የእጄን አቅጣጫ ተመልከቺ እሱ ደግሞ ትልቁ ሐይቅ ነው። ነይ ደግሞ ወደዛ እንሂድ ያ ደግሞ እያሉ ሲያልቅ የሚኖረውን ገጽታ አስረዱኝ።

ኢንጅነር ስመኘው እንዲህ ናቸው። ለመጣ ለሄደው ሁሉ ያስረዳሉ። አይሰለቹም። “አትሳቀቁ ጠይቁ የእናንተ እኮ ነው”ይላሉ።

2004 ዓ.ም “የጉባ ተጋድሎ” ን ልንሠራ ደወልሁ።

ኢንጅነር ልንመጣ ነበር።

መስከረም እያስፈቀድሽ ነው? ልጅሽ እኮ ነው። ያኔ የነበረውን አረሳም አሉኝ። ደስ አለኝ። ሄድን አገኘናቸው።

በዚያው ጉልበት ነበሩ። ይመራሉም ይሠራሉም። ለእኛ የተቆፈረ መሬት ብቻ ቢታየንም እሳቸው ለእኛ እንዲገባን በቀላል ለማስረዳት ብዙ ደከሙ።

ስንመለስ ከእኔ ጋ ነው ምትመለሱት ብለው ራሳቸው መኪናቸውን እየነዱ በየከተማው እየጋበዙን ጥሩ የማይረሳ የቤተሰብ ጊዜ አሳልፈን አዲስ አበባ ገባን። 

በእነዛ ሁሉ ኪሎ ሜትሮች ስለግድቡና ግድቡ ብቻ ነበር ወሬያቸው። ስለጠቀሜታው አብዝተው ደግሞ ስለዲፕሎማሲ ጫናው። ደክሞን ተኝተን ስንነቃ እሳቸው ቀጥለዋል። መሀል ላይ ቢገርመኝ ሳላስበው “ኢንጅር ቤተሰብ ደህና ናቸው?” አልሁ። ዞረው አይተው “አላቆም አልሁ” አሉና ፈገግ ብለው “ ደህና ናቸው። ግን ብዙ እያገኘኋቸው አይደለም” አሉኝ።

2010 ዓ.ም “መንታ መንገድ” ዘጋቢ ፊልምን ለመሥራት በድጋሚ ደወልሁ “ እናንተ ስታስፈቅዱ እኮ ይከብደኛል” አሉ። ያው ትህትናቸው እንጂ ካለፍቃድ መሄድ እንደማይቻል ያውቁታል።

ተፈቀደ ሄድን። ከስር ያያዝሁት ፎቶ ከባዱን መርዶ ከመስማታችን ከወራት በፊት ለዚሁ ሥራ ሂደን ባገኘናቸው ወቅት ነበር።

ያኔ ቅርጽ ይዞ መሬት ወርዶ ነበርና ስናየው ደስ አለን።

ሁሌም አልቆ ማየት ምኞታቸው ነበር። እኛ በሳቸው ልክ ምንሮጥ አይመስላቸው። ደጋግመው “ የያዝነው ኃላፊነት ከባድ ነው” ይላሉ። አልቆ ማየትን ሲያወሩ እየተመረቀ ቦታው ያለን ያህል እንዲሰማን ያደርጋሉ። ጉጉታቸው ይጋባል።

ኢንጅነር እንዳላርቅህ አንተ ልበልህ።

ዛሬ ከ14 ዓመታት በኋላ ግድባችን ተመረቀ እኮ። እግዚአብሔር ለምን ባይባልም አንዲት ሰከንድ ቢፈቅድና ብታይ ብዬ ተመኘሁ።

ዛሬ ያኔ በባዶ መሬት ያስረዳኸኝ ገብቶኛል። እንዴት ያምራል መሰለህ?

ሁሌም ያን ድካምህን አንረሳም!

በድጋሚ እንኳን ደስ አለን።

ላሰቡ፣ ለጀመሩ፣ ለጨረሱ ሁሉ ምስጋና ይሁን!